ሥራው ሳንቲም ከማግኘት ባለፈ ህይወቴን ቃኝቶታል – አስናቀች እንዳለ

በደረሰ አስፋው

ሴቶች በወንዶች ውበት አገልግሎት (ፀጉር ስራ) መሰማራት እንደነውር ይታይ ነበር፡፡ ሴት አትችልም የሚለው አመለካከት እንዳለ ሆኖ ለሌላ ዓላማ እንደተሰማራች ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ በበርካታ ማህበረሰብ ዘንድ የሚስተዋለው የአመለካከት ችግር መነሻው ሴቶችን በፀጉር ቤት ማየት እንግዳ ነገር ስለነበር ስለመታዘቧም ነው የገለጸችው።

ተጽዕኖው ግን ካሰበቸው ዓላማ ወደ ኋላ አልጎተታትም፡፡ ይልቁንስ ሙያውን እንጀራዋ ልታደርገው እልህ ተጋች፡፡ በ1993 ዓ.ም በ30 ብር በጽዳት ሠራተኝነት የጀመረው ስራዋ ዛሬ ላይ የራሷን ድርጅት አቋቁማ ለሌሎችም የስራ ዕድል መፍጠር አስችሏታል፡፡ በዚህ ሙያ መሰማራቷም በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እንዳጎናጸፋት ነው ተናገረችው፡፡

በወቅቱ የውበት ማሰልጠኛ አልነበረም። እንደአሁኑ መረጃዎችን ከድረ-ገጽ ማግኘት የሚቻልበት አማራጭም አልነበረም። ከሚሰሩ ሰዎች በመመልከትና በመሞከር ብቻ የሙያውን ክህሎት አዳበረች፡፡ ከጽዳት ሰራተኝነት ወጥታም በሙያው ተቀጥራ መስራት ችላለች፡፡ በዚህ የስራ ጅማሬዋ የአንድ ወንድ ፀጉር አስተካክላ 2 ብር ብቻ ታገኝ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

የዛሬው የእቱ መለኛ አምድ ባለታሪካችን እዚህ ለመድረስ በርካታ የሚባሉ ተግዳሮቶችን ያለፈች ቢሆንም ዓላማ ካለ መድረስ የሚገባው ቦታ ከመድረስ የሚገድብ ነገር የለም ስትል ነው የገለጸችው፡፡

የስራ ቦታዋ ሀዋሳ ከተማ አረብ ሰፈር ምድረ ገነት አንደኛ ፎቅ ህንጻ ላይ ነው። በዚህ አገልግሎቷም ማንኛውንም የወንዶች የጸጉር ውበት አገልግሎት ትሰጣለች፡፡ “ወንዶች ሲመጡ እንደፍላጎታቸው ውብ አድርገን እናሳምራቸዋለን” ስትል ሁሉንም ዓይነት የፀጉር ሥራ እንደምትሰራ በልበ-ሙሉነት ትናገራለች፡፡

የዛሬው እቱ መለኛዋ እንስት አስናቀች እንዳለ ትባላለች፡፡ የተወለደችው በአርባ ምንጭ ከተማ በተለምዶ ልማት በሚባለው ሰፈር ነው፡፡ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም በዚሁ ከተማ እስከ 6ኛ ክፍል ተምራለች። ወላጅ አባቷ ወደ ሀዋሳ እርሻ ልማት ተቀይረው ሲመጡ እሷና ሌሎች ቤተሰቦቿም ወደ ሀዋሳ ከተማ መጥተው መኖር ጀመሩ፡፡ በሀዋሳ ከተማ ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በታቦር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡

ቤተሰቦቿ በድጋሜ ለስራ ተመልሰው ወደ አርባ ምንጭ ሲሄዱ አስናቀች እና እህቷ ግን ሀዋሳ ከተማን መኖሪያቸው አደረጉ። በትምህርቱ መቀጠል ብትፈልግም ሰርቶ እራስን መቻል ወደሚለው ሀሳብ አዘነበለች። ብዙዎች ለምን አትማሪም እያሉ ምክር ቢሰጧትም አስናቀች ግን “ከመማር ይልቅ መብላት ይቀድም ነበርና ስራን ምርጫዬ አደረኩ” ስትል መልስ ትሰጥ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

አስናቀች ይህን ማለቷ መማርን ጠልታ ሳይሆን ከቤተሰብ ድጋፍ ውጭ ለነበረው ኑሮዋ በልቶ ማደር የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ስለነበረች ነው፡፡ መጀመሪያ የተቀጠረችበት የስራ መስክ የወንዶች የጸጉር ቤት ውስጥ በጽዳት ሠራተኝነት ነበር፡፡ ጎን ለጎንም በሂሳብ ተቀባይነት በመስራት በወር 30 ብር ይከፈላታል፡፡ ይህ ለጀማሪ ስራ ተቀጣሪዋ ብርቅ ነበር፡፡ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቿ ጋር ተግባብታ ትሰራለች፡፡ ለአስናቀች ይህ ዕድል መልካም ነገር ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ ከጽዳቱ ስራ ጎን ለጎን ሙያውንም በአንክሮ ትከታተል ጀመር፡፡

የእለት ሂሳብ የምትመዘግበው እሷው ስለነበረች የሚያስገኘውን ጥቅም ተገነዘበች። ተቀጥረው የሚሰሩት ባለሙያዎችም ቢሆን በዚሁ ስራ በሚያገኙት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ የቤት ኪራይ የሚከፍሉበት፣ ልጆቻቸውን ከፍለው የሚያስተምሩበት እና ሌሎች ወጪዎቻቸውን የሚሸፍኑበት ስለመሆኑ አረጋገጠች፡፡ በዚህም ለሙያው ያላት አመለካከት ተቀየረ፡፡ ስራውንም የራሷ ለማድረግ ወሰነች፡፡ በዚህም አትኩሮቷን በስራው ላይ አደረገች፡፡

በአንዳንድ በጎ ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ስራውን መለማመድ ጀመረች፡፡ “የነገዋን አስናቀች ራዕይ እውን ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡኝን፣ ቅን ወዳጅነታቸውን የለገሱኝን ወገኖች ሳላመሰግናቸው አላልፍም። ከፍለውኝ እኔ ደግሞ እለማመድባቸው ነበር›› ያለች ሲሆን ስራውንም እንድትወደው እድል እንደፈጠሩላት ነው የተናገረችው፡፡

“ለመለወጥ የነበረኝ ጉጉት የተለየ ነበር። በፀጉር ቤቱ ስራ መጀመሬም በጽዳት ከማገኘው ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ፈጠረልኝ። አምስት ሰው ሰርቼ 10 ብር አስገብቼ 5 ብር የማገኝበት ዕድል ተፈጠረ፡፡ በወር 150 ብርና ከዚያ በላይ የማግኘት እድሌን አሳደገው። በሙያውም እራሴን እያሻሻልኩ መጣሁ። ከተቀጣሪነት ወጥቼ የራሴን የወንዶች ጸጉር ውበት አገልግሎት ከፈትኩ፡፡

