“አካል ጉዳተኛ መሆን ምንም ማለት አይደለም፤ ከሆነ በኋላ ዋናው አምኖ መቀበል ነው” –  አቶ ፈቀደ ባደታ

በጋዜጣው ሪፖርተር

የዛሬው የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን “በሰዓቱ ቀላሉ ነገር ከባድ ነው፤ ነገር ግን ካለፈ በኋላ እንደ ቀልድ እናወረዋለን” በማለት ነበር ሀሳባቸውን መነሻ ያደረጉት፡፡

ቤተሰብ ተስፋ ቆርጦ “ቢማር ምን ይጠቅማል” ተብለው ከቤት አይወጡም ነበር፡፡ እንግዳ  ሲመጣ ይደብቋቸው ነበር፡፡ በእኛ ሀጢአት ነው ልጃችን እንዲህ የሆነው ብለው በፈጣሪ ይማረሩ ነበር። በዚህ የተነሳ ከልጆች ጋር አይቀላቅሏቸውም፡፡ እነኚህንና መሰል የተዛቡ አስተሳሰቦችን አልፈው ዛሬ ላይ ያለፉበትን መንገድ እንደ ተረት ተረት አውግተውናል፡፡ 

አቶ ፈቀደ ባደታ ይባላሉ፡፡ የጉራጌ ዞን አካል ጉዳተኞች ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት በቀድሞ ስሙ እነሞርና ኤነር÷ በአሁኑ አጠራር ደግሞ እኖር ወረዳ  አጫወደ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው፡፡ 

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በጋዛንቻ ንጋት ጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በቸሀ ጃቱ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲሆን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በጉንቸሬ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡

የአካል ጉዳት የገጠማቸው÷ በልጅነታቸው ማንኛውም ልጅ እንደሚታመመው ድንገት ታመው ነበር፡፡ ቤተሰብም ወደ ህክምና ወስዷቸው÷ በተወጉት መርፌ ምክንያት ደም ስራቸው ተነክቶ ሁለቱም እግራቸው ሽባ እንደሆነ ቤተስብ የነገራቸውን በማስታወስ ገልፀውልናል፡፡ 

ቤተሰብ በሰዓቱ ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት ቢወስዷቸውም ምንም ለውጥ አላመጡም፡፡ “የህክምና ስህተት ነው፤ ምንም መፍትሄ የለውም” እንደተባሉ ያወሳሉ፡፡  

እስከ 4 ዓመት ዕድሜያቸው በእግራቸው ይራመዱ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ በእንፉቅቅ ለመሄድ ተገደዱ፡፡

“ሰፈራችን ጭልም ያለ ገጠር አልነበረም። በአቅራቢያችን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡  ከቤተሰቦቼ ጋር መምህራን ይግባቡ ስለነበር አልፎ አልፎ ቤታችን ይመጣሉ፡፡ አባቴ ግብርናውንም ንግዱንም ይሠራ ነበር፡፡

“አንድ ቀን ርዕሰ መምህሩ አባቴን እንዲህ አለው÷ ‘ይህ ልጅ በንግዱም፤ በእርሻውም  ውጤታማ አይሆንም፡፡ አካሉን እንደምታየው ነው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሲማር ብቻ ነው፡፡ እንደ ምንም ብለህ ብታስተምረው ይሻላል’ ብሎ ለአባቴ ግንዛቤ በማስጨበጡ ትምህርት ቤት እንድገባ ሰበብ ሆነኝ፡፡” ሲሉ የትምህርት ዕድል እንዴት እንዳገኙ አጫውተውናል፡፡

ትምህርታቸውንም እስከ 3ኛ ክፍል በእንብርክክ እየሄዱ ነበር የተማሩት፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ቤተሰቦቻቸው መረጃ አግኝተው አዲስ አበባ መናገሻ አካባቢ የሚገኝ ቸሻየር የሚባል ድርጅት ውስጥ ህክምና አግኝተው የእግር ድጋፍ ተደርጎላቸው መራመድ ችለዋል፡፡ የእግር ድጋፍ ካገኙ በኋላ ተንቀሳቅሰው ቤተሰብ ማገዝ ሲጀምሩ አመለካከቱ እንደተቀረፈም አንስተዋል፡-

“የትምህርት ህይወቴ ላይ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፌያለሁ፡፡ በተለይ በአቅራቢያችን  ትምህርት ቤት አለመኖሩ ትልቅ ችግር ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ግን ችግሩን እንድወጣ ብዙ ጥረት ያደርጉልኝ ነበር፡፡ የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ ችግሩን ተቋቁሜ አልፌያለሁ።” ብለዋል፡፡ 

አቶ ፈቀደ ጎበዝ ተማሪ ቢሆኑም ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ውጤት አልመጣላቸውም ነበር። ውጤታቸው ዲፕሎማ ለመማር የሚያስችል ቢሆንም በወቅቱ መማር አልቻሉም፡፡ ዲፕሎማ ለመማር ሙሉ ጤነኛ የሆነ ተብሎ ማስታወቂያ ይወጣ ስለነበር የትምህርት ዕድል አላገኙም፡፡

ጎበዝ ተማሪ ስለነበሩ የተለያዩ ሥራዎች ላይ ይሳተፉ ነበር፡፡ በነቃ ተሳትፏቸው የወረዳው አመራሮች ያውቋቸው ስለነበር ማስታወቂያ ሲወጣ ሥራ አስቀጠሯቸው፡፡ ማዘጋጃ ቤት በኮንትራት መደብ አስተዳደር እና ፋይናንስ ፕርሶኔል ፀሐፊ ሆነው መሥራት ጀመሩ፡፡

የተወሰነ ጊዜ ከሠሩ በኋላ ብቃታቸውን አይተው በቋሚነት ቀጠሯቸው፡፡ እየሠሩ ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርስቲ የግል ኮሌጅ የትምህርት ዕድል አገኙ፡፡ በዲፕሎማ መርሃ-ግብር በአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል በርቀት ለ 3 ዓመታት ተከታትለው መመረቅ ችለዋል፡፡ ድጋሚ እዚያው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ድግሪያቸውን በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተምረው አጠናቅቀዋል፡፡

በኮንትራት የተጀመረው የሥራ ልምድ አድጎ በኃላፊነት ደረጃ አቅማቸውን አጎልብተው የቄራ ሀላፊ የቦታ አስተዳደር ሆነው በብቃት አገልግለዋል፡፡ በየጊዜው ራሳቸውን እያበቁና  ተወዳድረው እያለፉ የተለያዩ መደቦች ላይ ሠርተዋል፡፡ ከዚያም በትዳር ምክንያት ወደ ደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ወልቂጤ ቅርንጫፍ  ተዘዋውረው  የልማት ዕቅድ ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል፡፡

መኖሪያ ቤታቸው ከሥራ ቦታቸው ትንሽ ርቀት ስለነበረው ወደ ሚቀርባቸው የዞን ፋይናንስ ተቀይረው የሰው ሀብት አስተዳደር ውስጥ አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ፕሮጀክት ላይ ማስታወቂያ ወጥቶ ተወዳድረው አልፈዋል፡፡ ከሣምንት በኋላ ሥራ እንደሚጀምሩ ገልፀውልናል፡፡

“ሥራ ከተቀጠርኩ በኋላ የሥራ ባልደረቦቼ ለኔ በማዘን ይመስለኛል ‘በየቀኑ ለምን ትመላለሳለህ? ደመወዝ ሲደርስ ብቻ ለምን አትመጣም’ ይሉኝ ነበር፡፡  እኔ ግን  ደመወዙን ብቻ ሳይሆን ሥራውንም ጭምር እፈልገዋለሁ፡፡ ከማንም በላይ መሥራት እችላለሁ፤ እናንተ አትሳቀቁ ይሏቸው እንደነበር  አቶ ፈቀደ በትዝብት ስሜት ሆነው ገልፀውልናል፡፡

