ጉዳት የሚያስከትሉ ተላላፊ በሽታዎችን ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት በተከታታይነት መከላከል እንደሚጠበቅባቸው ኢንስቲትዩቱ አሳሰበ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያየ መንገድ በዜጎች ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ተላላፊ በሽታዎችን ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት በተከታታይነት መከላከል እንደሚጠበቅባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳስቧል።
ኢንስቲትዩቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ አካላት በተገኙበት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በጂንካ ከተማ ምክክር አድርጓል።
በመድረኩ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች፣ የተላመዱና በተለያየ ጊዜ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችና መሰል ጉዳዩች ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት በተሳታፊዎች ተደርጓል።
ከኤም ፖክስ በሽታ ጋር በተያያዘም ገለፃ ተደርጓል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አጉኔ አሾሌ እንደገለፁት፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ዋና ዓላማ በየአካባቢው በተለያየ መንገድ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን በአንድ አሀድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታስቦ ነው።
በተለይ ከእንስሳት ወደ ሰው እንዲሁም በተለያየ መልኩ እንስሳት ላይም የሚከተሰቱ በሽታዎችንም መከላከል ያስችል ዘንድ ከጤና ባለሙያዎች በተጨማሪ ከእንስሳትና ዓሳ ሀብት፣ ከደንና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ካላቸው ሴክተር መሥሪያ ቤት የተውጣጡ አካላት በተገኙበት ግንዛቤ መፈጠሩንም ኃላፊው አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከመቸውም ጊዜ በላይ ለዜጎች ጤናና ደህንነት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ስለመሆኑም አቶ አጉኔ ገልፀዋል።
በመድረኩ የተገኙ አካላትም በተወያዩትና በተስማሙት ልክ ወደመጡበት አካባቢ ሲመለሱ እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን ተገለጸ
የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የጤናው ዘርፍ ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አደረገ
እድሚያቸው ከ40 አመት በላይ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የአንጀት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቆመ