“ችግር ተስፋ ቢስ ሊያደርገኝ ሞከረ፤ እድል ግን አልሰጠሁትም” – ወጣት መውደድ ታደሰ
በደረሰ አስፋው
ሰርቼ ያፈራሁትን ገንዘብ በአጭበርባሪዎች መና ቀረሁ፡፡ ራሴን ተስፋ እንደሌለው ሰው አድርጌ ቆጠርኩ፡፡ ደስታዬን ሁሉ ቀማኝ፡፡ በራስ የመተማመን ስሜቴን ጎዳው፡፡ የበረታውን ጉልበቴ አልፈሰፈሰው፡፡
ይሁን እንጂ ከጎኔ የነበሩ አይዞሽ ባዮች ለጊዜያዊ ችግሬ ጉልበት ሆኑኝ፡፡ ምክራቸው አበረታኝ፤ የደከመውን ጉልበቴን አበረቱት። ዛሬ አዲስ ማንነት ለብሼ ባደረኩት ጥረት ለዚህ በቅቻለሁ። አልችልም የሚለው ስሜቴ በእችላለሁ ተቀይሮ በአዲስ ምዕራፍ ላይ ጉዞ ጀምሬያለሁ ስትል ነው ሀሳቧን የጀመረችው፡፡
ወጣቷ ባለታሪካችን ትምህርቷን አቋርጣ፣ ከትውልድ ቀዬዋ ስትወጣ አንድ ዓላማ ነበራት። ከተማ ሰርቼ እለወጣለሁ፤ ቤተሰቤንም እለውጣለሁ የሚል፡፡ በሰው ቤት ተቀጥራ ከተላላኪነት እስከ ሆቴል ቤት አስተናጋጅነት ሰርታለች፡፡ በዚህም በርካታ ውጣ ውረዶችንና ችግርን ተጋፍጣለች፡፡ ይህ የህይወት ገጠመኞቿ ግን የራሴ የምትለውን ስራ ለመጀመር አነሳሳት፡፡
ከዛሬ 6 ዓመት በፊት ወደ ሀዋሳ ከተማ መጥታ የራሷ ሻይ ቡና ስራ በመጀመር እውን አደረገችው፡፡ ስራውም ውጤታማ አደረጋት፡፡ ከምታገኘው እለታዊ ገቢም በመቆጠብና እቁብ በመግባት የወደፊት እጣ ፈንታዋን ለማለምለም የሞራል ስንቅ ሆናት፡፡ ታዲያ ከእለታት በአንዱ ቀን ያላሰበችው ክፉ ቀማኛ አጋጠማት፡፡ ሻይ ቡና ሰርታ ያጠራቀመችውን ከ300 ሺህ ብር በላይ የሆነ ገንዘቧን ባልገመተችው መንገድ አጣች፡፡
ነገን ለትልቅ ቁም ነገር ለምትመኘው ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዋ ያልጠበቀችው መሰናክል ሆነባት፡፡ ተስፋ ቢስ ሊያደርጋትም ሞከረ፡፡ የስራ ተነሳሽነቷን ጎዳው፡፡ ይሁን እንጂ እድል አልሰጠችውም። ይልቁንስ ይህ ገጠመኝ አንድ የኑሮ ዘዴን አለማመዳት፡፡
ማግኘት እንዳለ ሁሉ ማጣት ሊኖር እንደሚችል፤ ይህን ማሸነፊያ መንገዱም ትጋትና ፅናት እንደሆነ ተገንዘበች፡፡ መንፈሰ ብርቱዋ የዛሬው የእቱ መለኛ አምድ ባለታሪካችን የትናንቱን መጥፎ ገጠመኝ ወደ ኋላ ማሰብን አትሻም፤ ይልቁንስ ከፊቷ ለሰነቀችው ራዕይ ትተጋለች፡፡
ወጣት መውደድ ታደሰ በጉራጌ ዞን ምሁር ኢየሱስ ገዳም አካባቢ ነው የተወለደችው፡፡ በዚሁ የትውልድ ቀዬዋ ከመሰል እኩዮቿ ጋር አፈር ፈጭታ፣ ጭቃ አቡክታ፣ በሜዳው ቦርቃ፣ አቀበቱን ወጥታና ቁልቁለቱን ወርዳ አድጋለች፡፡
ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም በአካባቢዋ በሚገኝ ጬዛ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል፣ በተመሳሳይ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷንም በጬዛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 10ኛ ክፍል ተምራለች፡፡
የጀመረችውን የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ግን አላዛለቀችውም፡፡ ትምህርቷን አቋርጣ አካባቢዋንም ለቃ ለስራ ወደ ኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ሄደች፡፡ በትውልድ አካባቢዋ ለስራ ወደ ከተማ የመሄድ ልምድ በእሷም ላይ ጫና ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ይህም አካባቢዋን ለመልቀቅ ምክንያት እንደነበር ነው የገለጸችልን፡፡
