በጉድለት ያልተገደበ
በአለምሸት ግርማ
የሰው ልጅ ትልቁ ችሎታው የሚለካው ባስገኘው ውጤት ብቻ ሳይሆን፤ አንድን ነገር ለማከናወን ባለው በራስ መተማመንና ጥንካሬ ነው። በራሱ የሚተማመን ሰው ቢወድቅ ይነሳል፤ ሌላ የተሻለ አማራጭ በመሞከርም ስኬትን ለማግኘት ጥረት ያደርጋል።
በተለይም ደግሞ አካል ጉዳት ለአንዳንዶች የጥገኝነት ሰበብ በሆነበት በዚህ ጊዜ ራስን ለመለወጥ የሚጥር ሲገኝ ደግሞ የበለጠ ያስደስታል፡፡ በዚህ መነሻ አካል ጉዳተኛ ቢሆኑም መስራት እንደሚችሉ በማመንና ወደ ስራ በመሰማራት ውጤታማ የሆኑም ብዙዎች ናቸው።
የዛሬው የችያለሁ ዓምድ ባለታሪካችንም ከእነዚህ ዓይነት ጠንካራ ሰዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ከፊታቸው የሚነበበው በራስ መተማመን ከራሳቸው አልፎ ለሌላም የሚተርፍ ነው።
አቶ ተስፋዬ አለሙ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በሰሜን ወሎ አካባቢ ነው፡፡ ልጅ ሆነው እንደማንኛውም ልጅ ተጫውተው ቦርቀው ነው ያደጉት። የልጅነት ሩጫቸው ግን በገጠማቸው አካል ጉዳት ምክንያት እንደቀድሞው ሊቀጥል አልቻለም።
አካል ጉዳቱ የገጠማቸው ከጊዜ በኋላ የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊ ልጅ እያሉ መሆኑን አጫውተውናል፡፡ ቤተሰብም የገጠማቸውን ችግር ችላ አላለም፡፡ ችግሩ በአንድ ጊዜ የተከሰተ ሳይሆን ቀስ በቀስ እየተጠናከረና እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ህመሙ ሲጀምራቸው ቀለል ያለ ህመም መስሏቸው ነበር፡፡ እንደ ብርድ ያደርጋቸው ስለነበር የተለያየ ባህላዊ ህክምና ያደርጉላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ህመማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጣ እንጂ ምንም ለውጥ ማሳየት አልቻለም።
በዚሁ ህመም ምክንያት የሚወዱትን ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ሲማሩ አካላቸው ጤናማ ነበረ። ከስምንተኛ ክፍል በኋላ ግን በሁለቱም እግሮቻቸው ላይ በተከሰተ ህመም መንቀሳቀስ አልቻሉም።
በዚህም ምክንያት ሙሉ ጊዜያቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቤት ውስጥ ለማሳለፍ የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጠረ። ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ ዓመታት ተቆጠሩ። ቤተሰቦቻቸው በልጃቸው መፍትሔ አለማግኘት ማዘናቸው እረፍት የነሳቸው አቶ ተስፋዬ በወቅቱ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ውሳኔ ወሰኑ።
በውሳኔያቸው መሰረት በ1995 ዓ.ም የትውልድ ቀያቸውን ለቀው ወደ ሃዋሳ ከተማ መጡ፡፡ ወደ ሃዋሳ በመጡበት ወቅት የተለየ ነገር ገጥሟቸው እንደሆነ ጠይቀናቸው እንዲህ በማለት መልሰውልናል፦
በትውልድ አካባቢያቸው ስለ አካል ጉዳት ብዙም ግንዛቤ አልነበረም፡፡ ይልቁንም አካል ጉዳት እንደ እርግማ ተደርጎ ይወሰድ ስለነበር በዚያ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ይሳቀቁ ነበር። የቤተሰቦቻቸውን መሳቀቅ የተገነዘቡት አቶ ተስፋዬ አማራጭ ብለው ያሰቡት ከቤተሰቦቻቸው ራቅ ብሎ መኖርን ነበር፡፡
“በመጣሁበት ወቅትም ከቤተሰቦቼ ናፍቆት በስተቀር ምንም የገጠመኝ ችግር አልነበረም። ይሁን እንጂ የቤተሰቦቼን ሰቆቃ አለማየት ዓላማዬ ስለነበር የሚገጥመኝን ነገር በትዕግስት ለመወጣት ወስኜ ነበር›› ሲሉም በትውስታ አጫውተውናል፡፡
ሃዋሳ ሲመጡ የ18 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ ሲመጡ ያገኙት መረጃ “ማዘር ትሬዛ” የሚባል ድርጅት ወላጅ ለሌላቸው ወገኖች ድጋፍ እንደሚያደርግ ነበር፡፡ ባገኙት መረጃ መሰረት ወደ ድርጅቱ አቀኑ፡፡ ድርጅቱም በሩን ከፍቶ ተቀበላቸው፡፡ በድርጅቱ ለመግባት በሚያስችሉ መስፈርቶች መሰረት የሚያስጠጋ ዘመድ ስላልነበራቸው በድርጅቱ ውስጥ የመኖር ዕድሉን አገኙ፡፡ በማዕከሉ ለሚኖሩ ሰዎች የመኖሪያ፣ ምግብ፣ የተለያዩ የህክምና አገልግሎትና የሙያ ስልጠናዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ እሳቸውም በቆይታቸው የልብስ ስፌት ስልጠና ማግኘት ችለዋል፡፡
በማዕከሉ ውስጥ ለአምስት ዓመታት ቆይተዋል። በነበራቸው ቆይታም በርካታ የህይወት ተሞክሮዎችን መቅሰማቸውን ይናገራሉ። በማዕከሉ ህግና ደንብ መሰረት ሰዎች በቆይታቸው በጤናቸው ለውጥ ሲያመጡና መስራት ሲችሉ ከማዕከሉ እንዲወጡ ይደረጋል። በምትኩ ሌላ አዳዲስ ሰዎች ይተካሉ። በህጉ መሰረት የእሳቸው የመውጫ ጊዜያቸው ሲቃረብ ራሳቸውን ማዘጋጀት ጀመሩ።
ባደረጉት ዝግጅት በራሳቸው ዕቅድ ከድርጅቱ የመውጣት ዓላማ ሰነቁ፡፡ በዓላማቸው መሰረት ሁኔታዎችን በማመቻቸትና ስነ-ልቦናቸውን ዝግጁ በማድረግ ከማዕከሉ ለቀቁ። ቀደም ሲል ስለቸሻየር ኢትዮጵያ ሃዋሳ ቅርንጫፍ መረጃው ስለነበራቸው በቀጥታ ወደ ማዕከሉ በመሔድ ባለሙያዎችን አነጋገሩ፡፡
በወቅቱ ለነበሩ አካላት የልብስ ስፌት ሙያ ልምድ እንዳላቸው አስረዱ፡፡ ስለሁኔታው የተረዱት የቸሻየር ሰራተኞች መስራት የሚችሉበትን የልብስ መስፊያ ማሽን ገዙላቸው፡፡ በዚያም እየሰሩ ራሳቸውን የማስተዳደር ኃላፊነትን አሃዱ ብለው ጀመሩ፡፡ ቸሻየር ኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የተለያየ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፥ እሳቸውም የስልጠና፣ የአካል ድጋፍ፣ የገንዘብ ብድር የመሳሉትን ድጋፍ አግኝተዋል።
ባገኙት የገንዘብ ብድር ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በማሟላት መስራት ጀመሩ። ስራውን ይወዱት ስለነበር ለመላመድ ምንም አልተቸገሩም። በስራቸው ደስተኛ እንደነበሩና በደንበኞቻቸው በቀላሉ ተቀባይነትን እንዳገኙ አጫውተውናል።
ስራቸው እየተጠናከረ ሲመጣ በ2004 ዓ.ም ትዳር የመሰረቱ ሲሆን ከትዳር አጋራቸው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የትዳር አጋራቸው የአካል ጉዳት አልባ የተገናኙትም በእሳቸው መልካምነት መሆኑን አስረድተውናል፡፡ በእርግጥ አብረው እንዳይሆኑ ብዙዎች ጫና ሲያደርጉ እንደነበር ቆየት ብለው ቢሰሙም፥ በትዳራቸው ላይ የሌሎች ተፅዕኖ እንዳይኖር ያደረጉትን አጋራቸውን አመስግነዋል።
ባለቤታቸው በኮምፒውተር ዘርፍ ከቴክኒክና ሙያ ቢመረቁም ስራ ባለማግኘታቸው ከተማሩበት ውጭ በሆነ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን፥ በትዳራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በራሳቸው መስራት ከጀመሩ አስር አመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፥ በሙያቸው በርካታ ደንበኞችን አፍርተውበታል፡፡ አብዛኛዎቹ የረጅም ጊዜ ደንበኞቻቸው መሆናቸውንም አጫውተውናል፡፡
ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ስራው መቀዛቀዝ እያሳየ ቢሆንም ስራቸውን በመስራት ልጆቻቸውን እያስተማሩ፣ ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ። ለስራ የሚንቀሳቀሱበትን ባለሶስት እግር ሞተር ሳይክልም መግዛት ችለዋል።
