“የሰው ፍቅርን አትርፌበታለሁ” – መምህር ሰለሞን ወርቅነህ
በደረሰ አስፋው
የመምህርነት ሙያ የነብሳቸው ጥሪ ነው፡፡ የማስተማር ወይም የመምህርነትን ሙያ ከምንም ጋር ሊያወዳድሩት እንደማይፈልጉና ቅድሚያ የሚሰጡት የሙያ ዘርፍ እንደሆነ ነው የተናገሩት። “አንዳች ለውጥ በሕይወቴ ተከስቶ ማስተማርህን ተው ቢሉኝ የምችል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ማስተማር በደም ስሬ የተዋሃደ ነገር ነው” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ከአንድ ሰዓት የዘለለ ቆይታ አደረግን። መልካም በሆነው የማስተማር ህይወታቸው በሀዋሳና አካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ስለመሆናቸው ታዘብኩ፡፡ “ሶል ኬሚስትሪ” የእውነተኛ ስማቸው እስከሚመስል ብዙዎች በዚህ ስም ይጠሯቸዋል፡፡ እሳቸውም የተስማሙበት ይመስላል በዚሁ ስም አቤት ብለው እጅ ነስተው ከሰዎች ጋር ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡
ባለታሪካችንን ከቅርብና ከሩቅ የሚጠራቸው ሰው ስፍር ቁጥር የለውም፤ እኔም በዚህ ጉዳይ መገረሜ አልቀረም፡፡ የነበረንን ቆይታ በጣም ነው የወደድኩት፡፡ በርካታ ቁም ነገሮችንም አግኝቼበታለሁ፡፡ በ41 ዓመታት የመምህርነት ቆይታቸው ገንዘብ ከማፍራት በዘለለ የሰውን ፍቅር ያተረፉበት በመሆኑ በመምህርነታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ነው የገለጹልኝ፡፡
ባለታሪካችን ገና ተማሪ እያሉ አርአያ የሆኑ መምህራኖቻቸውን በመመልከት መምህር የመሆን ውጥን ነበራቸው፡፡ መምህራኑ በአለባበሳቸው ጥንቁቅ፣ የሚያስተምሩትን ትምህርት ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ተማሪን በዕውቀት ለማነጽ የሚያደርጉት ትጋት ይማርካቸው ነበር፡፡ በተለይ ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል ያስተማሯቸው የሳይንስና ሒሳብ መምህር የሳይንስ ትምህርትን (ኬሚስትሪን) እንዲወዱት አደረጋቸው፡፡ “እኔ ሳድግ እንደእነሱ ጎበዝ መምህር እሆናለሁ ብዬ ራሴን በትምህርት አዘጋጅ ነበር” ነው ያሉት፡፡ ይህም 41 ዓመታትን ለዘለቀው የመምህርነት ሙያ መነሻ እንደሆናቸውም ነው የተናገሩት፡፡
መምህር ሰለሞን ወርቅነህ ባለትዳርና የ3 ሴት ልጆች አባት እና የሁለት ልጆች አያት ናቸው፡፡ የተወለዱት በቀድሞው ሀረርጌ ክፍለ ሀገር በጣፋጭ ብርቱካኗ በምትታወቀው ኤረርጎታ ተብላ በምትጠራው መንደር ነው፡፡ ወላጅ አባታቸው ወታደር በመሆናቸው አብዛኛው ኑሯቸው በወታደር ካምፕ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ቤት ተከራይተው ከማህበረሰቡ ጋር ይኖሩ ነበር፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል ቆጥረው፣ ቁጥርን እና አራቱንም የሂሳብ ስሌቶችን ለይተው፣ ማንበብና መጻፍ ሲችሉ በኤረርጎታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት ከ1ኛ እስከ 2ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ሲማሩ በትምህርት ቤቱ ያስተማሯቸው መምህራኖች በሳቸው ላይ ያሳደሩባቸውን በጎ ተጽእኖ እስከዛሬም አልዘነጉትም፡፡ አርአያነታቸው በሳቸው ልብ ውስጥ እስከ ዛሬም ታትሞ እንደዘለቀ ነው፡፡
ይሁን እንጂ፤ መምህር ሰለሞን አባታቸው ወታደር በመሆናቸው በአንድ ቦታ ተረጋግተው የመማር ዕድል አልነበራቸውም፡፡ ወላጅ አባታቸው ጦርነትና ግጭት አለበት በተባለ ቦታ ሁሉ በመሄድ ወታደራዊ ግዳጃቸውን ያከናውናሉ፡፡ በዚያው በርካታ ስፍራዎችን ለማየትና ከብዙ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅም ዕድል የፈጠረላቸው ነበር፡፡
ወላጅ አባታቸው ከሀረርጌ ወደ መቂ ከተማ ተዘዋውረው ሲመጡ እሳቸውም በመቂ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ3ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል። መቂ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ወደ በቀድሞ ዝዋይ (ባቱ) 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤት ተዘዋውረው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ በዝዋይ (ባቱ) በነበራቸው ቆይታ ግን የፖለቲካ ዓላማን አንግበው በሚንቀሳቀሱ ተማሪዎች በተፈጠረ ግጭት ያልጠበቁት ነገር ገጥሟቸው ለ3 ቀናት ለእስር ተዳረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለአንድ አመት ዘግይተው ነው የወሰዱት፡፡
በዚህም የተነሳ የዩኒቨርስቲ የማለፊያው ነጥብ ቀድሞ ከነበረው ከ2 ነጥብ 4 ወደ 2 ነጥብ 8 ከፍ በማለቱ እሳቸው ግን 2 ነጥብ 6 ብቻ በማምጣታቸው ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት አልቻሉም፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ገብተው በዲፕሎማ በኬሚስትሪ መምህርነት በከፍተኛ ነጥብ ተመረቁ፡፡ መምህር ሰለሞን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በክረምት የትምህርት መርሀ ግብር በኬሚስትሪ ተመርቀዋል፡፡
ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከተመረቁ በኋላ በወቅቱ ትምህርት ሚኒስቴር በእጣ ምደባ የሚሰጥበት በመሆኑ ጎጃም ክፍለ ሀገር ደረሳቸው። ይሁን እንጂ ደቡብ የተመደበ ባልደረባቸው ለመምጣት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ተቀያይረው ወላይታ ዞን በዴሳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው በኬሚስትሪና በሂሳብ መምህርነት መስራት ጀመሩ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት የነበራቸው ቆይታ ግን ድንገት ባጋጠማቸው ማህበራዊ ችግር ምክንያት ወደ ቦዲቲ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመዛወር እንደሰሩ ነው የተናገሩት። በዴሳ እያሉ ያጋጠማቸው ችግር ግን ስር የሰደደ በመሆኑ ከነአካቴው አካባቢውን እንዲለውጡ አስገዳዳቸውና ወደ አለታ ወንዶ ቀየሩ፡፡
ለሚያስተምሩት ትምህርት በእየለቱ ሁለትና ሶስት ጊዜ በማንበብ ዝግጅት አድርገው ወደ ክፍል ይገባሉ፡፡ ቤተመፅሃፍ ገብተው በተለያዩ መጽሃፍት ጠቃሚ መረጃዎችን ይመለከታሉ፡፡ ከድረ-ገጽ ጭምር መረጃዎችን በማጠናከር እራሳቸውን ሙሉ አድርገው ወደ ክፍል ይገባሉ፡፡ ይህም በኬሚስትሪ ትምህርት በቂ እውቀት እንዲጨብጡ ከማገዙም ባሻገር ጥሩ የሆነ የማስተማር ስነ ዘዴን እንዲላበሱም አድርጓቸዋል፡፡ በተማሪዎቻቸው ዘንድም ተወዳጅነትን አትርፎላቸዋል፡፡
በተለይ መምህር ሰለሞን ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታ እስከወጡበት 2016 ዓ.ም ድረስ ቆይታ ባደረጉበት የሀዋሳ ታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ዝናቸው በተማሪዎችና በከተማው ህብረተሰብ ዘልቆ የወጣበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ 90ዎቹ ላይ የመምህር ሰለሞን ክፍለጊዜ የትኛው ክፍል በስንት ሰአት እንደሆነ አስቀድሞ መረጃ ማሰባሰብ በተማሪዎች ዘንድ ቀዳሚ ተግባር ነበር፡፡ በአንድ ክፍል 80 እና ከዚያ በላይ መደበኛ ተማሪ ሊኖር ይችላል። ግን የቁጥሩ ልክ ግድ የለም ብቻ መምህሩ ሶል ኪሚስትሪ ይሁን እንጂ፡፡
ተማሪው ከየትኛውም ክፍል ይምጣ በመስኮትም፣ በበርም በኩል ቆሞ የመማር መብት አለው። መቼ ይሄ ብቻ ከክፍል ማስተማሩን ጨርሶ ሲወጣ ተከትሎ በመውጣት ቲቸር ይህቺ አልገባችኝም ላለ ተማሪ ክፍለ ጊዜህ አልቋል! አይባልም። በዚህ ትምህርት የብዙ ተማሪዎችን ቀልብ ሳቡ፡፡ ለጉብኝት የሚመጡ እንግዶች ሳይቀር መዳረሻቸው የመምህር ሰለሞን የኬሚስትሪ ክፍል ሆነ፡፡
በርካታ ተማሪዎችም በግል በትርፍ ጊዜህ አስተምረን የሚል ጥያቄ ሲበዛም ከስራ ሰዓት ውጪ በወር 5 ብር እያስከፈሉ በማስተማር በርካታ ተማሪዎችን ውጤታማ ማድረግ ቻሉ፡፡ ኬሚስትሪ በበርካታ ተማሪዎች ዘንድ ተወዳጅንነትንና አድናቆትን ያተረፉበት የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ የተማሪዎች አድናቆትና መልካም አክብሮት ደግሞ መምህር ሰለሞንን ይበልጥ ለሙያቸው መነሳሳትን ፈጠረላቸው፡፡
መምህር ሰለሞን 41 ዓመታትን በመምህርነት አገልግለው ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታ ወጥተዋል። ይሁን እንጂ፥ ዛሬም ከማስተማር አልተቆጠቡም። ጡረታ እንደወጡ ለመቅጠር መንደራቸውን አስሰው የመጡ የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች በቀረበላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መሰረት አሁን ላይ አኖሌና ሌሎች ትምህርት ቤቶች በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የሚወዱት መምህርነት ሙያ ዛሬም ዝም ብሎ ለመቀመጥ እድል አልሰጣቸውም፡፡ ከገንዘብ ባለፈ ማስተማሩ ለአእምሯቸው ሰላምን ይሰጣቸዋል፡፡ እውቀታቸውን አካፍለው የሰውን እርካታ መፍጠር ደስታን ይሰጣቸዋል፡፡
በመምህርነት ስኬታ ለመሆን የውስጥ ፍላጎት መሰረታዊ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ማርፈድ፣ በረባ ባረባ ምክንያት ከትምህርት ቤት መቅረት በሳቸው ዘንድ አጸያፊ ነገር ነው፡፡ “ከገንዘብ ጥቅም ባለፈ ለሰው ልጅ ካለኝ ፍቅርና አክብሮት የተነሳ ለማስተማር ጉልበቴን አልሰስትም፡፡ ጊዜየንም አልሸራርምፍም፡፡ በዚህ ባህሪየ በሰዎች ዘንድ ፍቅርንም አትርፌያለሁ፤ በ41 ዓመታት የማስተማ ስራ ላይ ከተማሪ ጋር የተጋጨሁበት ገጠመኝም የለኝም” ሲሉ ከተማሪዎች፣ ከመምህራን፣ ከቅርብ የስራ ኃላፊዎቻቸውና ከማህበረሰቡ ጋር በፍቅር የመኖር መርህ እንዳላቸውና ይህም በህይወታቸው እንደጠቀማቸው ነው የተናገሩት፡፡ በሚያስተምሩት የኬሚስትሪ ትምህርት ታዋቂነትን ቢያተርፉም እሳቸው ግን በዚህ ስመ ጥር ስራቸው እራሳቸውን አያኩራሩም፡፡
