“ዓላማ የሌለው ሰው መድረሻውን አያውቅም” – አቶ ተሰማ አለማየሁ

“ዓላማ የሌለው ሰው መድረሻውን አያውቅም” – አቶ ተሰማ አለማየሁ

በካሡ ብርሃኑ

ሠላም ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን! እንደምን ከረማችሁ? ዛሬም እንደተለመደው የአንድ ባለታሪክን የሕይወት መንገድ ልናካፍላችሁ ወደናል፡፡ ባለታሪካችን አቶ ተሰማ አለማየሁ ይባላሉ፡፡ ውልደታቸው በ1962 ዓ.ም በቀድሞ አጠራር አርሲ ክፍለ-ሃገር፤ በአሁኑ ምሥራቅ አርሲ ዞን ውስጥ በምትገኝ ጢቾ በምትባል የገጠር ከተማ ገርጊዳ ቀበሌ ነው፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ገርጊዳ በሚገኝ ‹‹ሀሰን ኡስማን›› የሚባል ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ጢቾ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡

ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ያለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ወደ ናዝሬት/አዳማ በማቅናት አፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት በመከታተል በ1981 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነዋል፡፡

በፈተናው ያመጡትን ውጤት ተከትሎ አምቦ እርሻ ኮሌጅ በመግባት ለሁለት ዓመታት ያህል የእፅዋት ሳይንስ ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀው የሥራ ዓለምን ተቀላቅለዋል፡፡

በ1983 ዓ.ም በቀድሞ አጠራሩ ዳሎቻና ላንፉሮ አውራጃ የልማት ጣቢያ ሠራተኛ በመሆን የጀመሩት ሥራ ከግብርና ባለሙያነት ጀምሮ የተለያዩ ደረጃዎችን አልፎ እስከ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ለ18 ዓመታት አገልግለዋል፡፡

በ2001 ዓ.ም የመንግስት ሥራ በመልቀቅ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት/NGO በመቀላቀል ህዝብን የሚጠቅም ሥራ ለአራት ዓመታት መሥራታቸውን የሥራ ማስረጃዎችን በማንሳት አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሃል ዕድገት የዘር ብዜትና አምራች ዩኒየን በ2002 ዓ.ም መመስረቱን ተከትሎ የሥራ ቦታውን እሳቸው የሚሰሩበት መሥሪያ ቤት ግቢ ሲያደርግ እሳቸውም ሙያዊ ድጋፍና ምክር በመስጠት አጋርነታቸውን ማሳየት ጀመሩ፡፡

በኋላም ያላቸውን ልምድ በማጋራት የጀመሩት እገዛ ወደ ተቀጣሪነት ተሸጋግሮ የምርትና ግብይት ክፍልን በኃላፊነት መምራት ጀመሩ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን መንግስታዊ ባልሆነው ድርጅት (Self Helep Africa) ውስጥ የነበራቸውን ሥራ አላቆሙም፡፡ ነገር ግን ዩኒየኑ የእሳቸውን የበለጠ ትኩረትና እገዛ በፈለገበት ወቅት ሥራውን አቁመው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ማገልገል ጀመሩ፡፡

በቀለም ትምህርታቸው ጎበዝ እንደነበሩ የሚያስታውሱት ባለታሪካችን አይን አፋር ከሚባሉ ልጆች መካከልም ተጠቃሽ እንደነበሩ ያወሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከትምህርት ቤት መልስ የተለያዩ የእርሻ ሥራዎችን በመሥራት ቤተሰብን በማገዝ ነበር ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት፡፡

ምንም እንኳን የግብርና ሥራ እየሰሩ ቢያድጉም ተምረው በዚሁ ሙያ ተመርቆ የመሥራት ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ይልቅ ከማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች መካከል የንግድ ሥራ አስተዳደር (Business Administration) ወይም የሂሳብ አያያዝ (Accounting) ማጥናት ነበር ፍላጎታቸው፡፡

ይሁን እንጂ እሳቸው ያሰቡት ቀርቶ በአምቦ እርሻ ኮሌጅ የጀመረው የግብርና ዘርፍ ትምህርት ወደ አለማያ ዩኒቨርስቲ እንዲዘልቁ አድርጎ በእፅዋት ሳይንስ (Plant Science) በዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ይህም የነበራቸው የሥራ ትጋት ላይ ታክሎ ህዝብና መንግስትን ያለመታከት ለ18 ዓመታት ያህል እንዲያገለግሉ እንዳደረጋቸው ወደኋላ መለስ ብለው በማስታወስ አጫውተውናል፡፡

