“አካል  ጉዳተኝነት  ምንም ነገር ከማድረግ አያግድም” – ወጣት አብዱል ሀቅ ሙክሲን

 “አካል  ጉዳተኝነት  ምንም ነገር ከማድረግ አያግድም” – ወጣት አብዱል ሀቅ ሙክሲን

በሙናጃ ጃቢር

አካል ጉዳተኞች ለዘርፈ ብዙ ችግሮች  የተጋለጡ ናቸው፡፡ በተለይ ከአመለካከት ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ብዙ ችግሮችን ተቋቁመው ተምረው ለቁም ነገር በቃሁ ሲሉ ሥራ ለማግኘት ትልቅ ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡

ሥራውን አገኘው ብለው ሲደሰቱ ደግሞ ቢሮ ላይ ያለው ተፅዕኖ ሌላ ፈተና ይሆንባቸዋል። በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት ገና  አልተቀረፈም፡፡  ችግሩን  ለመቅረፍ ሁላችንም  ኃላፊነት መውሰድ አለብን፡፡ እያልን ለዛሬ የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን እነዚህን መሠል ተፅዕኖዎችን  እየተቋቋመ ያለበትን መንገድ ልናጋራችሁ  ወደናል፡፡  

ስሙ ወጣት አብዱል ሀቅ ሙክሲን  ይባላል።  ተወልዶ ያደገው ጉራጌ ዞን፥ ኢነሞር ወረዳ፥  ወርቃት በምትባል ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡

እንደአብዛኛው የኢትዮጵያ ልጅ እድገቱ  ገጠር ውስጥ ሲሆን   ቤተሰቦቹ  የሚተዳደሩት በግብርናው  ዘርፍ ነው፡፡ አብዱል አቅ  ለቤተሰቦቹ  የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡  የመጨረሻ ልጅ መሆኑን ተከትሎ ቤተሰቦቹ የተለየ ድጋፍ ያደርጉለት ነበር።  ወላጅ አባቱ ያለው  አማራጭ ትምህርት ብቻ ነው ብለው ያምኑ ስለነበር ትምርቱን እንዲማር አድርገውታል፡፡ የቤተሰቦቹም የተለየ ድጋፍ  ትምህርቱ ላይ ውጤታም እንዲሆን አግዞታል፡፡

አብዱል ሀቅ አካል ጉዳት የገጠመው  ህፃን እያለ ነበር፡፡ ሲሮጥ  እንጨት ላይ ወድቆ  ግራ እግሩ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ቤተሰቦቹ  ቢነግሩትም ኋላ ላይ ግን በፖሊዮ ምክንያት እንደ ሆነ ነው ሀኪሞቹ ያረጋገጡት፡፡ እሱም በወቅቱ ፖሊዮ በሽታ   ህፃናትን  በስፋት ያጠቃ  እነደ ነበር ቤተሰብ የነገረውን ያስታውሳል፡፡

ምንም እንኳን አቅራቢያው ትምርት ቤት ባይኖርም፥ በእግሩ እስከ 1 ሰዓት ከ30 ደቂቃ  እየተጓዘ ይማር ነበር፡፡ ጓደኞቹ እየሮጡ ሲሄዱ አንድ ጊዜ ዝናብ ዘንቦ   ወንዝ ሞልቶበት  ሊወስደው ሲል  ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ የተረፈበት አጋጣሚ እነደ ነበር አውግቶናል፡፡

ወላጅ አባቱም  መቸገሩን አይተው በቅሎ ገዝተው  ሰጡት ፡፡  በበቅሎ እየተመላለሰ  ከ1ኛ አስከ 7ኛ ክፍል “ተርሆኛ አንደኛ ደረጃ ትመህርት ቤት” ተምሯል፡፡  ከ8ኛ  አስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ “ጉብሬ አባፍራንሷ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” የተከታተለ ሲሆን ከ11ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ወልቂጤ አብሩኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተምሮ በ2003 ዓ.ም አጠናቋል፡፡

በ 2004 ዓ.ም ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ለ 5 ዓመታት ተከታትሎ 2008 ዓ.ም በጥሩ ውጤት መመረቅ ችሏል፡፡

“ከዩኒቨርስቲ ተመርቄ ስወጣ ዓላማዬ የነበረው በተማርኩት ዘርፍ ሠርቼ ቃል በገባሁት መሰረት ከራሴ አልፌ ሀገሬን እጠቅማለሁ የሚል ምኞት  ቢኖረኝም ምኞቴ ከንቱ ሆኖ ቀረ፡፡