ይሁን እንጂ ለወጣት መውደድ አካባቢን ለቆ ወደ ከተማ መፍለስ እንዲሁ ገንዘብ የሚታፈስበት አይደለም፡፡ በርካታ የኑሮ ጫናዎችን ለማሸነፍ ሌት ተቀን የሚጋፈጡበት እንጂ፡፡
ገጠር ሆኖ እንደሚታሰበው አለመሆኑን ከወጣች በኋላ ተገነዘበች፡፡ ደክሞ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንዳልነበረ ነው ያረጋገጠችው፡፡ ሰርታ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ህልም ቢኖራትም ችግሩ ግን ሰፊ ነበር፡፡
አምቦ ከተማ ሄዳ ከተላላኪነት እስከ የሆቴል ቤት አስተናጋጅነት ሰራች፡፡ በዚህም በወር 300 ብር ብቻ እየተከፈላት ትሰራ ነበር፡፡ በዚህ ስራ ለአንድ አመት መቆየቷን ነው የተናገረችው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መኖሪያዋን ያደረገችው በሀዋሳ ከተማ ነው፡፡
ሀዋሳም የጀመረችው የመስተንግዶ ስራ ነው። ይሁን እንጂ በሰው ቤት እስከ መቼ የሚለው ሀሳቧ ሚዛን እየደፋ መጣና የኔ የምትለውን ስራ ለመጀመር የነበራት ውጥን እውን ሆነ፡፡
የዛሬ 6 አመት የጀመረችው ስራ የሻይ ቡና ንግድ ነው፡፡ በዚሁ ቦታ ላይ እየሰራች አግኝተን ነው ያነጋገርናት፡፡ በርካታ ደንበኞች በታደሙበት ወቅት ነው ያገኘናት፡፡ ሻይ፣ ቡና እና ማኪያቶ የምትሰጣቸው አገልግሎቶች ናቸው፡፡
በምታዘጋጃቸው ትኩስ መጠጦች የደንበኞችን ፍላጎት ያሟላች ስለመሆኗ ከደንበኞቿ መረዳት ቻልኩ፡፡ በጥራት የምታዘጋጃቸው ትኩስ መጠጦቿ ለደንበኞቿ መበራከት ምክንያት እንደሆነና እሷም ቢሆን ለደንበኞቿ ልዩ ክብር እንዳላት ነው የገለጸችልን፡፡
በዚህ ስራ ብቻ የተገደበች እንዳልሆነም ወጣት መውደድ ገለጸችልን፡፡ ማምሻ ላይ ደግሞ ጎመን በቂጣ የምታዘጋጅ ሲሆን በዚህም ጣፋጭ ምግቧ ከርቀት ስፍራ ጭምር ደንበኞቿ እንደሚመጡ ነው የተናገረችው፡፡ የሰው ልጅ የሀሳብ ጥንካሬ ካለው መለወጡ አይቀርም፡፡
በመውደቅ በመነሳት መካከል ማሸነፍ አለ የሚል አስተሳሰብ አላት፡፡ “ከውጭ ሆኖ ለሚያየው ቡና እና ሻይ ሸጦ መለወጥ የሚባል ነገር ያለ አይመስለውም፤ እኔ ግን ተለውጬበታለሁ” ያለች ሲሆን በዚህም ስራ በርካታ የህይወት ለውጦችን እንዳመጣችበት ነው የተናገረችው፡፡
ይሁን እንጂ ወጣት መውደድ ከእለታት በአንዱ ክፉ ቀን አንድ መጥፎ አጋጣሚ ገጠማት፡፡ ነገ የተሻለ ሰው ለመሆን አስባ ቆጥባና እቁብ ገብታ የሰበሰበችው ከ300 ሺህ ብር በላይ ባልታመነ ሰው እጅ ገባና ላታገኘው አመለጣት፡፡
ለአመታት የሰራችበትን ጥሪቷን ከንቱ አደረገው፡፡ ይህ ህይወት ከባድ የሆነ ፈተናን እንድትጋፈጥ አደረጋት፡፡ ተስፈኛዋን ወጣት ተስፋ ሊያስቆርጣት ሞከረ፡፡ ግን አልሆነለትም፡፡
ዛሬ ላይ መውደድ በአዲስ ማንነት ውስጥ ሆና ስራዋን ጠንክራ እየሰራች ነው፡፡ “ምስጋና ከጎኔ ሆነው ላጽናኑኝና ላበረቱኝ ወገኖች ዛሬ ላይ የትናንቱን ረስቼ በአዲስ የማንነት ምዕራፍ ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ካጣሁት በላይ ማግኘት እችላለሁ ብዬ ተነስቻለሁ፡፡ ነገን የተሻለ ለማድረግ እየተጋሁ ነው” ስትል ነው የገለጸችልን፡፡
ተስፋ መቁረጥ ህይወትን የሚጎዳ ነገር እንደሆነ ስለመገንዘቧም ነው ያጫወተችን፡፡ ሰዎች ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ እንዳይገቡም ትመክራለች። ይሁን እንጂ ያጋጠማት ችግር ይበልጥ ብርታት እንደሰጣትም ታነሳለች፡፡ ዛሬ ላይ ከምትሰራውም ከወጪ ቀሪ በየቀኑ 300 ብር እቁብ ትጥላለች፡፡ አብራት ከምትሰራዋ እህቷ በተጨማሪ ለ2 ሰዎችም የስራ ዕድል ፈጥራለች፡፡
