በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል‎

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል

‎በመርሃ ግብሩ የዞን ደጋፊ አመራሮች፣ የወረዳው አመራሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የቀበሌው ህብረተሰብ በንቃት ተሳትፈዋል።

‎በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሐቴ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ጥበቃን ከማጠናከር ባሻገር ለትውልድ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ለማስቀመጥ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

‎በዚህ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 567 ሺህ 721 ችግኞች እንደሚተከሉ ገልፀው ይህም የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሀብትን በዘላቂነት ለመጠበቅ እና ለቀጣይ ትውልድ አረንጓዴ አካባቢ ለማስተላለፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሐቴ ገልፀዋል።

‎በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ አካላት የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ በመንከባከብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ግቦችን ለማሳካት በትብብር ሊስሩ እንደሚገባ አቶ ታደለ ሐቴ አሳስበዋል።

‎የዳሰነች ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም አይመላ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ታልሞ በንቅናቄ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

‎በቀጣይም በመትከል ሥራው ብቻ ሳይወሰን ችግኞቹን በአግባቡ በመንከባከብ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራ ሀላፊው አመላክተዋል።

‎ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን