በደረጀ ጥላሁን
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ዶክተር ኃይሉ ታምራት ይባላሉ፡፡ ከእንስሳት ጤና ባለሞያነት እስከ ኮሌጅ መምህርነት እንዲሁም በግብርና ጽ/ቤት በባለሞያነትና ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በዶሮ እርባታ በመሰማራትም ለአካባቢያቸው እንደ አርአያ የሚታዩ ናቸው፡፡ አሁን ላይ የቡኢ ግብርና ግብአትና አገልግሎት ማእከል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በሰሩትና አሁን በሚሰሩት ሥራና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ
ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ኃይሉ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፦ በትውውቅ እንጀምር
ዶክተር ኃይሉ፦ ዶክተር ኃይሉ ታምራት እባላለሁ፡፡ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሶዶ ወረዳ በኬ ቢሳንጅራ ቀበሌ ነው የተወለድኩት፡፡ አድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ አዲስ አበባ ከአባቴ ዘመዶች ጋ ሆኜ ተማርኩኝ፡፡ 5ኛ ክፍል ስደርስ አባቴን በሞት በማጣቴ እስከ 12ኛ ክፍል የቀን ሥራ እየሰራሁ ነበር የተማርኩት፡፡ 12ኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በእንስሳት ሕክምና ትምህርት በዶክተሬት ተመርቄያለሁ፡፡
ንጋት፦ የሥራ አጀማመርዎ እንዴት ነበር?
ዶክተር ኃይሉ፦ ሥራ የጀመርኩት በመንግስት መስሪያ ቤት ሲሆን ዳራማሎ ወረዳ የእንስሳት ጤና ባለሞያ ሆኜ ነበር። ከዚያ በኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ ለአንድ አመት በመምህርነት አገልግያለሁ፡፡ ወደ ጉራጌ ዞን ከመጣሁ በኋላ ቡኢ ላይ የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳት ሐኪም እና የጤና ቡድን መሪ በመሆን አገልግያለሁ፡፡ እንዲሁም የሶዶ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆንም ለሁለት አመታት ሰርቻለሁ።
እንደ እንስሳት ሀኪም በተለይ አርሶ አደሩ በእንስሳት ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት አደርግ ነበር፡፡ በዚህ መነሻ ዶሮ እርባታ ላይ በመሰማራት አርሶ አደሮች ዶሮን እንዴት ማርባት እንዳለባቸው ከማስተማር ባሻገር ለዶሮ እርባታ የሚረዱ የማርቢያ ቁሳቁስና መድሐኒት በማቅረብ በግል እሰራ ነበር። እነዚህ በመንግስትም ሆነ በግል ደረጃ የሰራኋቸው ሥራዎች ብዙ ልምድ እንዳካብት ረድተውኛል፡፡
ንጋት፦ የቡኢ ግብርና ግብአትና አገልግሎት ማእከል ሥራ እንዴት ጀመሩ?
ዶክተር ኃይሉ፦ የአርሶ አደሩን የግብአት ችግር በመቅረፍ እንደ ሀገር ግብርናውን ለማዘመን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት እየሰሩ መሆኑን መረጃ ደረሰኝ። ሁሉም ዓይነት የግብርና ግብአት በአንድ ማእከል ቢቀርብ አርሶ አደሩ ምርታማቱን ማሳደግ ይችላል፡፡ እንዲሁም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ለሱ የሚሆን ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር ግብአት ትልቁ ችግር ነበር፡፡ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል አሰራር ተቋሙ እንደሚከተል መረጃ አገኘሁ፡፡ በዚህ መሰረት ተቋሙ ያዘጋጀውን ፈተና ተወዳድሬ በማለፍ ወደ ሥራው መግባት ችያለሁ፡፡
ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ጋር የአርሶ አደሩን ችግር ለመቅረፍ ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ ይህ ሥራ ቢዝነስ ሳይሆን ማህበረሰብ ተኮር እንደመሆኑ የአርሶ አደሩን ችግር ለመፍታት ጥራት ያለው ግብአትን በተመጣጣኝ ዋጋና በሚፈለገው ጊዜና መጠን እያቀረብን ነበር፡፡ በምናቀርበው ግብአት አርሶ አደሮች እርካታ ያገኙበት ሲሆን ለወደፊቱ ቀበሌ ድረስ እንዲሰፋፋም ይፈልጋሉ፡፡
ንጋት፦ የማእከሉን አገልግሎት ለማዘመን ምን እየተሰራ ነው?