ሴት ሆነሽ የወንድን ጸጉር በመስራትሽ ያጋጠመሽ ነገር አልነበረም? ስንል ላነሳንላት ጥያቄም፡-

“በእርግጥም ገጠመኞች ነበሩ፡፡ ሴት ልጅ የወንድን ጸጉር ይዛ መስራት የተለመደ አልነበረም፡፡ ከሀይማኖት አኳያም በሴት ልጅ ሊነኩ የማይፈልጉ አሉ፡፡ ሴት መሆኔን አይተው ከበር የሚመለሱ በርካቶች ነበሩ። አንዳንዶች ደግሞ ሴትነቴን ያዩና ጺሜን ብቻ ስሪ ይሉና አያያዜን ሲያዩ ሙሉ ጸጉር እንድሰራ የሚፈቅዱ አጋጥመውኛል፡፡ ለሌላ ዓላማ እንደምሰራ የሚገምቱም አልጠፉም። ቲፕ ሰጥተው ንግግራቸው ሌላ አዝማሚያ ያለው ይሆን ነበር፡፡ ሚስቴ ወይም እህቴ ብትሆኚ የወንዶች ጸጉር ስራን አላሰራሽም የሚሉም አጋጥመውኛል፡፡ አሁን ላይ ግን ይህ አመለካከት ተለውጧል፡፡ መጀመሪያም ውበት ለሴቶች እንጂ ለወንዶች የተሰጠ አልነበረም›› ስትል ገጠመኞቿን አገውግታናለች፡፡

‹‹ልጅ ተወልዶ ቀድሞ የሚላጨው ማነው? እናቱ ናት፡፡ ወንዶች ቀድመው ስራውን ስለጀመሩ ሙያው የወንዶች መሰለ እንጂ ሙያው የሴቶች ነው፡፡ ውበት የሴት ነው፤ ማሳመር የሴት ነው እንጂ የወንድ አይደለም። አሁን ላይ ወንዶችም ይህን ተቀብለውታል” ስትልም ሃሳቧን ታጠናክራለች፡፡

በ1996 ዓ.ም የጀመረችው የአስናቀች (አስኒ) የወንዶች የጸጉር ውበት አገልግሎት መተዳደሪያዋ ነው፡፡ በዚህ ስራ በመሰማራቷ በርካታ ጥቅሞችን አግኝታበታለች፡፡ በማህበራዊ ቢሆን በኢኮኖሚያው ዘርፍ ተጠቃሚ አድርጓታል፡፡ በስራዋም ደስተኛ እንደሆነች ነው የተናገረችው፡፡

ስራውን ስትሰራ እንደ ወንድም እንደ ሴት ሆና እንደምትሰራ የምትገልጸው አስናቀች፤ ሥራዋን በምትሰራበት ወቅት በርካታ ማህበራዊ ጉዳዮች እንደምትቀስም ነው የገለጸችው፡፡ ወንዶች በሚያነሷቸው ማህበራዊ ጉዳዮች በተለይ ከትዳር አጋራቸው ጋር ስለሚፈጠር አለመግባባት መነሻ በማድረግ ምክሯን እንደምትለግስ ነው የተናገረችው፡፡ “ብልህ ከሰው ይማራል፤ ሞኝ ደግሞ ከደረሰበት ይማራል” እንደሚባለው አንዳንድ ወንዶች በምትለግሳቸው ምክሮች ህይወታቸው እንደተቀየረም ነው የምታነሳው።

“ስራው ከብዙ ታላላቅ ሰዎች ጋር አስተዋውቆኛል፡፡ ማህበራዊ ግንኙነቴን እንዳሳድግ እድል ፈጥሮልኛል፡፡ በራስ መተማመን እንዲኖረኝ አድርጓል። ከምሰማው ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፡፡ ከማየውም እንዲሁ። በዚህ ሙያ መሰማራቴ ሳንቲም ከማግኘት ባለፈ ህይወቴን ቃኝቶታል የሚል አመለካከት አለኝ” ነው ያለችው፡፡

ዛሬ ላይ ስራው ቢቀዘቅዝም ቀደም ሲል እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ትሰራ ነበር፡፡ ከስራ ስትመለስ በቤተሰቧ መልካም አቀባበል ነው የሚደረግላት፡፡ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አኳያም የተሻለ ገቢ ታገኛለች፡፡ የኑሮ ዘይቤዋን ቀይሮላታል፡፡ ከቤት ተከራይነት ወጥታ የራሷን መኖሪያ ቤት መስራት ችላለች። ባለቤቷ የመንግስት ሰራተኛ በመሆኑ በወር አንዴ ተጠብቆ ከሚገኝ ገቢ ታድጓታል። “አለቃዬ ስራዬ በመሆኑ በዚህም ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን አግዞኛል፡፡ በራስ መተማመንን ፈጥሮልኛል” ብላለች፡፡

