በጋዜጣው ሪፖርተር
የዚህ ሳምንት የንጋት እንግዳችን ዶ/ር ኤፍሬም ዘለቀ ይባላሉ፡፡ የሀላባ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን ትምህርት ላይ ነው ያሳለፉት፡፡ ለትምህርት ትልቅ ጉጉት ስለነበራቸው መደበኛውን ትምህርታቸውን በመማር፣ ከዚያም ከዲፕሎማ ተነስተው እስከ ሦስተኛ ዲግሪ(phd) ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በሥራው ዓለም ደግሞ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ላይ በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ ከስርዓተ ትምህርቱ እና የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ጋር የተያያዙ ነጥቦች በማንሳት ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡- የእረፍት ጌዜዎን ሰውተው ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆኑ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡
ዶ/ር ኤፍሬም፡- እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- ከትውልድና ዕድገትዎ እንጀምር? የትምህርት ጉዞዎስ ምን ይመስል ነበር?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- ትውልድ እና እድገቴ በሀድያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ሆያዋ በምትባል የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ ትምህርቴን እስከ 5ኛ ክፍል የተከታተልኩት ሆያዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን ኢህአዴግ ሲገባ ትምህርት ቤቱ ፈርሶ ስለነበር ወደ ሀላባ ዞን በመምጣት 6ኛ ክፍልን ሙዳ ሆሎሎቃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ፡፡ ከ6ኛ ክፍል በኋላ በአቅራቢያ ትምህርት ቤት ስላልነበረ ወደ ቁሊቶ ከተማ መጥቼ ዕድገት መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትያለሁ፡፡
በ1991 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ተፈትኜ 2 ነጥብ 8 ውጤት ባመጣም ወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ስለነበር የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት በጣም ጥብቅ ነበር፡፡ ዩኒቨርስቲዎች የመቀበል አቅም የላቸውም በሚል በተላለፈው ውሳኔ ምክንያት ዩኒቨርስቲ የመግባት ከፍተኛ ጉጉት ቢኖረኝም መግባት ግን አልቻልኩም፡፡ ውጤቴ ኮሌጅ የሚያስገባ ስለነበር ተወዳድሬ ሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መማር ጀመርኩ፡፡
ከዚያም ለ2 ዓመታት ተከታትዬ 1993 ዓ.ም መመረቅ ችያለሁ፡፡ ድግሪዬን ዩኒቨርስቲ ገብቼ ለመማር ቁጭት ስለነበረኝ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ተወዳድሬ ነበር፡፡ ቀድሞ ጅማ ዩኒቨርስቲ ዕድል አገኘሁ፡፡ በክረምት መርሀ-ግብር በእንግሊዘኛ ቋንቋ በድግሪ ፕሮግራም መማር ስጀምር አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተወዳድሬ ስለነበር የጅማ ዩኒቨርስቲውን ትቼ አዲስ አበባ 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ በድግሪ ፕሮግራም በቀኑ ክፍለ ጊዜ መከታተል ጀመርኩኝ፡፡
ድጋሚ ለመመረቅ አንድ መንፈቅ ሲቀረኝ የማስተርስ ዕድል አግኝቼ እዛው 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ መማሬን ቀጠልኩ፡፡ ከዚያም በ 2000 ዓ.ም ተመረቅኩኝ፡ ፡ 2011 ዓ.ም ላይ የሦስተኛ ዲግሪ/phd ፕሮግራም ዕድል አግኝቼ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ለ5 ዓመታት ተከታትዬ 2015 ዓ.ም መመረቅ ችያለሁ፡፡