የወደፊት ዕቅዳቸውን ጠይቀናቸው እንዲህ ሲሉ ነበር ያጫወቱን፦
“ቢሆንልኝ የራሴን ስራ ማጠናከር እፈልጋለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ቤት ለመከራየትና አዲስ የልብስ ስፌት መኪና ለመግዛት ደህና ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ዘመናዊ ማሽን በመግዛት ተጨማሪ ሰራተኛ ቀጥሬ አስፋፍቼ ብሰራ ደስ ይለኛል፤ ካልሆነም ደግሞ ወደ ንግዱ የመግባት ፍላጎትም አለኝ፡፡ ንግድ ሲባል ብዙ ሰዎች የሚያስቡት ሸቀጣ ሸቀጥን ነው። እኔ ግን የተለያዩ ነገሮችን በመነገድ ራሴን ማሻሻል ነው ፍላጎቴ፡፡ እሱም ትንሽ አቅም ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚሳካልኝ በማመን ነው ዓላማ ያደረኩት፡፡”
ከአካል ጉዳታቸው ጋር የተለየ ገጠመኝ እንደሌላቸው ያጫወቱን አቶ ተስፋዬ በአቅራቢያቸው ያሉ ሰዎች በሁሉም ነገር እንደሚደግፏቸው አንስተዋል፡፡ ጓደኞቼ የተለያየ ነገር ገጠመኝ ሲሉ አደምጣለሁ፤ እኔ ግን ይሔ ነው የሚባል ነገር ገጥሞኝ አያውቅም ይላሉ፡፡
ትምህርታቸውን እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ቢከታተሉም፤ በአካል ጉዳታቸው ምክንያት ከዚያ ለማለፍ ግን አልቻሉም፡፡ በዚህም በራሳቸው ያላሳኩትን በልጆቻቸው ለማየት ተግተው እያስተማሩ ይገኛሉ።
ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙት አቶ ተስፋዬ፤ ለቤተሰባቸው ሶስተኛ ልጅ ናቸው፡፡ በልጅነታቸው ቤተሰቦቻቸውን አቅማቸው በፈቀደው መጠን ያግዙ ስለነበር ጉዳቱ ከደረሰባቸው በኋላ ግን እንደቀድሞው መስራት ስላልቻሉ ቤተሰቦቻቸው በሁኔታው ማዘናቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ነገር ግን አዝነው ብቻ አልተቀመጡም፤ ይልቁንም ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ዕረፍትን የሚሰጥ ውሳኔ ወሰኑ። እችላለሁ ብለው በማመናቸው ህይወታቸውን በራሳቸው መምራት ችለዋል። ቤተሰቦቻቸው ሲረበሹ እሳቸውም ይረበሹ እንደነበር በማስታወስ ሁኔታው በመደጋገሙ ራቅ ለማለት መወሰናቸውን ውሳኔያቸው ዛሬ ላሉበት ሁኔታ መነሻ እንደሆነም ይናገራሉ።
“በቸሻየር መመሪያ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም፡፡ ስለዚህ ማንም አካል ጉዳተኛ ጉዳቱን እንደመጠቀሚያ ወይም ከሌሎች ጥቅም ማግኛ አድርጎ መውሰድ የለበትም፡፡ ቢሰሩ ራሳቸውን ከመጥቀም አልፈው ሀገርን ሊጠቅሙ ይችላሉ፡፡ ጥቂቶች በሚሰሩት የተሳሳተ ስራ ለሁሉም አካል ጉዳተኛ ስም ይሰጣል፤ ስለዚህ አካል ጉዳተኛ ቢሆኑም የሚችሉትን ስራ በመስራት መለወጥ ይችላሉ” በማለትም ነው ምክራቸውን የለገሱትን፡፡
በአካል ጉዳተኝነታቸው ሳይገደቡ በመማር፣ እንዲሁም ስራ በመፍጠር ለብዙዎች ምሳሌ የሆኑ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ አቶ ተስፋዬም ከእነዚህ መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህም ጠንካራ ተሞክሮ ያላቸውን ግለሰቦች ህይወት በመመልከት ብዙዎች ሊማሩ ይገባል መልዕክታችን ነው፡፡
More Stories
“ምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው” – መሊቅ የስልጤ የገበሬዎች ሕ/ሥራ ዩኒየን
አጎቴና የእኛ ሰፈር ጠንቋይ
“የትምህርት ሥራ ውጤቱን ለማየት ረጅም ጊዜ ይፈልጋል” – ዶ/ር ኤፍሬም ዘለቀ