ዶክተር ኃይሉ፦ አገልግሎቱን ዘመናዊ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ እየሰራን ነው፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ አርሶ አደር በተቻለ አቅም ቴክኖሎጂውን መጠቀም እንዲችል ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አሁን ላይ መረጃ እንዲያገኝ ከመጋዘን ጀምሮ ሽያጭ ክፍል /ማሳያ ክፍል/ ድረስ ዲጂታል አድርገናል፡፡
ከዚህ አንፃር አርሶ አደሩ ግብአት ሲገዛ የግብአቱ ምንነት እንዲሁም የምናቀርባቸው አጠቃላይ መድሐኒቶች አጠቃቀሙን እንዲያውቅ ባለሞያዎቻችን ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ አርሶ አደሩ ግብአት ሲገዛ ስሙና ስልኩ ይመዘገባል፡፡ አጠቃላይ የወሰዳቸው መድሐኒቶች ኮምፒውተር ላይ ይመዘገባሉ። በዚህ መነሻ በእጅ ስልኩ ላይ መልእክት እንዲደርሰው እናደርጋለን፡፡
ዲጅታል በማድረጋችን አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ግብአት መኖሩን ለማረጋገጥ ይጠቀምበታል፡፡ በሽታ ሲገባና እንዲሁም የተሻለ አቅርቦት ሲኖር በስልክ መልእክት ይገለፃል፡፡ ይህንን ሲስተም መዘርጋታችን አርሶ አደሩን ከመጥቀም ባሻገር ሁሉም ባለሞያዎች በሲስተም ስለሚሰሩ ለማእከሉ ሥራ እገዛ እያደረገ ነው፡፡
ንጋት፦ በአርሶ አደሩ ዘንድ ቴክኖሎጂውን የመጠቀም ሁኔታ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ኃይሉ፦ ሥራችንን ድጂታላይዝድ ለማድረግ የሰራነው ሥራ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ እስኪሆን እንቀጥላለን፡፡ በአጠቃቀሙ ላይ አርሶ አደሩ ያለውን ክፍተት ለመሙላትም ጥረት እናደርጋለን፡፡ ሥራው በሂደት እየተለመደ የሚመጣ ከመሆኑ አንፃር ሁሌም በተግባር እየሰራን እንሄዳለን፡፡
በአንድ ወቅት ማዳበሪያ እናሰራጭ ነበር። ነገር ግን አርሶ አደሩ ማዳበሪያ ማግኘት ስላለበት ሁሉንም በማንዋል ማዳረስ ሊያሳስት ይችላል፡፡ ስለዚህ ድጂታል እናድርግ በማለት ልጄ ኮዲንግ አስተምረው ስለነበር ይህን ችግር የሚፈታ አፕልኬሽን ሰራ፡፡ ከዚያም ሶፍት ዌር አልምቶ አጠቃላይ ቢዝነሱን ዲጅታል በሆነ መልክ መምራት አስችሎናል፡፡
ወደፊትም በዚህ በመቀጠል እያንዳንዱ ያሉንን ምርቶች ለአርሶ አደሩ በስልኩ አማካይነት መረጃና የምክር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በመልእክት አሁንም እየሰራን ቢሆንም ሌሎች መረጃዎችን በዚሁ መንገድ ማግኘት ላልቻሉ እናዳርሳለን።
ወደፊት በማእከላችን ከሚገኙት ምርቶች መርጠው መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ ሌላው ዓላማ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ያለበት ክላስተር ተመርጦ በዚህ ቀን ይህ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይገለፃል፡፡ ከሞባይል መልእክት በተጨማሪ ኦን ላይን አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂውን በተጠቀመው ልክ አገልግሎት እንዲያገኝ እንሰራለን፡፡ ከምክር አገልግሎት በተጨማሪ ክፍያም በዲጅታል እንዲሆን እየተመቻቸ ነው፡፡
ንጋት፦ የተጠቃሚውን እርካታ እንዴት ነው የምታውቁት?
ዶክተር ኃይሉ፦ በማእከሉ የምናቀርበውን ግብአት አርሶ አደሩ መቼ መጠቀም እንዳለበት እናስረዳለን፡፡ ለዚህም የእንስሳት ጤና ባለሞያዎች፣ የሰብል ባሞያዎች እና ሌሎችም በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በአገልግሎታችን አርሶ አደሮች መርካት አለመርካታቸውን የምናውቀው ግብረ መልስ እንዲሰጡን በማድረግ ነው፡፡ ለዚህም የተለያዩ መንገዶችን እንጠቀማለን። ቼክ ሊስት በማዘጋጀት ግብረ መልስ እንሰበስባለን፡፡ ለምናቀርበው ግብአት ጥራት እና ውጤታማነቱን እንጠይቃለን፡፡ በቃልም እንዲሁ እንጠይቃለን፡፡ ምላሻቸውን መሠረት በማድረግም የሚስተካከል ነገር ካለ የማስተካከል ሥራ እንሰራለን፡፡
ንጋት፦ ሥራውን በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ምን ታስቧል?
ዶክተር ኃይሉ፦ የግብርና ግብአት ለአርሶ አደሩ እያስገኘ ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡ የግብአት ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ለሌሎች አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን አሁን ካለን ተጨማሪ ማእከል ከፍተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ሥራውን ከዚህም በላይ ለማስፋት ደግሞ መስሪያ ቦታ እንዲሰጠን ሰባት ማእከላትን መርጠናል። ይህም አርሶ አደሩ አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኝ የሚረዳው በመሆኑ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ ጽፈን አስገብተናል፡፡ ጥሩ ምላሽ እናገኛለን ብለንም እንጠብቃለን፡፡
ንጋት፦ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ኃይሉ፦ ይህን ማእከል ያቋቋሙት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ነው፡፡ ተቋሙ ያስቀመጠውን መስፈርት በሟሟላት ሥራ ስንጀምር የቢሮ እቃዎችን አሟልተው ለአንድ አመት ያህል ለሠራተኞች ደሞዝ ከፍለው ነው ሥራ ያስጀመሩን፡፡ ተቋሙ በፋይናንስ ከሚያደርግልን ድጋፍ በተጨማሪ በአቅም ግንባታና በአሰራር ዙሪያ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል የድጋፍና ክትትል ሥራ ይሰራሉ። ባጠቃላይ የግብአት አቅርቦት ሥራውን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡
ንጋት፦ ህገ ወጥ የግብአት አቅርቦትን ለመግታት በናንተ በኩል ምን እየተሰራ ነው?
ዶክተር ኃይሉ፦ አሁን ላይ በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡ ግብአቶች በየገበያው የመቅረብ ሁኔታ አለ፡፡ ይህ አደጋ አለው፡፡ ለዚህ በመንግስትና በሚመለከታቸው አካላት ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡
ህጋዊ በሆኑ የግብአት አቅራቢዎች በኩል የሚቀርቡ ግብአቶች ታማኝነታቸው የተረጋገጠ በመሆኑ በአካባቢያችን እንዲሁም በአጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ይጠቀማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባለማወቅ አመጣጡ የማይታወቅና በሚመለከተው አካል ያልተረጋገጠ ግብአት የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ለችግር የሚጋለጡ በመሆናቸው ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ ይህን ለመቋቋም በእኛ በኩል ትክክለኛ ግብአት የቱ እንደሆነ እያስተማርን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብቻ በቂ ባመሆኑ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡
ንጋት፦ የማእከሉ ካፒታል ምን ያህል ደርሷል?
ዶክተር ኃይሉ፦ ሥራውን ስንጀምር የነበረን ካፒታል አነስተኛ ነው፡፡ አሁን ማእከል ሆኖ እየተጠቀምንበት ያለው ቤት መኖሪያችን ነበር፡፡ ለመኖሪያ የሚሆን ቤት ተከራይተን ነው የወጣነው፡፡ ሥራችን ህብረተሰብ ተኮር ስለሆነ ትርፍ ላይ አናተኩርም፡፡ ለወደፊቱ ይህ አገልግሎት ወደ ሎካል /ተቋም/ ተቀይሮ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ ለመፍጠር ነው፡፡ አሁንም በትንሽ ትርፍ የአርሶ አደሩ አቅም እስኪገነባ እያገለገልን ነው፡፡
እኔ የማየው በእስካሁኑ የሥራ ቆይታዬ ትልቁ ካፒታል ታማኝነትን ማትረፍ ነው፡፡ ይህም ከገንዘብ በላይ ነው፡፡ ከሥራችን ጋር በተያያዘ አንዳንድ አስመጪዎች ጋር ባለን ጥሩ የሥራ ግንኙነትና መተማመንን በመፍጠር ሰርተን እንድንመልስ በብድር ግብአት ይሰጡናል፡፡ እኛም ሸጠን እንመልሳለን። ስለዚህ ካፒታል ላይ ብዙም አናተኩርም። ለወደፊቱም ቢሆን ከባንክ ጋር በመነጋገር ብድር በመውሰድ ሥራውን ይበልጥ አስፋፍተን እንሰራለን፡፡
ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ እድሉን ልስጦት
ዶክተር ኃይሉ፦ የግብአት ሥራ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በተለይ የአግሮ ኬሚካል ሥራው ካልተጠነቀቅን ለሰው ጤና አደገኛ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ከአጠቃቀም እና ከአያያዝ ችግር አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ አሳሳቢው ጉዳይ በህገ ወጥ መልኩ የሚገቡ የአግሮ ኬሚካልና ሌሎች መድሐኒቶች በህብረተሰቡ ላይ ከባድ ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ህገ ወጥ ግብአትና መድሐኒት ንግድ በየገበያው መታየቱ ነው፡፡ መንግስት መመሪያ ያወጣል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ኬሚካል ከሸቀጥ ጋር ሲሸጥ ይስተዋላል፡፡ አርሶ አደሩ ባለማወቅ ሊገዛው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በዚህ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት መስራት ይገባል እላለሁ፡፡
ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ኃይሉ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
More Stories
“እኔ የደረስኩበትን ደረጃ ለእናቴ ብሰጣት ደስ ባለኝ ነበር” – መምህር ተሾመ አንሼቦ
“የሰው ፍቅርን አትርፌበታለሁ” – መምህር ሰለሞን ወርቅነህ
“ችግር ተስፋ ቢስ ሊያደርገኝ ሞከረ፤ እድል ግን አልሰጠሁትም” – ወጣት መውደድ ታደሰ