“የሥራ ብቃቴን ካዩ በኋላ ግን 3 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከምሠራው ሥራ ውጭ  ከአንድም ሁለት ሥራ ደርቤ እንድሠራ በውክልና ይሰጡኝ ነበር፡፡ የሚገርመው ከተቀጠርኩ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የማኔጅመንት አባል ነኝ፡፡ ብዙን ጊዜ በአስተባባሪነት ቦታዎች ላይ ነው የሠራሁት፡፡

“ብዙ የኮሚቴ ሥራዎች ላይ እሳተፋለሁ። የተሰጠኝን ሥራ በአግባቡ ልቅም አድርጌ ነው የምሠራው፡፡ በሥራ አፈፃፀም ውጤቴ አንድም ቀን ከ90 በታች ሆኜ አላውቅም፡፡ የሥራ ባልደረቦቼ ምንም ነገር ይሠራል ብለው ስለማያስቡ ሥራዬ ላይ ውጤታማ ሆኜ ሲያዩ በጣም ይገረሙ ነበር። ‘ቤት ቁጭ ይበል ስንል ለዚህ በቃ፡፡’ ይሉኛል” በማለት አቶ ፈቀደ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡

“ወደ ትዳር ዓለም ለመግባት ብዙ መሰናክሎች ገጥመውኛል፡፡ ባለቤቴን ‘ሌላ ወንድ ጠፍቶ ነው እንዴ እሱን የምታገቢው’ የሚሉ እና ከተሳሳተ አመለካከት የመነጩ አስተያቶች ነበሩ፡፡ የማህበረሰቡ አመለካከት ፈታኝ ነበር፡፡

“በፍቅር ተገናኝተን በቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ትዳሬን እስከ ማጣት ደርሻለሁ” ያሉት አቶ ፈቀደ የሁሉም ሰው አመለካካት አንድ አይደለም በሚል ተስፋ ሳይቆርጡ ድጋሚ አግብተው አሁን ላይ ከባለቤታቸው ጋር 3 ልጆችን አፍርተው በፍቅር አብረው እየኖሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡  

“አሁን ላይ በተሠሩ ሥራዎች ለውጦች መጡ እንጂ የአካል ጉዳታችን የፈጣሪ ቁጣ ነው ብለው የሚደመድሙ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ይህን ለመቀየር ገና ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡

“እኔ ግን ብዙም አይሰማኝም፤ ምክንያቱም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የተዘጋጁ ጽሁፎችን እና በሚዲያ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን  ስለምከታተል ግንዛቤው አለኝ:: ስለዚህ በስነ ልቦና ብዙም አልተጎዳሁም፡፡ ነገር ግን ግንዛቤው የሌላቸው በስነ-ልቦና በብዙ መልኩ ሲጎዱ ይስተዋላል” ብለዋል፡፡

“አካል ጉዳተኝነት ይቆማል ተብሎ አይታሰብም፤ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል። እንደ ዞን  ማህበሩ ላይ እንንቀሳቀሳለን፡፡ ግን ብዙ የሚጎድሉ ነገሮች አሉ፡፡ እንዳጋጣሚ  አካል ጉዳተኝነት ቢከሰት ምን ይጠቅማል ምን ያገለግላል ብለው ተስፋ የመቁረጥ ነገር ቤተሰብ ላይ ይንፀባረቃል፡፡ አመለካከት እንዲቀየር በስፋት መስራት ያስፈልጋል፡፡

“የሚረዳ አካል ቢኖር አመለካከት ላይ ወደፊት ማህበረሰቡን አንቅቶ አካል ጉዳተኛ ልጅ ካለው በአግባቡ እንዲያስተምር ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አሁንም ድረስ እታች ቀበሌ ወርደን ብንመለከት ልጆቻቸውን የሚደብቁ፤ እንደ ልጅ የማይቆጠሩ ቤተሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ያስፈልጋል፡፡

“አብዛኛውን ጊዜ አካል ጉዳተኞች ቁጡ ናቸው ተብሎ ይፈረጃል፡፡ ካለባቸው ስነ-ልቦና ችግር የተነሳ ቁጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቁጡ ከሆኑ አካል ጉዳተኝነታቸውን አምነው አልተቀበሉም ማለት ነው፡፡”

“አካል ጉዳተኝነት ቢከሰት ምንም  ማለት አይደለም፡፡ አዕምሮ እስካለ ድረስ እንደማንኛውም ዜጋ ሠርቶ መኖር ይቻላል፡፡ ዋናው የደረሰብንን ነገር አምኖ መቀበል ነው፡፡ ተስፋ የለኝም ምንም ማድረግ አልችልም ብሎ የሰው እጅ ከማየት እንዴት መሥራት  እንዳለባቸው  ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

“የተረጂነት አስተሳሰብ መወገድ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ታክሲ ላይ ይገጥመኛል፡፡ ሒሳብ ክፈሉ ሲባሉ አካል ጉዳተኛ ነኝ አልከፍልም የሚሉ አሉ። ይህ ተግባር ተገቢ አይደለም ተረጂነትን ማሳደግ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አስተሳሰቦችን የመቅረፍ ዕቅድ አለኝ፡፡” በማለት ስለ ሁኔታው በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

“እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአካል ድጋፍ ማምረቻ የለም፡፡ ‘አርባ ምንጭ ተሀድሶ ማዕከል’ ሄደን ነው የአካል ድጋፍ የምናገኘው፡፡ ስለዚህ ለአካል ጉዳተኞች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ማምረቻ እንዲቋቋም እንቅስቃሴ የማድረግ ዕቅድ አለኝ፡፡” ሲሉ የወደፊት ዕቅዳቸውን ገልፀውልናል። 

“አካል ጉዳት ማለት ክስተት ነው፡፡ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ ክስተት በማንኛውም ሰዓት ሊከሰት ይችላል፡፡ አካል ጉዳተኛ መሆናቸውን ተቀብለው የተለያዩ ዘመን ያመጣቸው መተኪያዎችን ተጠቅመው ከማንኛውም ዜጋ ባላነሰ ራስን ለመቻል ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 

“ከምንም በላይ ግን ቅን አሳቢ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ማንኛውንም ነገር በተቃራኒው ካየነው ጥሩ አይደለም፡፡ ሰው የሚኖረውን ኑሮ መኖር እችላለሁ የሚል አስተሳሰብ ውስጣቸው ሊኖር ይገባል፡፡ 

“የሚያጋጥማቸውንም ችግር ከሰው ጋር መነጋገር አለባቸው፡፡ ውይይት ከተደረገ የማይፈታ ችግር የለም፡፡ በርካታ አካል ጉዳተኞች ተአምር እየሠሩ ነው፡፡ የኛ ጉዳት ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ልዩነቱ አልችልም፤ እችላለሁ የሚል ስነልቦና መያዝ ነው፡፡ ስለዚህ  በተቻለ መጠን አካል ጉዳተኞች እችላለሁ የሚል ስነልቦና መያዝ እንዳለባቸው ማስገነዘብ እፈልጋለሁ፡፡” ሲሉ ለአካል ጉዳተኞች ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በመጨረሻም በጎ የዋሉላቸውን አካለት እንደሚከተለው አመስግነዋል፡-

“ማመሥገን የምፈልገው ቤተሰቦቼን ነው፡፡ እናት እና አባቴ ተቸግረው እንድማር ባያደርጉኝ ኖሮ ምን አልባት ዛሬ የደረስኩበት የአስተሳሰብ ደረጃ አልደርስም ነበር፡፡ እንዲሁም እህት ወንድሞቼን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ 

“በተለያየ የክፍል ደረጃ ያስተማሩኝን መምህራን÷ ሁልጊዜ ጠንክሬ እንድማር ይመክሩኝ ስለ ነበር አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ወደ ሥራ ዓለም ከገባሁ በኋላም የሀሳብ ድጋፍ የሚያደርጉልኝ የሥራ ባልደረቦቼን አመሰግናለሁ፡፡ አንዳንዴ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሚጎዱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በዛው ልክ ደግሞ ከዓላማዬ እንዳልወድቅ ድጋፍ ያደረጉልኝ ጓደኞቼን ማመስገን እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