አጎቴና የእኛ ሰፈር ጠንቋይ

አጎቴና የእኛ ሰፈር ጠንቋይ

በአንዱዓለም ሰለሞን

ልጅ ሆነን ትምህርት ቤት የተከራከርንበት አንድ ርዕሰ ጉዳይ ትዝ ይላችኋል? “ከገንዘብ እና ከእውቀት የቱ ይበልጣል?” በሚል በሁለት ጎራ ተከፍለን፣ አንዱ አንደኛውን ወገን ለማሳመን ሀሳብ ያንሸራሸረበት?

በእርግጥ ነገሩ በወቅቱ ሀሳብ ለማፍለቅ ብሎም ሀሳባችንን ለመግለጽ የሚያስችለንን ክህሎት ለማዳበር ጠቅሞን ይሆናል፡፡ ከዚያ ባሻገር ግን አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ክርክሩ ጉንጭ ማልፋት ነው፡፡ ለምን ካላችሁኝ፣ ሁለቱም ለህይወታችን ወሳኝና አስፈላጊ ነገሮች ናቸውና፡፡ እዚህ ላይ “ኑሮ ማፕ” ከሚለው የዶክተር ኤርሲዶ ለንዴቦ መጽሀፍ ላይ ያገኘኋትን አንድ ሀሳብ ባነሳ ወደድኩ፡-
“ሁሉም ነገርና ማንኛውም መስተጋብር፤ በተፈጥሮ የየራሱ ልክ አለው፡፡ በልካቸው መጠን በተመጋጋቢነት ሊያድጉ ይችላሉ። አንዱ ነገር ለብቻው ከሌሎቹ ልክ አልፎ ሲሔድ ወይም ሲጎድል፤ ያኔ የማያንቀሳቅስ ገዳቢ ምህዋር ይፈጠራል፡፡

“ለምሳሌ፤ ሙያ ማዳበርን ቸል ብለህ፤ ብር መቆጠብ ላይ ብቻ ብትተጋ እድገትህ አይፋጠንም፡፡ ሙያና ገንዘብ፤ እርስ በእርስ የተሳሰሩ ‹የአንድ ሲስተም ሁለት አካላት ወይም ፈርጆች ናቸው› አንዱን ፈርጅ ብቻ በቁንጽል እያየን፣ የዛሬዋን ቅጽበት ብቻ እየተመለከትን የምንጓዝ ከሆነ ስኬታማ ልንሆን አንችልም፡፡

“በቁጠባ ገንዘብ ባጠራቀምክ ቁጥር፤ ሀብትን በአግባቡ ቢዝነስ ላይ ለማዋል የሚያስችል ሙያም ማዳበር አለብህ – ያኔ ገንዘብና ሙያ በተደጋጋፊነት ስኬትህን ያፋጥኑልሀል፡፡ አለበለዚያ ግን ስኬትህ ይገደባል፡፡ መፍትሔው ምንድነው? አሁንም ሙያ ሳታዳብር በመዘንጋት፤ ብር መቆጠብ ላይ ብቻ ብታተኩር፤ አይሳካልህም::”

እንግዲህ ሁለቱም ነገሮች አስፈላጊ ናቸው ለማለት ያህል ነው፡፡ እውቀት ሲባል ደግሞ ዝም ብሎ ተምሮ መመረቅ ብቻም አይደለም፡፡ መገለጫው ብዙ ነው፡፡ ማገናዘብ፣ መመርመር፣ በዲሲፕሊን መታነጽ፣ ራስን መግዛት፣ ማዳመጥና ማስተዋል የሌለበት እውቀት ባዶ ነው፡፡ አንዳንድ ዲግሪያቸውን የቤታቸው ግድግዳ ላይ በትልቅ ፍሬም የሰቀሉ፣ ግን ደግሞ የመፍትሔ ሳይሆን የችግሮች ምክንያት የሆኑ ሰዎች አልገጠሟችሁም፡፡ ውስጣቸው ባዶ የሆነ፣ ዝም ብለው እንደቆርቆሮ የሚጮሁ፡፡

አንድ መጽሀፍ ላይ ያገኘሁት አባባል እንዲህ ይላል፡-
“መማር ከመመገብ ጋር ይመሳሰላል። ብዙ መመገብህ ሳይሆን ምግቡ ምን ያህል ከሰውነትህ ጋር ተዋህዷል የሚለው ነው ቁምነገሩ፡፡”

