“ምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው” – መሊቅ የስልጤ የገበሬዎች ሕ/ሥራ ዩኒየን
በደረጀ ጥላሁን
የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች የአርሶ አደሩ ምርታማነት እንዲሻሻል የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን እና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናውን ለማሳደግ እየሰሩ ከሚገኙ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየኖች መካከል በስልጤ ዞን የሚገኘውን መሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን የሥራ እንቅስቃሴ እንቃኛለን።
በስልጤ ዞን የሚገኙ 13 ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት ውስጥ የተደራጁ 3 ሺህ 101 አባላትን በማካተት በ1996 ዓ/ም የተመሰረተው መሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን፤ አሁን ላይ ወደ 86 ህብረት ሥራ ማህበራት በአባልነት በመያዝ የአባላቱን ቁጥር ከ109 ሺህ በላይ ማድረስ ችሏል፡፡ በ65 ሺህ ብር ካፒታል ሥራ የጀመረው ይህ ዩኒየን ዛሬ ላይ ካፒታሉ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን÷ ዩኒየኑ በተሰማራባቸው የሥራ መስኮች 65 ቋሚ እና 157 ጊዚያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡
የመሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ሕ/ሥራ ዩኒየን በዋናነት ለአርሶ አደሩ ምርት ማሳደጊያ የሚረዱ የግብርና ግብዓትና ላመረተው ምርት ተገቢ ዋጋ እንዲያገኝ ገበያ የመፈለግ ሥራ ይሰራል፡፡ ዩኒየኑ ከአርሶ አደሩ የተሰበሰበው ምርት በተሻለ ዋጋና ጥራት በማቅረብ ለአካባቢ ኑሮ ማረጋጊያ እገዛ ማድረጉን የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሸምሰዲን ናስር ገልጿል። በተለይም ለማህበረሰቡ፣ ለፋብሪካዎች፣ ለዓለም ምግብ ፕሮግራም።ለትምህርት ምገባ ፕሮግራም እንዲሁም ወራቤ ዩኒቨርስቲ፣ የተማሪ ምገባ ፕሮግራም እና አዳሪ ትምህርት ቤትና ማረሚያ ተቋም ከዩኒየኑ ጋር ውል በመግባት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት አርሶ አደሮች የግብርና ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ታግዘው መስራታቸው ከዩኒየኑ ከሚደርሳቸው የግብርና ግብዓት ጋር ተዳምሮ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ የአባላቱ የኑሮ ደረጃ እየተሻሻለ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የመሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ገግሰቦ ረዲ እንዳሉት ዩኒየኑ አርሶ አደሩን የሚያግዝና ምርትና ምርታማትን የሚያሻሽሉ ተግባራት ያከናወናል፡፡ ለዚህም የተሻሻሉና የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን እና አገልግሎቶችን ለአባል ማህበራት የሚያቀርብ ሲሆን ከእነዚህም የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች መካከል የአፈር ማዳበሪያ፣ ኬሚካሎች፣ የጓሮ አትክልት ዘሮች፣ ምርጥ ዘር እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የመደገፍ ሥራ ይሰራል።
