“ምንም ቢገጥመኝ ከፈተና እማራለሁ” – ወጣት አሸናፊ ሙሴ

“ምንም ቢገጥመኝ ከፈተና እማራለሁ” – ወጣት አሸናፊ ሙሴ

በደረሰ አስፋው

በእችላለሁ መንፈስ ነገሮችን ወደፊት መመልከት የተሻለ እድልን እንደሚያጎናጽፍ ያምናል፡፡ ጠንክሮ መማሩና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በመስራት ያካበተው ልምድ እንደጠቀመው ያነሳል፡፡ በሚሰራበት የስራ ዘርፍ ጥሩ ባለሙያ እንዲሆን አግዞታል፡፡

ይህ ጥሩ ተሞክሮ ደግሞ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች እንዲተርፍ ይፈልጋል፡፡ ዕውቀቱንና ልምዱን በማጋራት አካል ጉዳተኞች የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ምኞቱ ነው፡፡

የዛሬው የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን ወጣት አሸናፊ ሙሴ ሁሌም በአንድ እውነታ የታሰረ ነው፡፡ “እችላለሁና ምንም ቢገጥመኝ ከፈተና እማራለሁ እንጂ አልወድቅም” የሚል። ሌሎችም በዚህ መንገድ ቢጓዙ አትራፊ እንደሚሆኑ ነው የሚመክረው፡፡

አካል ጉዳተኞች ካለባቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና አንጻር ማንም እንዲረዳቸው ከመጠበቅ ይልቅ ብዙ መልፋት እንደሚጠበቅባቸውም ይመክራል፡፡ ራሳቸውን በእውቀት ማጎልበት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነም እንዲሁ፡፡

አሸናፊ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የወላጆቹ እና የራሱ ጥረት ለዛሬ እንዲደርስ አስተዋጽዖ አድርጎለታል። ትችላለህ ነው የሚሉት፡፡ ሲማር የሚፈልጋቸውን ግብአቶች ያሟሉለታል፡፡ እሱም በርትቶ ያጠና ነበርና ውጤታማ ሆነ፡፡ ቤተሰቦቹ በንግድ እና እርሻ ስራ ከሚያገኙት የገቢ ምንጭ ነው የሚተዳደሩት፡፡

እሱም የራሱን ህይወት ለመምራት ከ1ኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ባለፈባቸው የትምህርት ጊዜያት ጠንክሮ በመስራት ለዛሬው ህይወቱ መሰረት የጣለ ነው፡፡ ዛሬ ላይ በቀሰመው እውቀት ከራሱ አልፎ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ተርፏል፡፡

አካል ጉዳቱ የተከሰተው ከተወለደ ከ7 ዓመት በኋላ ነው፡፡ የአካል ጉዳቱ ምክንያትም በህክምና ስህተት እንደሆነ ነው የገለጸው። በህመም ምክንያት ለህክምና ክትትል ወደ ይርጋለም ሆስፒታል በሄደበት ወቅት በመርፌ ስህተት በሁለቱ እግሮቹ ላይ ለጉዳት መዳረጉን ነው ከቤተሰቡ የተረዳው፡፡

እንደመታደል ሆኖ በአካል ጉዳተኞች የሚስተዋሉ ተጽዕኖዎች በእሱ ቤተሰብ አልተከሰተም፡፡ ቤተሰብ ከመጠን ያለፈ ድጋፍ፣ ፍቅርና እንክብካቤ እንደሚደረግለት ነው የተናገረው፡፡ ድጋፍ አትችልም ከሚል አስተሳሰብ እንዳልሆነ ይገነዘባል፡፡

አሸናፊ ሙሴ ትውልዱና ዕድገቱ ሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስም በሀዋሳ ኮምቦኒ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ እስከ 12ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ የ12ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተናን ጥሩ ውጤት በማምጣት ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በጤናው ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ 2ኛ ዲግሪ ተመርቋል። በአድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በጤና አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከፋርማ ኮሌጅ በገንዘብ አስተዳደር 2ኛ ዲግሪ፣ እንዲሁም በማርኬቲንግ የአድቫንስድ ዲፕሎማ አለው፡፡

አሸናፊ በጤናው ዘርፍ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በበርካታ ተቋማት አገልግሏል፡፡ በሰራባቸው ተቋማትም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቀሰመውን ዕውቀት ለመጠቀም ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ ልምድም አዳብሮበታል፡፡ በሙያው ሀገርንና ህዝብን በማገልገሉም ደስተኛ ስለመሆኑ ነው ያጫወተን፡፡

ከዩኒቨርስቲ ከተመርቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ የሰራው ኮንሶ ዞን ነው፡፡ በአቅም ግንባታ ቢሮ በመረጃ መረብ እና በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ለ3 ዓመታት አገልግሏል፡፡

ከኮንሶ ወደ ሀዋሳ ከተማ በመምጣት በሀዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ በልማት ዕቅድ አስተባባሪነት፣ የስርአተ ምግብ ፕሮግራምና የጤና መረጃ አያያዝ ስርአት ላይ ለአመታት አገልግሏል፡፡

ወደ ቀድሞው ደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተዛውሮም በፕሮጀክት አስተባባሪነት በከፍተኛ ባለሙያነት ለረጅም አመታት አገልግሏል፡፡ በማህበራዊ ዘርፍ፤ በአካል ጉዳተኞች ጋይዳንስና ካውንስሊንግ፣ በአካል ጉዳተኞች ድጋፍና ማቋቋም፣ የፕሮጀክት ጥናትና ሀብት ማሰባሰብ፣ እንዲሁም በተለያዩ መደቦች አገልግሏል፡፡

በተለይ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሰራበት ጊዜ ረጅሙን ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ገልጾ በዚህም ደስተኛ ስለመሆኑ ነው የተናገረው፡፡

አሸናፊ አካል ጉዳተኛ በመሆኑ የአካል ጉዳተኞች መሰረታዊ መብቶች ተከብሮ ማየትን ይመኝ ነበር፡፡ ከነበረው ፍላጎትና ተነሳሽነት የተነሳ ከጤናው ዘርፍ ይልቅ አብዛኛውን የአገልግሎት ጊዜውን በአካል ጉዳተኞች ላይ በመስራቱ የመንፈስ እርካታን የፈጠረለት ስለመሆኑም ተናግሯል፡፡

የአካል ጉዳተኞች ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ በመሆን ባገለገለባቸው ጊዜያት ሰፊ ልምድ አካብቶበታል፡፡ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የአካል ጉዳተኞች ህይወት እንዲቀየር በማድረጉ ሂደት የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ አካል ጉዳተኞች ከተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።

ከ2011 ዓ.ም በኋላ በተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት የመንግስት ስራውን ለቆ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ አገልግሏል፡፡ በዚህም በሲዳማ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ 8 ወረዳዎች የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ፕሮጀክቱ አካል ጉዳተኞችን በጤናው ዘርፍ ማካተት ስለሆነ ያለውን እውቀትና ልምድ ተጠቅሞ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ያገለገለ ባለሙያ ነው፡፡

ፕሮጀክቱም ጤና እና ማህበራዊ ዘርፉን አጣምሮ ይሰራ ስለነበረ የቀደመ ልምዱ ለስራው አግዞታል፡፡ ድርጅቱ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ትልቅ ልምድ ያለው በመሆኑ እሱም ተጨማሪ ልምድም ያገኘበት ነበር። ሴቶችን በአካል ጉዳተኝነታቸው ችግር ሳይገጥማቸው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በስነ ተዋልዶና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረግ ነበር፡፡

አሸናፊ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ፕሮጀክቱ ሲቋረጥ የስራ አድራሻውን ያደረገው በሲዳማ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ነው፡፡ በጥናትና ሀብት ማሰባሰብ ከፍተኛ ኤክስፐርት በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ሁሌም አካል ጉዳተኞችን ማገልገል የመንፈስ እርካታ ለሚሰጠው አሸናፊ አሁንም በዚሁ ዘርፍ ማገልገሉ ደስታ እንደሚሰጠው ነው የተናገረው፡፡

አካል ጉዳት በርካታ ፈተናዎች ያሉበት ነው፡፡ ችግርን ለማሸነፍ መጋፈጥን ይጠይቃል። አሸናፊ ምንም እንኳ በቤተሰቡም ይሁን በማህበረሰቡ የጎላ ችግር ባይደርስበትም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድረስ ያለፈባቸው ረጅም አመታት ለአካል ጉዳተኞች ፈታኝ ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን መሠረተ ልማት አለመኖር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት፣ በሕንጻዎች ላይ ጉዳተኞችን የሚደግፉ መወጣጫዎች እጦት፣ ተመጣጣኝ መጸዳጃ አገልግሎቶች አለመኖር፣ በመጓጓዣ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት አለመደረጉ በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይናገራል።

ለስራ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመድቦ የሄደው ኮንሶ ዞን ነው፡፡ ከነበረው የትራንስፖርት እጥረት ጋር ተያይዞ ለችግር የተዳረገበት ጊዜ ነበር፡፡ በአካባቢ የመብራት፣ የውሃና ሌሎች አገልግሎቶች ያልተሟሉ በመሆኑ ሌላው የአሸናፊ ችግር ነበር፡፡ የሚሰራባቸው ቢሮዎች ለአካል ጉዳተኞች አይደለም ለጤናማ ሰውም የሚመች ቦታ አለመሆናቸውም እንዲሁ፡፡

ችግሮቹም “በቁስል ላይ እንጨት—-” እንደሚባለው አይነት ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በተላበሰው የአሸናፊነት ስነ ልቦና ችግሮችን ተጋፍጦ አሸንፏል። አካል ጉዳተኛ ነኝ ብሎ ወደ ሩቅ ቦታ አልሄድም አላለም። አካል ጉዳቱን ለሌላ ነገር አልተጠቀመበትም። ይልቁንም እችላለሁ፤ ችግሮችን አሸንፌ ህዝብንና ሀገርን አገለግላለሁ አለ እንጂ፡፡

አሸናፊ በትምህርቱ ዘርፍ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ 2ኛ ዲግሪ ይዟል፡፡ ይህን ግን እንደ ስኬት እንደማይመለከተው ነው የተናገረው፡፡ ይህ ጅምር እንጂ ፍጻሜ አይደለም ያለ ሲሆን እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የመማር ሀሳብ እንዳለው ነው የተናገረው፡፡

“መማር ለእኔ ፍላጎቴ ነው” ያለ ሲሆን ከአንዱ ዩኒቨርስቲ ሲመረቅ ወደ ሌላው ዩኒቨርስቲ በመሸጋገር በበርካታ የሙያ ዘርፎች የመማር ፍላጎት ነው ያለው፡፡

በማህበራዊ ዘርፍ ባሉ ጉዳዮች የመማርና ዕውቀቱን የማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ገልጾልናል፡፡ በተለይ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በሚያያዙ የትምህርት መስኮች ላይ ለመማር ያለው ፍላጎት ለየት ይላል፡፡ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች በማስጠበቅ ረገድ በእውቀት ላይ ተመሰረተ ድጋፍ ለማድረግ መማር መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነም ይገልጻል፡፡

“የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች ሆኜ ለማገልገል ነው ምኞቴ፡፡ በዚህ ደግሞ ሙሉ ግንዛቤ እንዲኖረኝ እመኛለሁ፡፡ ይህ ሲሆን እንደተባለውም በትምህርት ስኬታማ ነኝ ማለት ይቻላል” ሲል ነው የተናገረው፡፡

ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ በማህበረሰቡ አይችሉም የሚለው አመለካከት እንዳለ ሁሉ በራሳቸው አካል ጉዳተኞች የሚስተዋል ችግር እንዳለም ስለመገንዘቡ ይናገራል፡፡ ሁለቱም ከዚህ አስተሳሰብ ሊወጡ እንደሚገባም ነው አስተያየቱን የሰጠው፡፡

አካል ጉዳተኞች እድሉን ካገኙና ከተያዙበት ማህበራዊ ችግር ከተላቀቁ ለራሳቸውና ለሀገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

በሚሰራበት መስሪያ ቤትም በአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት እና ጥበቃ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡ የተሻለ አደረጃጀት ተፈጥሮ አካል ጉዳተኞች የመብቶቻቸው ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ አካል ጉዳተኞችም ቢሆን ከተበታተነ ሁኔታ ወጥተው ከክልል እስከ ወረዳ ማህበር መስርተው እንዲንቀሳቀሱ መደረጉ የራሳቸውን መብት በራሳቸውም ለማስከበር እንደሚረዳቸውም ይመክራል፡፡

በማህበር መሰባሰቡም በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ላይ የወጡ ዓለም አቀፍ መብቶችን፣ ህጎችንና ደንቦችን ለማስረጽ ፋይዳው የጎላ ነው። በህንጻ ግንባታ፣ በጤናም ይሁን በትምህርት ዘርፍ አካል ጉዳተኞች ያሏቸውን መብቶች እንዲገነዘቡ ይረዳል፡፡ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው ራሳቸውን የመቻል አስተሳሰባቸው እንዲጎለብት እና ከጥገኝነት ወጥተው እንዲወጡ በማህበር መሰባሰቡ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

አሸናፊ ትዳር መስርቶ 2 ልጆችን አፍርቷል፡፡ አካል ጉዳትና ትዳር የብዙዎች አካል ጉዳተኞች ፈተና ነው አንተስ የደረሰብህ ተጽእኖ አልነበረም ላልነውም፡

“ችግር ጎልቶ የሚንጸባረቀው ቤተሰብ ላይ ነው፡፡ ትዳር መስርተው የራሳቸውን ህይወት እንዲመሩ የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ይስተዋላል፡፡ አታገቢውም ወይም አታገባትም የሚል አመለካከት በማህበረሰቡ ዘንድ ዛሬም ያልተቀረፈ ችግር ነው፡፡

“ከትዳር በፊት አፍቅሮ ወደ ትዳር ሲመጣ በቤተሰብ ትዳር የሚቋረጥበት ሁኔታ አለ። እንደ እድል ሆኖ ይህ ችግር ግን እኔን አልገጠመኝም፡፡ ይሄ ችግር ወደ እኔ ስላልመጣ በሌላው የለም ማለት እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት” ነው ያለው፡፡

ስር የሰደደውን ችግር ለመቅረፍ በአንድ ጀንበር በሚሰራ ስራ ብቻ አይሆንም፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ይሁኑ መንግስታዊ ድርጅቶች በአካል ጉዳተኞች ግንዛቤ መፍጠር ላይ ይሰራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የሚፈገው ደረጃ ላይ አልተደረሰም፡፡ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚዲያ ሽፋኑና ተደራሽነቱ ገና በመሆኑ ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