“እውነተኛ ትምህርት ማለት ልብንና አእምሮን የሚያሰለጥን ነው” የምትለዋን አባባልም ያገኘሁት እዛው መጽሀፍ ላይ ነው፡፡

በዚህ ደረጃ እውቀት ሲዘልቅህ፣ እንደአጎቴ ትሆናለህ፡፡ ወግም አይደል የያዝኩት፤ እንግዲህ ነገሬን በጨዋታ እያዋዛሁ ልቀጥል፡-
አጎቴ ተወልደን ባደግንበት ከተማ የሚኖር የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ነው፡፡ አሁን የማጫውታችሁ ታሪክም በስራ ዘመኑ ካጋጠሙት ነገሮች አንዱን ነው፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ ሰዎች የተለየ መልክ ያላቸው ዶሮዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ወይ ሙሉ ነጭ፣ ወይ ድፍን ጥቁር፣ ገብስማ ወዘተ፡፡ ይህን የሚፈልጉት ጠንቋይ ቤት ሔደው፣ ጠንቋዩ ባዘዛቸው መሰረት ነው፡፡

አንድ ጊዜ ታዲያ እንደዚህ ሆነ፡-
አንድ ሰው ሙሉ ነጭ የሆነ ዶሮ ፈልጎ አጎቴ ዘንድ መጣ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ አጎቴ ያሉት ነጭ ዶሮዎች ትንሽ ጥቁር ጣል ጣል ያደረገባቸው ነበሩ፡፡ አጎቴ በመሀል አንድ ሀሳብ ብልጭ አለለትና ወደጓሮ ሄደ፡፡ አንደኛውን ነጭ ዶሮ አንስቶ ጥቁሩን ላባ ነጭቶ ከጣለ በኋላ ለሰውዬው አምጥቶ ሰጠው፡፡ ሰውዬውም ዶሮውን በውድ ዋጋ ገዝቶ ወደጠንቋዩ ዘንድ ሔደ እላችኋለሁ፡፡

የሚገርመው ነገር፣ ጠንቋዩ ይህን የአጎቴን ድርጊት አውቆ ለሰውዬው አልነገረውም። ስለዚህ አጎቴ፣ ተስፋና እምነቱን ለጠንቋዩ የሰጠውንም ሰውዬ፣ ጠንቋዩንም ሸወዳቸው ማለት ነው፡፡ እኔ ግን ይህን ሽወዳ አልለውም፤ ስራ ፈጠራ እንጂ፡፡

ለምን ካላችሁኝ፤ አጎቴ የሸወደው እኮ ብዙዎችን ሲያታልልና ሲያጭበረብር የነበረን ጠንቋይ ነው፡፡ ሰውዬውም ቢሆን ፈቅዶና ወዶ ራሱን ለዚህ ጠንቋይ ያስገዛ ምርኮኛ መሆኑ ነው፡፡

ነገሩን ከዚህ አንጻር ከተመለከትነው፣ አጎቴ “ስራ ፈጣሪ” መባል ብቻም ሳይሆን፣ አብዮተኛም ጭምር ነው፡፡ በአጉል ባህል አለያም በባዕድ አምልኮ አራማጆች ላይ ያመጸ አብዮተኛ፡፡

የአጎቴ ድርጊት ለእኔ፣ “መተተኛይቱ በህይወት እንድትኖር አትፍቀድላት” አለያም፣ “አስማት አታድርጉ፣ ሞራ ገላጭም አትሁኑ” እያለ ከሚሰብክ የሀይማኖት አባት ያልተናነሰ ነው፡፡

የጠንቋይን ነገር ካነሳን አይቀር በቅርቡ ፌስ ቡክ ላይ ያየኋትን አንድ ቀልድ ጀባ ብላችሁስ፡-
ሰውዬው ሚስቱን ጠረጠራትና ዕውነቱን ለማወቅ ጠንቋይ ቤት ሄደ። ጠንቋዩም፡-
“እውነቱን ለማወቅ ከፈለግህ በሚቀጥለው ሣምንት ቤትህ አጠገብ ካለው ቦታ ላይ አፈር ይዘህ አምጣልኝና እነግርሃለሁ” አለው።

ሰውዬው በቀጣዩ ሣምንት የተባለውን አፈር ይዞ ጠንቋዩ ዘንድ ቀረበ። ጠንቋዩም አፈሩን ይዞ ከራሱ ጋር ትንሽ ከተነጋገረ በኋላ እንዲህ አለው፡-
“የምነግርህን ጉድ እንዴት እንደምትሸከመው አላውቅም። ሁለቱ ልጆችህ ያንተ አይደሉም። ሴቷ ልጅህ ችግር ላይ ነች። ሚስትህ ሌላ ወንድ ይዛለች”

ሰውዬው በሰማው ነገር ከት ብሎ ሳቀ። ጠንቋዩ የሰውዬው መሣቅ ገርሞት ጠየቀው፣

“የነገርኩህ ነገር የሚያስለቅስ ነው። ምን ያስቅሃል?”

“እኔም የምነግርህን ነገር እንዴት እንደምትሸከመው አላውቅም። ከቤቴ በር ላይ ማምጣት የነበረብኝን አፈር በችኮላ ስለረሳሁት አፈሩን ያመጣሁት ካንተ በር ላይ ዘግኜ ነው!”