ወጣት መውደድ የቤት ክራይና የየእለት ወጪዋን የምትሸፍነው በዚሁ ስራ ነው፡፡ ወደፊት ከዚህ የተሻለ ህይወትን ለመምራት አስባ ነው ምትሰራው፡፡ ከሻይ ቡናው አለፍ ሲልም ሆቴል ቤት ለመክፈት ዕቅድ እንዳላት ገልጻ ይህንንም እውን እንደምታደርገው እምነቷ ነው፡፡ ትናንት ተቀጥራ ከተላላኪነት እስከ አስተናጋጅነት ስትሰራ እዚህ እንደምትደርስ ነበር ህልሟ፡፡
በርካታ ወጣት ሴቶች በሀገር ውስጥ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ ወደ ውጪ የመሄዱን ነገር ትኮንናለች፡፡ የአመለካከት ችግር እንጂ በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል ባይ ነች፡፡ “በርካታ የስራ አማራጮች አሉ፡፡ ከውጭ ይልቅ በሀገር ውስጥ ሰርቶ ትርፋማ መሆን ይቻላል፡፡ እነዚህን እድሎች በመጠቀም ሰርቶ መለወጥ ይቻላል፡፡ ዋናው አስተሳሰብ ነው እንጂ” በማለት ትናገራለች።
“የቀደሙ እናቶቻችን በበርካታ ባህላዊ ተጽእኖ ውስጥ ሆነው ዘመናትን በችግር እንዳለፉ እገነዘባለሁ፡፡ አሁን ግን ዘመኑ ተለውጧል፡፡ መንግስትም ለሴቶች ልዩ ድጋፍን ሰጥቷል፡፡ ሴቶች ሰርተው ውጤታማ መሆን ይችላሉ፡፡
“ስለዚህ ራሳቸውን ከባህል ተጽእኖና አልችልም ከሚል አመለካከት አውጥተው ሰርተው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን መለወጥ አለባቸው” ስትል ነው አስተያየቷን የሰጠችው፡፡
ከአርሶ አደር ቤተሰቦች የተገኘችውና የቤተሰቡ 3ኛ ልጅ እንደሆነች የገለጸችው መውደድ በአካባቢዋ አብዛኛው ሰው ወደ ከተማ በመሄድ ሰርቶ የተለወጠ ቢሆንም በሀገር ቤትም ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ተገንዝባለች፡፡
ወደ ገጠሩም በርካታ የስራ አማራጮች በመኖራቸው ወደፊት በትውልድ አካባቢዋ ለእሷም ሆነ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሰማራት ፈር ቀዳጅ የመሆን ህልም አላት፡፡ ከራሷም አልፋ ለሌሎች የስራ ዕድል በመፍጠር የአካባቢውን ወጣት ከስደት ለማስቀረት ዕቅድ አላት፡፡
በቀን ከቡና ሽያጭ ከወጪ ቀሪ እስከ 500 ብር እንደምታገኝ ገልጻ ይህ ግን እንደ ገበያው ሁኔታ ከፍና ዝቅ ሊልም እንደሚችል ነው የተናገረችው፡፡ ጠንክሮ ለሰራ የጀበና ቡና ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ከህይወት ተሞክሮዋ መገንዘብ ችላለች፡፡ በእሷ ልምድም ሌሎች ሴቶች ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ቢኖር ጥረት ስኬታማ ያደርጋልና ወጥታችሁ ስሩ ስትል ነው አስተያየቷን የሰጠችው።
More Stories
“ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በክልሉ ምቹ የንግድ አካባቢ እንዲፈጠር አስችሏል” – የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ
“ሴትነት የጾታ እንጂ ያለመቻል መገለጫ አይደለም” – ወይዘሮ መኪያ እንድሪስ
“ተማሪዎቼ የሚፈልጉበት ደረጃ እንዲደርሱ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” – መምህርት ዋጋዬ ደግፌ