በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በማር ምርት ዘርፍ 360 ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ አስታወቁ
የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ከ’ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ሩራል ሪኮንስትራክሽን’ ከተሰኘ መንግሥታዊ ካልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመቀናጀት በማር ምርት ዘርፍ የወጣቶችን ተጠቃማሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ አካሂዷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍ የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸው የብድር እና መሥሪያ ቦታ ከማመቻቸት አኳያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ሊቀረፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ የወጣቶችን ሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ክልሉ ከማር ምርት ተጠቃሚ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መክረዋል።
የአይ. አይ. አር. አር. ካንቲሪ ዳይሬክተር አቶ ዘርይሁን ይልማ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው የገጠሩን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በተለይም ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን አይ ሲ ፔ እና ኦርዳ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በማር ምርት እና ተዛማጅ የሥራ ፈጠራ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት የማር ምርት መጠንና ጥራትን ለመጨመር በደቡብ ኢትዮጵያ በ18 ወረዳዎች ላይ ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ ዘርይሁን ተናግረዋል።
ለሥራው ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት አቶ ዘርይሁን፤ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ከኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ጋር የ5 ቢሊዮን ብር ብድር ስምምነት መፈራረማቸውንም ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል እና የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ሀላፊ አቶ በለጠ ሙንኤ በበኩላቸው፤ በክልሉ 360 ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማር ምርት ሥራ ላይ እንዲሠማሩ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው ባለድርሻ አካላት ለሥራው ስኬታማነት በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
በዕለቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የግብ ስምምነት የተፈረመ ሲሆን ሥራው በአግባቡ እንዲመራም አስተያየት ተሰጥቶበታል።
ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ ለ2መቶ 50 ድጋፍ ለሚሹ አቅመ-ደካማና አረጋውያን ማዕድ የማጋራት መርሃ-ግብር ተደረገ
በበዓላት ሰሞን የትራንስፖርት እጥረት፣ የታሪፍ ጭማሪና የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት እየሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ገለፀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ባደዋቾ ክላስተር በ2017/18 በበልግ የእርሻ ወቅት በክላስተር የተዘራ የበቆሎ ማሳ በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በተመራ ልኡክ የመስክ ምልከታ ተደረገ