“ሥራ ለማግኘት ብዙ ደክሜያለሁ፡፡ አዲስ አበባ ላይ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ለመሥራት ማስታወቂያ ሲወጣ አያመልጠኝም፤ እወዳደር ነበር፡፡ ገና ሲያዩኝ አይሠራም ብለው ያስባሉ፡፡ በተለይ በግንባታው ዘርፍ እንዴት  ይሠራል፤ይወድቃል ብለው ይሰጋሉ፡፡ ለደህንነት ከመጨነቅ  ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከኔ የተሻለ ሙሉ አካል ያለው መሥራት የሚችል ሰው እያለ ይቀጥሩኛል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡

 “ማስታወቂያ ሲወጣ  ተስፋ ሳልቆርጥ የሚጋብዘኝ ቦታ ሁሉ ተወዳድሬያለሁ፡፡ ሁሉም ቦታ የተስፋ ዳቦ ከመስጠት ባለፈ ችግሬን ቀርቦ  ለመረዳት እንኳን የሞከረ የለም ነበር ሲል ሥራ ለማግኘት የደረሰበትን እንግልት አጋርቶናል፡፡ 

በመጨረሻ ተስፋ ሲቆርጥ ወደ ትውልድ ቀዬው ተመልሶ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ኢነር ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት የተቀናጀ መሰረተ ልማት ባለሙያ ሆኖ  ለ 4 ዓመታት ካገለገለ በኋላ ወልቂጤ ከተማ ዝውውር አግኝቶ ጉራጌ ዞን  ንግድና ገበያ ልማት  መምሪያ ውስጥ ገበያ መሰረተ ልማት ባለሙያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ 

ከመንግስት ሥራ ውጭ በግሉ ኮንትራክትር ሆኖ  የመሥራት ዓላማ ቢኖረውም÷ በግል ለመሥራ የተቀመጡ መመሪያዎችን ስላላሟላ ሀሣቡ አልተሳካም፡፡ ለሥራ ያለው ተነሳሽነት  በመንግስት  ሥራ ብቻ ታጥሮ አልተቀመጠም፡፡ የተለያዩ ሥራዎችን  ጎን ለጎን ይሞካክራል፡፡ ከዚህም ባሻገር  በዲጂታል ዓለም ተወዳደሪ ለመሆን በኦን ላይን  አሜሪካ የሚገኝ ኢቫንጋዲ የሚባል ድርጅት ውስጥ የእስኮላር ሺፕ እድል  አግኝቶ ዌብሳይት ዲቭሎፕ ማድረግ ሥልጠና ለ1 ዓመት ተከታትሏል፡፡ ይህን አስመልክቶም፡-

“በሠለጠንኩት መሠረት  የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቢሮ ላይ ሠርቼ ለማስተዋወቅ   ብሞክርም ተቀባይነት አላገኘሁም፡፡ ይሠራል ብለው ስለማያስቡ ቦታ አልሰጡኝም፡፡  ለአካል ጉዳተኛ ያለቸው አመለካከት ገና አልተቀረፈም” ሲል  ትዝብቱን አጋርቶናል፡፡

 ከቢሮ ውጭ ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅ ብዙ ጥሮ ነበር፤ ግን አምኖ የሚቀበለው ሰው አላገኘም፡፡ “ማህበረሰቡ ገና ከቴክኖሎጂው ጋር አልተዋሀደም፡፡ ሲስተሙን ተረድተውት ቢሠሩበት ብዙ ነገር ያቀልላቸው ነበር፤ ነገር ግን ሀገራችን ላይ ያለው የግንዛቤ  እጥረት በአንዴ የሚቀረፍ አይደለም ፡፡ ለውጡ  ቀስበቀስ የሚመጣ ነው፡፡ በተለይ ክፍለ ሀገር  ላይ ትንሽ ይከብዳል፡፡ ትንሽ የክልል  ከተሞች ላይ የሚሻል ይመስለኛል። የተለያዩ ፋብሪካዎችና ካምፓኒዎችን የማግኘት ዕድል ይኖራል፡፡ የህብረተሰቡ ግንዛቤም በንፅፅር የተሻለ ነው” ሲል  አጫውቶናል፡፡  

አሁን ላይ መንግስት ወጣቱ  አዳዲስ ቴክኖሎጆዎችን እንዲተዋወቅ  እያደረገ ነው፡፡  በዚህም መሠረት ለቢሮ አድል መጥቶ  ሶስቱንም  አይነት የኮደርስ ስልጠና ወስጃለው ወደ ተግባር ለመግባት ግን አልቻለኩም፤ ምክንያቱም ግንዛቤው ገና አልዳበረም  ብሏል፡፡

አካል ጉዳተኝነት  ምንም ነገር ከማድረግ አያግድም የሚለው አብዱል ሀቅ አንዱ ሥራ ባይሳካ ሌላው ሥራ ይሳካል  የሚል እምነት ስላለው፤ ሳይታክት  የተለያዩ የሥራ አማራጮችን ሞክሯል፡፡  