የምርት ግብይት በተመለከተ ገበያው ላይ ዩኒየኑ ካልገባ ህገ ወጥ ነጋዴና ደላላ የአርሶ አደሩን ምርት ዋጋ ዝቅ አድርጎ ይገዛል፡፡ ይህን ለመከላከል ምርቱን ከአርሶ አደሩ በመግዛት እሴት በመጨመር ለተለያዩ ተቋማት የማቅረብ ሥራ ይሰራል፡፡ እንዲሁም ገበያ የማፈላለግና የሽያጭ ሥራ ይሰራል፡፡ ምርቱን ከማስተዋወቅ ባሻገር አባላቱ ባቀረቡት ምርት ልክ ትርፉ ወደ ማህበሩ እንደሚወርድ ነው ምክትል ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት በሜካናይዜሽን አገልግሎት ከሰው ጉልበት ወደ ማሽነሪ መቀየሩ ለአርሶ አደሩ ጊዜን ስለሚቆጥብለት በሌሎች ሥራዎች ላይ እንዲሰማራ ያግዛል፡፡ ጥራት ያለው ምርት እንዲመረትና በጥራት እንዲወዳደርም የሜካናይዜሽን አገልግሎት እያገዘ ነው፡፡ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዳ በመሆኑ ዩኒየኑ ኮምባይነር እና ትራክተር ጨምሮ 5 ማሽነሪ ያለው ሲሆን የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖች፣ ጋሪዎችን ለሜካናይዜሽን አገልግሎት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበነው ብለዋል፡፡
የሜካናይዜሽን ሰርቪስ ሴንተር ለሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚውል የማዕከል ግንባታ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን የደቡብ ማዕከል ጋር በመሆን ግንባታው ተጠናቆ ለሥራ ዝግጁ ሆኗል። ዓላማውም የሜካናይዜሽን ዘርፍ ችግር የሆነው የመለዋወጫ እቃዎች እጥረትን ለመፍታት ይረዳል፡፡ በዚህም የጥገና አገልግሎት መስጠት፣ ማሽነሪዎች ሲበላሹ ወደ ሌላ አካባቢ ሳይኬድ እዚሁ መስራት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል የማብቃት ሥራ መስራትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት በስፋት በመስጠት የሜካናይዜሽን ሥራውን ለማስፋፋት ያግዛል፡፡
ዩኒየኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያገለግሉ 5 ተሸከርካሪዎች አሉት ያሉት ኃላፊው የአፈር ማዳበሪያ እስከ ጣቢያ ድረስ ማጓጓዝ እንዲሁም ከክልል ጋር ውል ተገብቶ የኖራ አቅርቦት ለተለያዩ ዞኖች የማጓጓዝ ሥራ ይሰራል፡፡ ስኳርና ዘይትም በማምጣት የማሰራጨት እና ከተቋማት ጋር ውል በመግባት የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
መሊቅ ዩኒየን በጥሬው የሚቀበለውን ምርቶች እሴት የመጨመር ሥራ ይሰራል፡፡ ለዚህም 2 ወፍጮዎችን በመጠቀም ለተለያዩ ተቋማት ዱቄት ያቀርባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስድስት አይነት የእንስሳት መኖዎችን በማምረትና እሴት በመጨመር ለተጠቃሚ አርሶ አደር ያሰራጫል፡፡
ከዚህ ሌላ የእንቁላል ጣይ ዶሮ ፕሮጀክትን በተመለከተ፤ ከላይፍ ፕሮጀክት ጋር በነበረ ውል 4 ሺህ 250 ዶሮዎችን በማስገባት ሥራ ጀምሯል፡፡ ይህም የሸማቹን የእንቁላል ፍላጎት ለማረጋጋት ያስችላል፡፡ በየቀኑ 3 ሺህ 200 እንቁላል በማምረት ለገበያ እየቀረበ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ የመኖ ምርት፣ የወተት፣ የድለባ፣ የእንቁላል ጣይ፣ የቄብ ዶሮ እና የማሞከት /በግና ፍየል/ ሥራዎች በዩኒየኑ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ከኢትዮ ሊዝ ማሽነሪዎች ጋር በተያያዘ ከግብርና ሚንስቴር፣ ከፌደራል ህብረት ሥራ ኮሚሽን፣ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት እና ከክልል መስተዳድርና ከዞን አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እልባት እንዲያገኝ እየሰራ ነው፡፡ እንዲሁም የዩኒየኑ ማእከል 30 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ስላለው የአጥር ሥራ ለመስራት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ይህን ለማከናወን እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ዩኒየኑ ካለበት ቢሮ ፊት ለፊት ባለው 4 ሺህ ካሬ መሬት ላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ባለ 7 ፎቅ የአርሶ አደር ህንፃ ለመገንባት እንዲሁም በመጪዎቹ አምስት አመታት 10 ተሳቢ ተሸከርካሪዎችን ለማስገባት ማቀዱንም ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ሌላ የሮዝመሪ ምርትን በስፋት ወደ ውጪ ገበያ ለመላክ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ የተገኘ ሲሆን የሀይብሪድ /ድቅል/ ዘሮች ወይም ምርጥ ዘሮች፣ ምርት የሚያሻሽሉ ስለሆነ የዘር ብዜት ላይ ለመሳተፍ ውጥን መያዙም ተመላክቷል፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ከዩኒየኑ ጋር በርካታ ሥራዎችን መስራቱን የጠቀሱት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ዩኒየኑ የሰራቸው ሥራዎች በተቋሙ እገዛ የተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በማዕከሉ ሥራ ላይ 70 በመቶ የተቋሙ ድጋፍ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡ ከዚህ ሌላ የሰው ሀይል የማብቃት ሥራ፣ ኦፕሬተሮችን የማሰልጠን፣ የሂሳብ ሥራ፣ ቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት፣ በፕሮጀክት አዘገጃጀት ላይ ባለሞያዎችን ከማብቃት አንፃር እገዛ አድርገዋል፡፡ በሀሳብ ጭምር ክትትልና ሁሉ አቀፍ ድጋፍ በማድረግ በገንዘብ የማይተመን ስራ እንደሰሩ ገልጸዋል።
አቶ ኡመር አብደላ የመሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን የሜካናይዜሽን ክፍል ሀላፊ ናቸው፡፡ ዩኒየኑ የአርሶ አደሩ እንደመሆኑ የማምረት ዘይቤውን ለማሻሻል እና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የሜካናይዜሽን ሥራ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል። ለዚህ ሥራ የሚሆን የተለያዩ ማሽነሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው አርሶ አደሩ በእነዚህ መሳሪያዎች በመታገዝ ምርትን ከብክነት በመጠበቅ ጉልበቱንና ጊዜውን ጠብቆ እየሰራ ይገኛል፡፡
አርሶ አደሩ በመሳሪያዎቹ የመጠቀም ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ያነሱት የክፍል ሀላፊው ከዋጋና ከጊዜ ጋር ሲነፃፀር ማሽነሪው በአጭር ሰዓት ብዙ ስለሚሰራ ተመራጭ ነው፡፡ የዩኒየኑ ዓላማም በተመጣጣኝ ዋጋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስለሆነ የአርሶ አደሩን አቅም ያገናዘበ በመሆኑ ተመራጭ ነው ብለዋል፡፡
ዩኒየኑ ያሉት ማሽነሪዎች በቂ ባለመሆናቸው በቀጣይ ተጨማሪ ማሽን የሚያስፈልግ ቢሆንም ከዚያ በፊት ግን ማእከሉ የሰው ሀይል የማሟላትና ሌሎች ቀሪ ሥራዎች የማጠናቀቅ ሥራ በመስራት ወደ ተግባር ለማስገባት እየተሰራ ነው፡፡ የዩኒየኑ ማዕከል በሙሉ አቅም ሲሰራ አጎራባች ዞኖችም በማዕከሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አቶ አብዱልዳኢም አህመድ የመሊቅ የስልጤ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግ በተሰራው ሥራ አምና አርሶ አደሮች ትራክተርና ኮምባይነር በመጠቀም ውጤታማ ሥራ መሰራቱንና ለምርቱም ገበያ የማመቻቸት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት በአግሪሀብ በኩል ሥልጠና በንግድ ሥራ ክህሎት ከደረጃ 1 እስከ 3 በመስጠት እንዲሁም የሂሳብ መዝገብ አያያዝ በተመለከተ በሶፍት ዌር በመታገዝ እንዲሰራ ከፍተኛ እገዛ ያደረገ ሲሆን አሁንም ከዩኒየኑ ጋር አብሮ እየሰራ ይገኛል፡፡
More Stories
በጉድለት ያልተገደበ
አጎቴና የእኛ ሰፈር ጠንቋይ
“የትምህርት ሥራ ውጤቱን ለማየት ረጅም ጊዜ ይፈልጋል” – ዶ/ር ኤፍሬም ዘለቀ