የቡና ግብይት ችግሮችን በመለየት ለመፍትሔዎቹ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፣ ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡናን የግብይት ሰንሰለት ችግሮችን በጥናት በመለየት መፍትሔዎችን ለማምጣት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ አሳሰቡ።
ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ያመላከታቸውን ችግሮች በመቅረፍ ቡና ለክልሉና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
በክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለሥልጣን በኤፍ ኤስ አርፒ (FSRP) ፕሮጀክት የበጀት ድጋፍ በቡና እሴት ሰንሰለት ዙሪያ በተደረገ ጥናት ውጤት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።
የዳሰሳ ጥናቱን ያቀረቡት የፕሮጀክቱ ባለሙያ ዶክተር ሀብታሙ ገብረሥላሴ እንዳብራሩት በክልሉ በስድስት ከፍተኛ ቡና አምራች ወረዳዎች፣ አርሶ-አደሮች፣ አዘጋጆችና አቅራቢዎች በተካተቱበት ጥናት ከ560 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ልማት ሽፋን ቢኖርም ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
በክልሉ የቡና ምርታማነት በአማካይ 6.8 ኩንታል በሄክታር ብቻ ስለመሆኑ አብራርተው፤ ብዙ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
ክልሉ በዓመት 54 ሺህ 795 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን ቡና ምርት ገበያ 18 በመቶ እየሸፈነ ሲሆን ፤ ይህም ካለው እምቅ አቅም አንፃር ብዙ የሚቀረው ነው ተብሏል።
በጥናቱ እንደተገለፀው፤ ከአምራች አርሶ-አደሮች መካከል 54 በመቶዎቹ ብቻ ለህጋዊ አቅራቢ ነጋዴ ምርታቸውን ይሸጣሉ።
በመሆኑም በህገ-ወጦችና በደላሎች ዋጋ ተወስኖ የሚወጣውን ቡና መግታት የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል።
በምክክሩም የቡና አልሚ ባለሀብቶች፣ አቅራቢዎች፣ ባለሙያዎችና የዘርፉ አመራሮች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ፍቅሩ በላይ- ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ እና የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዕቅድ ዙሪያ በታርጫ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው
በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመረጃ ጥራት ዙሪያ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ
የሀገሪቱን የሥጋ ምርት ጥራትና መጠን በላቀ ደረጃ ማረጋገጥ የሚያስችል ሁሉ አቀፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመረቀ