ትኩረት የሚሹ ሓሩራማ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከል የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
በጋሞ ዞን ትኩረት የሚሹ ሓሩራማ በሽታዎች ፕሮግራም የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች ማጥፊያ የማህበረሰብ አቀፍ መድሃኒት እደላ የአመራር እና የባለሙያዎች ስልጠና መርሀ ግብር ተጀምሯል።
የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች ማጥፊያ ዘመቻ ከ4 መቶ ሺህ በላይ ህፃናት በዞኑ መዋቅር ተደራሽ እንደሚደረጉ የጋሞ የዞን ጤና መምሪያ ገልጿል።
የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይፉ ዋናቃ በመክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ የአንጀት ጥገኛ ትላትል በህጻናት ላይ የሚያደርሰው የጤና ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳዩ በመንግሥት በኩል ትኩረት በማግኘቱ ከመደበኛው በተጨማሪ በዘመቻ የመድሃኒት እደላ ይካሄዳል ብለዋል።
በመድሃኒት እደላ ብቻ በሽታው አይጠፋም ያሉት አቶ ሰይፉ፤ የግልና የአካባቢ ንጽህናን ማጠናከር በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በዞኑ ህጻናት ላይ በሽታው ያሳደረው ጫና በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጠንቶ መሻሻል አሳይቷል ያሉት ኃላፊው፤ በ2018 ዓ.ም መስከረም ወር ጀምሮ ከዞኑ 18 የወረዳ መዋቅሮች ውስጥ በመከላከል ስራ ውጤታማነት ጥናት ሪፖርት መሰረት 6ቱ ከዘመቻ ውጪ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
እንደ ጋሞ ዞን በ18 የወረዳ መዋቅር ለሚገኙ ከ5-14 እድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ 470 ሺህ ህጻናት የአንጀት ጥገኛ ትላትል ማጥፊያ መድሃኒት በዘመቻው ተደራሽ ይደረጋል።
ለዚሁ አገልግሎት በተራድኦ የሚታደለው የአንጀት ጥገኛ ትላትል ማጥፊያ መድሃኒት ለታለመለት አላማ ብቻ በማዋል የጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት አቶ ሰይፉ፤ ዘመቻው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ዞኑ የድጋፋዊ ክትትል ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የመድሃኒት እደላው በትምህርት ቤት ጊቢ በስፋት ስለሚሰጥ የጤና ሴክተር ከትምህርት ሴክተር ጋር በቅንጅት ለመስራት ቅድመ ዝግጅት መደረጉም በመድረክ ተገልጿል።
የዘመቻው አላማ መደበኛ የመከላከል ስራውን ማጠናከር በመሆኑ በስልጠናው ላይ ከዞኑ 18 መዋቅሮች የተገኙ የጤና፣ የትምህርት፣ ሴቶችና ህጻናት አመራሮች እና ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በመድረኩ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ፕሮግራምን የተመለከተ ሰነድ ቀርቦ ተሳታፊዎች በዘመቻው ሴክተሩ የጣለውን ግብ ለማሳካት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለማስቀረት የቅድመ ማህጸን በር ካንሰርንና ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ያሉትን ምርመራዎች ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የአርባምንጭ ደምና ህብረህዋስ ባንክ በ2017 በጀት አመት ከ6 ሺህ 378 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ
ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት