ነጩ ወርቅ

ነጩ ወርቅ

በገነት ደጉ

ሰሊጥ በሰው ልጆች ታሪክ ቀደምት አዝርዕት እንደሆነ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ አዝርዕቱ በኢትዮጵያ የተዋወቀው ከ2 ሺህ እስከ 2 ሺህ 500 መካከል ባለው ዓመታት እንደሆነ ይታመናል፡፡ የሰሊጥ ምርት በግንባር ቀደምትነት ለውጪ ንግድ አቅርቦት ከመዋሉም ባሻገር ኢትዮጵያን ከተለያዩ የጎረቤት ሀገራት እንዲሁም ቀይ ባህርን በመሻገር ከሜዲትራንያን፣ ከመካከለኛው እና ከሩቅ ምስራቅ ሀገራት ጭምር በንግድ የማስተሳሰር ሚና ተጫውቷል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ የግብርና ስነ-ምህዳር ባለቤት መሆኗ በዓለም የልዩ ሰሊጥ ምርት መገኛ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዓመታዊ የሰሊጥ ምርት መጠኗ በአማካኝ 275 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሲሆን የማምረት አቅሟ ደግሞ ከ400 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ሀገራችን በሰሊጥ ምርት መጠን በዓለም በ4ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ደግሞ በ2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ሰሊጥ ለኢትዮጵያ ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታ ካላቸው ቀዳሚ ከሆኑ የግብርና ምርቶች አንዱ ነው። ሰሊጥ ወደ ውጭ ገበያ ተልኮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ሰብል ነው፡፡ እንዲሁም እያደገ የመጣውን የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍላጎት ለማሟላት ለፋብሪካዎችም ዋና ግብአት በመሆን ያገለግላል፡፡

ሰሊጥ በፕሮቲን፣ ቫይታሚን ቢ፣ ማግኒዥየም፣ ካልሲየም፣ ብረት እና መዳብ፣ ፋይበር፣ ፋቲ አሲድ ይዘት እና ኦሌይክ አሲድ በተሰኙ ንጥረ ነገሮች የበለፀገ ሰብል ነው፡፡ በተጨማሪም ሰሊጥ በመዋቢያ እና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪዎች ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ፕሮግራም በሚተገብርባቸው ክልሎች ውስጥ የሰሊጥን ምርት፣ ምርታማነት እና ግብይት ለማሳደግ በርካታ ስልታዊ አሰራሮችን ተግባራዊ አድርጓል።

እኛም ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባስኬቶ ዞን ግብርና መምሪያ የሚመለከታቸውን አካላት በስልክ አነጋግረን ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባስኬቶ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንዳፍራሽ ንጉሴ የባስኬቶ ዞን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ካሉት ሰሊጥ አምራች ዞኖች መካከል አንዱ ሲሆን በልግም መኸርም አምራች አካባቢ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በዞኑ ሰሊጥ የሚዘራው በበልግ ወቅት ብቻ መሆኑን የሚናገሩት የግብርና መምሪያ ኃላፊው አጠቃላይ የበልግ ዕቅዱ ወደ 18 ሺህ 666 ሄክታር ሲሆን 524 ሄክታር የበልግ ስራ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡ ከዚሀም መካከል 5 ሺህ 500 ሄክታር ሰሊጥ ለማምረት ታቅዶ በመስራት 5 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ማሳ መሸፈን ስለመቻሉ ነው የጠቆሙት፡፡

ከዚህም ውስጥ በኩታ ገጠም እና በክላስተር የተሰራው 720 ሄክታር ማሳ መሆኑንና በዚህም 18 ክላስተሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ከማሳ ሽፋን አንፃር አምና ከነበረው ዘንድሮ የተሻለ ሽፋን እንደሆነ አስታውሰው ከምርትም አንፃር የዘንድሮ ዓመት ለየት ያለ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

አጠቃላይ የዞኑ የበልግ ሽፋን ከማሳው ላይ ሲታይ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ከመሆኑም በላይ በዞኑ ያለው የአየር ንብረት ፀባይ ለምርቱ ምቹ እና አስተማማኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አምና ላይ የተገኘው በሄክታር ወደ 5 ነጥብ 5 እንደነበር ያስታወሱት ምክትል አስተዳዳሪው በዘንድሮው ዓመት ወደ 6 ነጥብ 6፣ ከዚያም አልፎ አንዳንድ ማሳዎች ላይ በሄክታር እስከ ሰባት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

ከአጠቃላይ ሽፋን አንፃር ሲታይ ከ35 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ የሚናገሩት የመምሪያው ኃላፊ በዘንድሮ ዓመት ለሰሊጥ ሰብል የተሰጠው ትኩረት ለየት ያለ በመሆኑ በአጨዳ ወቅት ብክነት እንዳያጋጥም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሚቀጥሉት ወራት የሰብሉን ጥበቃ ስርዓት ጤናማ በማድረግ፣ የአጨዳ ስራዎች ላይ ቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው በዞኑ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርቡ አራት ሰብሎች ሰሊጥ፣ ቡና፣ ቦለቄ እና ማሾ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል አንዱ እና ዋነኛው ሰሊጥ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

እንደ ሀገር ሰሊጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ምርት ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም የባስኬቶ ዞን ልዩ ድርሻ ያለው ሲሆን የውጪ ምንዛሪን ከማሳደግ አንፃር ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ ዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርበው ምርት አንፃር በመሰረተ ልማት ዙሪያ ትኩረት የተነፈገው ሲሆን ባሳለፍነው ዓመት የምርት ብክነት በማጋጠሙ ዘንድሮም ተማሳሳይ ችግሮች አሉ ብለዋል፡፡

ከመንገድ አለመኖር ጋር ተያይዞ መኪና መግባት ባለመቻሉ አርሶ አደሩ በጀርባው ተሸክሞ እና በጋማ ከብቶች ጀርባ ጭኖ በማድረሱ ምክንያት የምርት መበላሸትና እንግልት እየገጠማቸው ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የምርት ብክነት እና ለማዕከላዊ ገበያ ሀገር የምታቀርበውን ምርት ባለማድረስ የምንጎዳ ሲሆን የመንገድ ችግርን በጋራ እና በሚመለከተው መስሪያ ቤት በዘላቂነት መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ እና ባስኬቶ ዞን ከፍተኛ የሰሊጥ አምራች አካባቢዎች ሲሆኑ በእነዚህም አካባቢዎችና አጎራባች ዞኖች ላይ እሴት መጨመር ቢቻል መልካም ነው ያሉት የመምሪያው ኃላፊው፣ ይህም ስራ ቢሰራ የአርሶ አደሩ ፍላጎት እና የማሳ ሽፋን እንደሚጨምር ነው ያስረዱት፡፡

ዞኑ ተፈጥሯዊ ምርት ለማምረት እምቅ አቅም ያለው አካባቢ በመሆኑ አምና ላይ 30 ሺህ ኩንታል ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን አስታውሰው ከዚህም በላይ ለማምረት የመሰረተ ልማት ተግዳሮቶች እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው የጠቆሙት፡፡

ይህም ችግር አርሶ አደሩ በስፋት ሰብሉን በማምረት ምርትና ምርታማነትን እንዳያሳድግ ተግዳሮት እየሆነባቸው መሆኑን አንስተው ችግሩ ቀላል ተደርጎ ባይታይና አርሶ አደሩ ጓሮ ድረስ መኪና ገብቶ መጫን ቢችል ከዚህም በላይ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል አስረድተዋል። በዘንድሮ ዓመት ያለው የሰሊጥ ማሳ ሽፋን እጅግ ለየት ያለ እና አበረታች ነው ያሉት የመምሪያ ኃላፊው ሰብሉ ለማእከላዊ ገበያ የሚቀርብ እና ሀገርም እንደ ሀገር ብዙ የምትጠብቀው ምርት በመሆኑ ለአካባቢው መሰረተ ልማት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል መልዕክታቸው ነው።