መምህር ሰለሞን በረጅም ጊዜ የማስተማር ቆይታቸው በርካታ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ዜጎችን አፍርተዋል፡፡ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ የህግ ባለሙያዎች፣ በአሜሪካው ናሳ የሚሰሩ ሳይንትስቶችና ተመራማሪዎች፣ የአይሮፕላን አብራሪዎችን እና ሌሎችን አፍርተዋል፡፡ ይህን ሲመለከቱም የመንፈስ እርካታ ይሰማቸዋል፡፡ መምህር ሰለሞን በግል ጉዳይ በተለያዩ ቢሮዎች በገቡ ቁጥር ተማሪዎችን ሲያገኙ እጅግ ደስተኛ እንደሚሆኑም ነግረውኛል። “በቃ ድካሜ ፍሬ አፍርቶ ከማየት ሌላ ምን ትርፍ አለ?” ሲሉም ራሳቸውን መልሰው ይጠይቃሉ።
በዚህ የከበረ ሙያ በርካታ ሰብአዊ ልእልናን አትርፈውበታል፡፡ ገንዘብ ሳይሆን የሰውን ፍቅርና አክብሮትን አጎናጽፏቸዋል፡፡ “ለአንድ ባለጸጋ ከሚሰጠው በላይ ፍቅርንና አክብሮትን አትርፌበታለሁ፡፡ አንተ አስተምረኸኝ ዛሬ ለዚህ በቅቻለው ብለው ጎንበስ ብለው እጅ ይነሱኛል፤ ያመሰግኑኛል፡፡ ብታመም ብወድቅ ገንዘብ አለኝ ከሚለው ባለጸጋ በላይ ፈጥኖ የሚደርስልኝን ህዝብ አትርፌያለሁ፡፡ ለሰው ስትኖር ሰው ደግሞ ውለታውን ይመልሳል” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ረጅም ዓመታትን ባስቆጠረው የመምህርነት አገልግሎት አንድ ገጠመኛቸውንም አጫውተውኛል፡፡ መምህር ሰለሞን በተማሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ከመሆናቸው የተነሳ በማንኛውም ሁኔታ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ እልባት ለመስጠት በትምህርት ቤትም ይሁን በማህበረሰቡ ዘንድ የመጀመሪያው ሰው ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት (በ1997 ዓ.ም) በሚያስተምሩበት በታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በተማሪዎች ዘንድ ግርግር ተፈጠረ፡፡
ተማሪዎችም የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ ለቀው መንግስትን በመቃወም ድምጻቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ መምህር ሰለሞንም ይህን እንዲያረጋጉ ተመርጠው ተማሪዎችን አሰባስበው ማወያየት ጀመሩ፡፡ ችግሩን አርግበው ሰላምን በማስፈን ላይ እያሉ ግን አንድ ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ፡፡ ድንገት አጥር ዘለው የገቡ የታጠቁ ወታደሮች በተማሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተው ጉዳት አደረሱ፡፡ በርካቶችን ሙትና ቁስለኛ አደረጓቸው። እሳቸውም በነበረው ግርግር እጃቸው ላይ ጉዳት ደረሰባቸ፡፡ ይህ በህይወታቸው ሊረሱት የማይችሉት መጥፎ ገጠመኝ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
“በሌላ ጊዜ ደግሞ ተማሪዎች ስለሚወዱኝ በነበረው ግርግር ትምህርት ቤት እንዳልገባ እና ትምህርት ቤቱንም ለቀቄ እንድወጣ ነገሩኝ፡፡ ይህንንም ድብቅ መረጃ ለሌሎች የስራ ባልደረቦቼ ነገርኳቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ ተማሪዎችን ለቀን አንሄድም በማለት ፈቃደኛ አልሆኑም። አድማ በታኝ መጥቶ አስለቃሽ ጭስና ተኩስ ሲከፈት የተከሰተውን ክስተት ሳስስታውስ ደግሞ ዛሬም ውስጤን ያስቀዋል በማለት በስራ ቆይታቸው ያጋጠማቸውን አሳዛኝና አስደሳች ገጠመኛቸውን አጋርተውናል፡፡