አሁን ላይ ከተማረው የሥራ ዘርፍ ውጭ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ጥገናዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ የፍሪጅ ጥገና በስፋት ይሠራል። ቢሮዎች ላይ ኮምፒውተር ሲበላሽ ይሠራል።  የተለያዩ ፕሮግራሞችን ይጭናል፡፡ አሁን ላይ በሚሰራቸው ተጨማሪ ሥራዎች ከደሞዙ በላይ እንደሚያገኝ ገልጾልናል፡፡

“ከአመለካከት ጋር ተያይዞ ከቤተሰብ ምንም አይነት ችግር አልገጠመኝም፡፡ ትምህርት ቤት ላይም እንዲሁ፡፡ ከጓደኞቼ ወደ ኋላ ቀርቼ ወይም   አርፍጄ  ክፍል ስገባ መምህራኖቼ ይረዱኝ ነበር፡፡ ሥራ ዓለም ላይ ግን ከአመለካከት ጋር ተያይዞ ትልቅ ፈተና ገጥሞኛል፡፡ እንደሚታወቀው የአርተፊሻል ድጋፍ በላስቲክ ነው የሚሠራው፡፡ ሙቀት ሲሆን በጣም ያቃጥላል፡፡ ቢሮው ተከራይቼ ከምኖርበት ቤት ይርቃል፡፡ በዚህ  የተነሳ  ከቢሮ ወደ ቤት  መመላለሱ በጣም ሲከበደኝ  2004 ዓ.ም  ጀምሮ ሞተር እንዲገዛልኝ ጠይቄ ነበር፤ ነገር ግን ጠብቅ ይገዛልሀል እያሉ ይሸነግሉኛል፡፡ ሙቀቱ ሲበረታ ስለሚያቀጥለኝ አንዳንድ ጊዜ ስቀር እና ሳረፍድ ሰውሀብት ያስፈራራኛል፡፡ በያዓመቱ በጀት ሲያዝ እጠይቃለሁ አስካሁንም ድረስ እልባት አላገኘሁም፡፡  ዘንድሮ ግን ተስፋ ቆርጬ አልጠየኩም” ሲል የትራንስ ፖርት ችግር በጣም እንደፈተነው ገልጾልናል፡፡

የወደፊት ዕቅዱን ሲገልፅ፡- “የተሻለ ሥራ ሠርቼ፤ የተሻለ ቦታ መድረስ ነው ህልሜ፡፡ አሁን ባለሁበት ሁኔታ በፍፁም መቀጠል አልፈልግም፡፡ ተወዳዳሪ ሆኜ እሰከ ውጪ ድረስ ሄጄ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ከተሳካልኝ ከራሴ አልፌ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ትልቅ ምኞት አለኝ” በማለት በልበ ሙሉነት ገልጾልናል፡፡   

“ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ማስተላላፍ የምፈልገው መልክት ቢኖር ፡-  ሁል ጊዜ ስብሰባ ላይ የማነሳው ነጥብ አለ ፡፡ አካል ጉዳተኞች የጠባቂነት መንፈስ እና አልችልም የሚል አስተሳሳብ መቅረፍ አለባቸው፡፡  በርግጥ እኛ ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ ከባድ ነው፤ ነገር ግን ተምረን ፤ሠርተን  ራሳችንን መለወጥ አለብን፡፡ ከማንም በላይ የተሻለ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡ በተለያዩ ሥልጠናዎች ራሳቸውን  ማብቃት አለባቸው፡፡  እኛ ሠርተን ሌሎችን መርዳት እንደምንችል ማሳየት አለብን፡፡ 

“በተለይ ከልመና ራሳቸሁን  መቆጠብ አለባችሁ፡፡ ሰው ሊረዳን ይችላል፤ ግን ደግሞ ህይወታችንን የሚቀይር ነገር መሆን አለበት፡፡ በየቀኑ ሳንትም ቢሰጡን ምንም አይጠቅመንም፡፡ ለምሳሌ ለማህበራችን አንድ የውጭ ድርጅት በተከታታይ ፍርኖ ዱቄት በእርዳታ ይሰጡን ነበር፡፡ እና ሁልጊዜ የፍርኖ ዱቄት ምንም አያደርግልንም ብለን አስካሁን ድረስ ስላደረጉልን ድጋፍ  የምስጋና ወረቀት ሰጥተን ዘላቂ የሆነ ድጋፍ እንዲያደርጉልን ቢጋር አዘጋጀተን አቅርበናል፡፡

ቢጋሩ ተቀባይነት አግኝቶ ምላሻቸውን እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ የኮምፒዩተር ድጋፍ ቢደረጉልን ኮፒ ቤት ከፍተን መሥራት እንችላለን፡፡ መሥራት ያስከብራል መለመን ግን ያዋርዳል፡፡ ስለዚህ  ሠርተን ለሌሎች ዓርአያ  መሆን አለብን” ሲል መልክቱን አስተላልፏል፡፡