ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ እያሳደሩ ያለውን ጫና ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ አስታወቀ
በክልሉ ከሰኔ 9 ጀምሮ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተደራሽ የሚያደርገው ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች እንዲሁም የቢላሃሪዚያ እና የአንጀት ጥገኛ ትላትል መድኃኒት እደላ ማሰጀመሪያ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በጤናው ዘርፍ በተሠሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ሀላፊ አቶ መና መኩሪያ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በይበልጥ የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በተደረጉ ጥረቶች ለውጦች ተመዝግበዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ዜጎችን ለጤና ቀውስና ለሞት የሚዳርጉ የሀሩራማ በሽታዎች የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን አውስተዋል።
በይበልጥ የሀሩራማ በሽታዎች ብሎም የአንጀት ትላትል በሽታዎች በክልሉ ዜጎች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያሳደሩ ስለመሆናቸውም አቶ መና ተናግረዋል።
በክልሉ በተላላፊ በሽታዎች ላይ በተሠሩ ጠንካራ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የሚናገሩት አቶ መና መኩሪያ፤ የሀሩራማ በሽታዎች ግን ትኩረት መነፈጋቸውንም አልሸሸጉም።
በይበልጥ በአንጀት ትላትል የሚጠቁ ህፃናት በሽታው በሚያሳድረው ጫና ከትምህርት ገበታቸው እየተስተጓጎሉ ስለመሆናቸውም አመላክተዋል።
እነዚህ ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች በክልሉ እያሳደሩ ያለውን ከፍተኛ ጫና ለመግታት የተደራጀ የመድኃኒት እደላን አጠናክሮ መስራት እንደሚገባም አፅእኖት ሰጥተዋል።
አቶ መና መኩሪያ አያይዘውም ለበሽታው መከላከል ስራው የሚሰራጨው መድኃኒት ለታለመለት አላማ ይውል ዘንድ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ከሰኔ 9 እስከ 15 ቀን 2017 ድረስ በሚቆየው የመድኃኒት እደላ እድሜያቸው ከ5 እስከ 14 የሚደርሱ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ዘጋቢ: በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በክትባት ዘመቻው 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህፃናትን ይከተባሉ-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ
የታርጫ አጠቃላይ ሆስፒታል ለተገልጋዮች የተሻለ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተገለፀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ሊካሄድ ነው