መምህር ሰለሞን (ሶል ኬሚስትሪ) በተማሪዎችና በማህበረሰቡ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በበጎ እና ቅን አሳቢዎች አንድ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ነው የገለጹልኝ፡፡ በዚህም ለስጦታው ክብር እንዳላቸው ገልጸው ከስጦታው በላይ ደግሞ ይህን እውቅና ይገባሃል ብለው ላሰቧቸው ሰዎች ምስጋናቸው ወደር እንደሌለው ነው የተናገሩት፡፡ “የከተማው ነዋሪ፣ የቀድሞ ተማሪዎችና መምህራን፣ በሙሉ ተሰባስበው ይገባሃል በማለታቸው ያለኝ አክብሮት ልዩ ስፍራ አለው” በማለት፡፡
ባሳለፉበት የማስተማር ቆይታ የትምህርት ስርዓቱ ላይ ችግር እንዳለም ስለመታዘባቸው ነው የተናገሩት፡፡ በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በትምህርት ስርዓቱና በመንግስት የቁርጠኝነት ማነስ የትምህርት ስርአቱ መጎዳቱን ነው የተናገሩት፡፡ ተማሪዎች ዘመኑ ቴክኖሎጂ ያጎናጸፋቸው ዕድል ቢኖርም ይህን የእውቀት መገንቢያ ሀይል አድርገው አለመጠቀማቸው ችግር እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ተማሪዎች ዓላማቸውን በውል ተገንዝበው አለመጓዛቸው አብዛኞችን የጉዳት ሰለባ እያደረጋቸው ነው፡፡ ቤተሰብም የዚህ ችግር ተባባሪ ሆኗል ባይ ናቸው፡፡
በመምህራን ዘንድም ለሙያው ያላቸው ፍቅርና የአቅም ማነስ በትምህርት ስርዓቱ ላይ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ እያለፈ ስለመሆኑም ነው የታዘቡት፡፡ በተመደቡበት ክፍለ ጊዜ ገብተው ለማስተማር ዳተኛ የሆኑ መምህራን አሉ፡፡ በሰበብ አስባብ ትምህርት ቤት የማይመጡና ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ ያልሆኑ መምህራን አሉ፡፡ ምንም እንኳ በመምህራን ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳለ የማይካድ ቢሆንም ተማሪዎችን በተለያዩ ምክንያቶች መጉዳት አሁን ለተከሰተው የትምህርት ስብራት አንዱ ችግር እንደሆነ ታዝበዋል፡፡
መንግስትም ከትምህርት ጥራት ይልቅ ሽፋን ላይ ትኩረት ማድረጉ የትምህርት ስርዓቱን በእጅጉ እንደጎዳው ነው የተናገሩት፡፡ ተማሪዎች በውጤት ተለክተው ከማሳለፍ ይልቅ በጅምላ ከክፍል ክፍል እንዲያልፉ መደረጉ ዛሬ ላይ ችግሩ ገፍቶ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ ይህን ችግር ለመለወጥ ካስፈለገም ህጻናት ከመነሻው በእውቀትና በስነ ምግባር ታንጸው የሚወጡበት አሰራር መዘርጋት አለበት ባይ ናቸው፡፡
ለዚህ ስር ለሰደደ ችግር ደግሞ መፍትሄው ተወቃሽ የሆኑት አካላት ስር ነቀል የመፍትሄ ሀሳቦች ሊዘረጉ ይገባል፡፡ ከወቀሳ ባለፈ ሀገርን ለማዳንና ችግርን ለማረም መስማማት ይገባል፡፡ ችግሮችን ሁሉ መምህራን ላይ ብቻ የሚወረወር ከሆነ መፍትሄ አይመጣም ባይ ናቸው፡፡
More Stories
“በጀት በፍትሀዊነት ካልተመራ በህዝቦች መካከል መተማመን ያሳጣል” – ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ
ጨረቃ እና ሙዚቃ
እድሜ ጠገቧ ከተማ