የሥራ ዓለምን በ1983 ዓ.ም ሲቀላቀሉ ከነበረው ወቅታዊ ሁኔታና የባለሙያ እጥረት የተነሳ አንድ ባለሙያ እስከ 11 ቀበሌያት ተዘዋውሮ ይደግፍበት የነበረው ጊዜ የሥራ ዓለም ከባዱ ፈተና እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሥራ የሚሰራው የመጓጓዣ አማራጩ ከተገኘ ብስክሌት አልያም በቅሎ፣ ካልሆነ ግን በእግር ጉዞ መሆኑ አድካሚ ነበር፡፡

ነገር ግን በወቅቱ የተመዘገበውን ውጤት ተከትሎ የተሰጠን ዕውቅናና ሽልማት ችግሩን እንድንረሳ አድርጎናል ሲሉም ያስታውሳሉ። ‹‹ለዚህ ስኬት ያበቃኝ ሥራ ከጀመርኩ ዳር ሳላደርስ ማቆም አለመውደዴ›› ነው የሚሉት አቶ ተሰማ፤ ይህን ለማድረግ ግን ትዕግስትና ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

የሥራ ላይ እልኸኝነት (ሳልጨርስ አላቆምም የሚለው) የራሴ ባህሪ በብዙ መንገድ አግዞኛል፡፡ አብዛኛው ሥራዬ ከአርሶ አደሩ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ እነሱን መጥቀም ያስቻለ ሥራ ሰርቻለሁ ብዬ አስባለሁ›› ሲሉ የነበራቸውን የሥራ ላይ ባህሪ አጫውተውናል፡፡

‹‹ከአርሶ አደሩ ጋር እነሱን መስሎ መሥራት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ጠቅሞኛል። የፈጠርኩት ቤተሰባዊ የሆነ ግንኙነት የምነግራቸውን ነገሮች በቀላሉ ተቀብለው እንዲተገብሩ አድርጓል፡፡ ይህም በወቅቱ ለመጣው ውጤት የራሱን በጎ አስተዋፅኦ አበርክቷል›› ሲሉም የመሰረቱት ሰላማዊ ግንኙነት እንደጠቀማቸው ያነሳሉ፡፡
ከሰሩባቸው የተለያዩ መስሪያ ቤቶች በመነሳት ሰዎች የሥራ ቦታ መቀየርና ሁለገብ ሆኖ መሥራትን መፍራት እንደሌለባቸው ተከታዩን ሃሳብ በማንሳት መክረዋል፡-
‹‹ሰዎች የሚሰሩትን ሥራ ጠንቅቆ ከማወቅ ጎን ለጎን ሁለገብ በመሆን መሥራት ዘርፈ-ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ምክንያቱም ሥራዎችን ከመንግስት መሥሪያ ቤት በተለየ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የግል ድርጅቶች ጀምሮ አንዱ ከሌላው በተለየ በቀላሉ ሥራዎችን የሚሰሩበትን መንገድ ማወቅ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡

“እኔ እንደ ግለሰብ በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆነ እና አሁን በምሰራበት ዩኒየን የተለያየ የሥራ ልምድ መቅሰሜ ነገሮችን የማይበት መንገድ የተለየ እንዲሆን አድርጓል፡፡
“ይህም ከሦስቱም መስሪያ ቤቶች ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን በማጉላት ውጤታማ እንድሆን አግዞኛል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የውስጥ ፍላጎትና ተነሳሽነትን ይጠይቃል። በአጠቃላይ ሁለገብ ሆኖ መሥራት ጥቅሙ ብዙ ነውና ሰዎች ቢሞክሩት መልካም ነው›› ሲሉ ይመክራሉ፡፡

በእነዚህ የስራ ዓመታት ውስጥ ከሰሯቸው ሥራዎች በተለየ እንደ ትልቅ ስኬት የሚያነሱት ምንድን ነው ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ተከታዩን መልስ ሰጥተዋል፡-
‹‹እንደ ስኬት የማየው አሁን የምሰራበት ተቋም (ዕድገት የምርጥ ዘር ብዜትና አምራች ዩኒየን) ሲመሰረት አርሶ አደር እንዴት ዘር ያባዛል? አይቻልም! የሚል የተሳሳተ አመለካከት ነበር፡፡ ይህን የሚሉት በምርምር ጣቢያዎች የሚሰሩ ባለሙያዎችን ጨምሮ ትልቅ የሚባሉ ሰዎች መሆናቸው ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ አድርጎት ነበር፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ሰብረን ዛሬ ምርምሮችን ጨምሮ አርሶ አደሩ የእኛን ዘር ሲፈልጉ ማየቴ ለእኔ ትልቁ ስኬት ነው ማለት እችላለሁ፡፡

‹‹ዕድገት የዘር ብዜትና ግብይት ህብረት ሥራ ዩኒየን የሚያሰራጨው ዘር አሁን ላይ ከአካባቢው አርሶ አደር አልፎ እንደ ሃገር በተለያዩ አካባቢዎች ተፈላጊነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥራት፣ ተመጣጣኝ ዋጋ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ መሆን አግዞናል፡፡
በዚህም ዩኒየኑ ሲመሰረት የነበረውን 146 ሺህ ብር ካፒታል በማሳደግ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህ የሚያሳየው የአይቻልምን አስተሳሰብ በመርታት መቻላችንን በተግባር ማሳየት በመቻላችን የመጣ በመሆኑ ሁሌም እንደ ስኬት የማነሳው ነው›› ሲሉ በልበ-ሙሉነት አንስተዋል፡፡

ዛሬ በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት ዩኒየን የክልሉን 25 በመቶ የዘር ፍላጎት መሸፈን የሚያስችለው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከ1 ሺህ 200 ሄክታር በላይ ማሳ በመሸፈንም በዓመት ከ15 እስከ 20 ሺህ ኩንታል ዘር ማዘጋጀት ይችላል፡፡

በዚህም ዩኒየኑ በአስተማማኝ ሁኔታ ሥራውን የሚሰራበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚሉት ባለታሪካችን አቶ ተሰማ፤ ካለው 46 ሚሊየን የገንዘብ ካፒታል በተጨማሪ 15 ሺህ እና 7 ሺህ ኩንታል መያዝ የሚችሉ ሁለት መካዘኖች፣ 3 ዘር ማዘጋጃ ማዕከላት፣ አንድ ላቦራቶሪ፣ 1 ኤፍ.ኤስ.አር የጭነት እና 1 ፒካፕ መኪና፣ 1 ትራክተር፣ 1 የዘር መዝሪያ ማሽን እና 1 የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን አፍርቷል፡፡ ይህም በጥረት የመጣ በመሆኑ ከዚህ በተሻለ ለማሳደግ እንድንተጋ አድርጎናል ይላሉ፡፡

ባለታሪካችን በ1992 ዓ.ም በመሰረቱት ትዳር ሁለት ልጆች ማፍራት የቻሉ ሲሆን ሁለቱም ዩኒቨርስቲ በመግባት የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ሁሉ የሕይወት ውጣ ውረድና ጉዞ ውስጥ መምህርት የሆኑት ባለቤታቸው እገዛ የላቀ መሆኑን ‹‹ያለ እሷ ድጋፍ እዚህ መድረስ አልችልም›› ነበር ሲሉ አንስተዋል፡፡

ከባለቤታቸው ጋር ያለው መተሳሰብ ለልጆቻቸው ስኬት መሠረት ሆኖ ሴት ልጃቸው ጎንደር ዩኒቨርስቲ በመግባት የጤና (ሕክምና) ባለሙያ ለመሆን እየተማረች ነው፡፡ ወንዱ ልጃቸው በተመሳሳይ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በማቅናት በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቱን እየተከታተለ ነው።
በሕይወት ዑደት ውስጥ የሚገጥሙ ፈተናዎች ለማለፍ ዋናው ነገር ዓላማን አስቀድሞ መሥራት ነው የሚሉት አቶ ተሰማ፤ ከየት ተነስቼ የት ነው መድረስ የምፈልገው የሚለውን ማወቅ ለስኬት ያግዛል ይላሉ፡፡

ምክያቱም ዓላማ የሌለው ሰው ወዴት መሄድ እንደሚፈልግ መንገዱን እንደማያውቅ ይቆጠራል ሲሉም በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡ ወዴት እንደሚሄድ መንገዱን በጊዜ ያላወቀ ሰው ደግሞ መዳረሻ የለውምና ልፋቱ ከንቱ ይሆናል፡፡
በመሆኑም በግልም ሆነ በሥራ ዓለም ግልፅ ዓላማ አስቀምጦ መንቀሳቀስ ለስኬት እንደሚያበቃ እኔ ምስክር ነኝና ከእኔ ተማሩ ሲሉ ባስተላለፉት መልዕክት እኛም ተሰናበትን፡፡ ቸር ይግጠመን!