ሚዲያን ለአዎንታዊ ነገር በመጠቀም ወጣቱ ሀገርን መገንባት አለበት – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሚዲያን ለአዎንታዊ ነገር በመጠቀም ወጣቱ ሀገርን መገንባት አለበት ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲላ ከተማ ከ1 መቶ 50 በላይ ለሚሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎችና ወጣቶች ስልጠና እየሰጠ ነው።
በስልጠናው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በዲጂታል ዓለም ውስጥ ሚዲያ ያለው ተጽዕኖ የጎላ ነው።
ሚዲያን ለሀገር ግንባታ የተጠቀሙ ሀገራት ሀገራቸውን እየገነቡ ናቸው ያሉት አስተዳዳሪው፤ ይህን የሚደግፉ ወጣቶችን ማፍራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እሴቶቻችንን ሊሸረሽሩ የሚችሉ መረጃዎችን ወጣቶች በጋራ መከላከልና በአቅም ግንባታው ዘርፍ የተጀመሩ ተግባራትም መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምስራቅ ጌቱ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የሚዲያና የዲጂታል መረጃ አጠቃቀም ክህሎትን ለማሳደግ፣ የተሳሳተ መረጃን ለማጣራት እና ማህበራዊ ሚዲያን ለልማትና ለአገር ግንባታ ለመጠቀም የሚያግዝ ነው።
ባለስልጣኑ በተሰጠው ስልጣን የአቅም ግንባታ ላይ እየሠራ ነው ብለው፤ ሚዲያን ለአዎንታዊ ነገር በመጠቀም ወጣቱ ሀገር መገንባት እንዳለበት አሳስበዋል።
ባለስልጣኑ ከስልጠናው ጎን ለጎን በተለያዩ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናልም ተብሏል።
ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣኑ ፈቃድ ያገኙ 3 መቶ 29 ሚዲያዎችንና ከ2 ሺህ 5 መቶ በላይ የማስታወቂያ ድርጅቶችንና ሌሎችንም የሚያስተዳድር ተቋም መሆኑ ተመላክቷል።
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ጥራቱ የተጠበቀ ከ500 ቶን በላይ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲሱ የካቢኔ ስብጥር ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን በተግባር ያሳየ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
ዕጩ የካቢኔ አባላት ከወትሮ በተለየ መንገድ ባለዕዳና ከፍተኛ አደራ የተጣለባቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ ማሳሰብ እወዳለሁ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)