በዳዉሮ ዞን ታርጫ ከተማ የሚካሄዱ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ልማቶች አሁን ላይ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ገለጹ
በታርጫ ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ልዩ ልዩ ልማቶች በታርጫ ክላስተር የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝተዋል።
ግንባታዎቹም ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ድርሻቸው ላቅ ያለ መሆኑ ተገልጿል።
በጉብኝቱ ወቅት የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ወንድሙ እንደገለጹት፤ መንግሥት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን የታርጫ ከተማ ለኑሮ ምቹና ጽዱ እንድትሆንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የተሻለ እንዲሆን እየተሠራ ይገኛል።
የግሉ ባለሀብቶች በታርጫ ከተማ ዕድገት ላይ እያበረከቱ የሚገኙት አስተዋጽኦ ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በታርጫ ከተማ በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች ተገንብተው ለተለያዩ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ 16 የመሰብሰቢያ አዳራሾች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በቁጥር 52 የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሆቴልና ለቱሪዝም አገልግሎት እየዋሉ እንዳለም ነው ያብራሩት።
በቅርቡም በ5 ባለሃብቶች ለሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ግንባታዎች መኖራቸውንም ከንቲባው ጠቁመዋል።
የዕለቱ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና በብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢዮብ ቶማስ በበኩላቸው፤ መንግሥት በዞኑ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር በተለያዩ ጊዜያት የጋራ ውይይት በመፍጠር በታርጫ ከተማ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
መንግሥት በበኩሉ ባለሀብቶቹ በተገቢው ማልማት እንዲችሉ የሚያግዝ ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ከመሠረተ ልማት ዝርጋታና ተደራሽነት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ውስንነት ለማስተካከል የጋራ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው፤ መንግሥት የብልጽግና ጉዞን ለማረጋገጥ እንዲችል የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ላቅ ያለ ድርሻ በመኖሩ በተቀናጀ ጥረት ተግባሩ እየተከናወነ ይገኛል።
መንግሥት ምቹ ፖሊሲን በመቅረጽ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማበረታታትና ለማስፋፋት ባደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየታዩ መምጣታወንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ወደ ታርጫ ከተማ የሚመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ የሚያደርግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ልማቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በጉብኝቱ የታርጫ ከተማ የኮሪደር ልማት፣ የመሐል መንገድ መብራት ዝርጋታና በባለሃብቶች እየተገነቡ የሚገኙ ልዩ ልዩ ግንባታዎችንም ተመልክተዋል።
በመጨረሻም የማሙሽ ፔኒሲዮን ደረጃቸውን የጠበቁ በቁጥር 16 አልጋዎች ለአገልግሎት መብቃታቸውም የምልከታው አካል ነበሩ።
እነዚህ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ድርሻቸው ላቅ ያለ መሆኑም ተገልጿል።
ፔኒሲዮኑም በቀጣይ G+8 ሆኖ ግንባታው የሚጠናቀቅ ሲሆን በውስጡ ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጥ ሕንጻ መሆኑንም የፔኒሲዮን ባለቤት ወጣት ባይከዳኝ ወንድሙ ተናግሯል።
በጉብኝቱ በታርጫ ክላስተር የሚገኝ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞንና የታርጫ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሠማሩ የግል ባለሀብቶች ከመንግስት የተረኩቡትን ሀብት በተገቢው እንዲያለሙ ተጠየቀ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በማር ምርት ዘርፍ 360 ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ አስታወቁ
በስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ ለ2መቶ 50 ድጋፍ ለሚሹ አቅመ-ደካማና አረጋውያን ማዕድ የማጋራት መርሃ-ግብር ተደረገ