አስናቀች ከራሷ ባለፈ ለሌሎች የፈጠረችው የስራ ዕድል ደግሞ ይበልጥ እርካታን ፈጥሮላታል፡፡ በርካታ ሰዎች ሙያውን ወደውት ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጋለች፡፡ ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ያላትን ሙያ በማጋራት ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ ለብዙ ሴቶች አርአያ በመሆን በስራቸው እንዲበረታቱ አድርጋለች፡፡

ሴቶች ከቤት ወጥተው ለመስራት ብዙ ተጽእኖዎች አለባቸው፡፡ አንችስ ይህ ተጽእኖ አላጋጠመሽም? ስንል ላነሳንላት ጥያቄ፡-

“እንደ እድል ሆኖ ይህ ተጽእኖ በእኔ ላይ አልደረሰም፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሴት ሆና ስራ መስራትን የምትጠላ አለች የሚል ሀሳብ ግን የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ በወንዶች ያለው አመለካከት መለወጥ አለበት፡፡ ሴቷ ወጥታ እንድተሰራ ዕድል ሊፈጥሩላት ይገባል፡፡ እራሷን ከቻለች ስጋት አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ ይታያል፡፡ የእሱ ጥገኛ ሆና እንድትኖር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለብዙዎች ትዳር መፍረስ ምክንያት እየሆነ ይገኛልና ወንዶች ሴቶች ወጥተው እንዲሰሩ እድሉን ቢያመቻቹላቸው የሴቶችም ይሁን የቤተሰብ ህይወት ይለወጣል” ነው ያለችው፡፡

ይህ አስተሳሰብ በሷ የትዳር ህይወት እንደማይሰተዋል ገልጻ በዚህም ባለቤቷ ለሷ ያለውን አመለካከት ዛሬ ለደረሰችበት የለውጥ ጎዳና ከፍተኛውን ስፍራ እንደሚይዝ ነው የተናገረችው፡፡ ወጥታ እንድትሰራ እንጂ በቤት ውስጥ ጊዜዋን ባልባሌ ሁኔታ እንድታሳልፍ አይፈቅድላትም፡፡

አሰናቀች በ30 ብር ተቀጣሪነት የጀመረውን የወንዶች የፀጉር ውበት አገልግሎት ከዚህ የበለጠ ለማሳደግ ነው ሀሳቧ፡፡ ‹ሰው ያስባል እግዚአብሄር ይፈጽማል› እንደሚባለው የትናንቱ ታሪኳን ለመቀየር ነው የምትተጋው። ትናንት በ1 ሺህ 500 ብር ተከራይታ ከምትሰራበት ወጥታ ዛሬ ላይ ከ10 ሺህ ብር በላይ በሆነ ደረጃውን በጠበቀ ቤት ላይ ነው የምትሰራው፡፡ ስራውም እየዘመነ መጥቶ ከትናንቱ 2 ብር ክፍያ ተሻግሮ ዛሬ ላይ እስከ 300 ብር ነው በአንድ ሰው የሚከፈለው። ነገም በአቅምም ይሁን በግብአት በማደራጀት የተሻለ የስራ ቦታ ለማድረግ ነው እቅዷ፡፡

“ሙያዬን መጣል አልፈልግም። ነገ ልጆቼም ከዚህ በተሻለ በማዘመን የሙያው ባለቤት እንዲሆኑ እመኛለሁ። ሙያው ከማንኛውም ስራ የተሻለ ነው። ስለዚህ ሙያውን በማዘመን ወደ ልጆቼም የማደርስ ነው የሚሆነው” ስትል የነገ ዕቅዷን ነግራናለች። እኛም ያሰበችው እንዲሳካ እየተመኘን የዛሬን በዚህ አበቃን ሠላም፡፡