ንጋት፡- የሥራ ጅማሮዎስ እንዴት ነበር?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- በ1994 ዓ.ም ሀላባ ዕድገት ትምህርት ቤት የእንግሊዘኛ መምህር ሆኜ ተመድቤ ነው ሥራ የጀመርኩት፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ለ2 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ዲላ ዩኒቨርስቲ የእንግሊዘኛ መምህር በመሆን ለ4 ዓመታት ያህል አገልግያለሁ። በመቀጠል ሀላባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን ሆኜ ለ8 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ ሀላባ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያም ለተወሰነ ወራት ሠርቻለሁ። የሀለባ ዞን መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ ሆኜ ከሰራሁ በኋላ አሁን ያለሁበት የሀላባ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሆኜ እየሠራሁ እገኛለሁ።
ንጋት፡- የትምህርት ስብራት ሲባል ምን ለማለት ተፈልጎ ነው?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- የትምህርት ስብራት በተለያየ መንገድ ሊገለፅ ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር ትምህርት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፤ ሁሉም ተመልሶ ወደ ኋላ ቢመለከት በሁሉም ደረጃ ማለት ይቻላል ተማሪው፣ የተማሪ ቤተሰብ፣ አመራሩ፣ ርዕሰ መምህሩ እና መምህሩ ለትምህርት ይሰጥ የነበረው ቦታ ችግር ወስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው ቀደም ሲል ለጥራት ሳይሆን ቁጥር ላይ ነበር ትኩረት የሚደረገው፡፡
ተማሪን በከፍተኛ ቁጥር ከክፍል ወደ ክፍል ከማሳለፍ ባለፈ ትምህርት ቤትን በከፍተኛ ቁጥር ተደራሽ ማድረግ ነበር ዋና ትኩረት የተሰጠው፡፡ በዚህም ምክንያት 12ኛ ክፍልን አስፈትኖ ብዙ ተማሪ ወደ ዩኒቨርስቲ ማስገባት እንደ ስኬት ይታይ ነበር፡፡ የትምህርት ሥርዓት ተሻሻለ ተብሎም ትምህርት ከ10ኛ ክፍል ማጠናቀቅ ሲጀመር እና ከ10ኛ ክፍል በኋላ መሰናዶ ሲባል እንዲሁም የድግሪ ፕሮግራም 4 ዓመት የነበረው ወደ 3 ዓመት ሲወርድ የትምህርት ጥራት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር አንኮታኩቶታል፡፡ ከዚህ ጀምሮ ሥርዓቱ እየተበላሸ የመጣ ይመስለኛል፡፡
ለምሳሌ በእኛ ጊዜ ውጤት አምጥተን ወደ ዩኒቨርስቲ የምንገባው ከፈተናው 50 በመቶ በላይ ማምጣት ሲቻል ነው፡፡ ነገር ግን ገና የመሰናዶ ትምህርት ሲጀመር 400 የነበረው መግቢያ፤ ወደ 101 ወርዶ ወደ ዩኒቨርስቲ ይገቡ ነበር፡፡ ይህ ማለት በጣም የወረደ ውጤት ነው፡፡ ተማሪ 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ማምጣት አለበት፡፡ ከዚህም ባለፈ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ብዙ ተማሪ እንዲያሳልፍ ለኩረጃ ክፍት የሆነ ሂደት ይከተል ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ ኩረጃ ባህል እስኪመስል አድጎ የትምህርት ሥርዓቱን አሽመድምዶታል፡፡ አንዳንዴ ውጤት መጥቶላቸው ራሱ አልገባም የሚሉ ነበሩ፡፡
ምክንያቱም ኮርጀው ስለሆነ ውጤቱን ያመጡት በራስ መተማመን የላቸውም፡፡ ዩኒቨርስቲ ቢገቡም እንደማይሠሩ ያውቁታል፡፡ በራሱ የማይተማመን ዜጋ ከተፈጠረ በኋላ መልሶ ለማስተካከል በጣም ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ወደ ዩኒቨርስቲ በዝቅተኛ ውጤት ማለፍ የትምህርት ሥርዓቱን ጎድቶታል የሚባለው፡፡ በዚህ መልክ ተምሮ መምህር ሆኖ የሚወጣ፣ ሀኪም የሚሆን ወይንም ደግሞ ሌላ ባለሙያ ሆኖ የመጡ አብዛኞቹ የሚጎድላቸው ነገር እንደሚኖር እገምታለሁ፡፡
በአጠቃላይ በዘርፉ የተከሰተው ስብራት በተግባር ሲታይ በጥልቀት የማያስብ፣ ነገሮችን በጥልቀት የማይተነትን፣ በጥልቀት የማይፅፍ እና በጥልቀት መናገር የማይችል ተማሪዎች እንዲበራከቱ በማድረግ ስብራት አስከትሏል፡፡
ንጋት፡- እንደ ሀገር ስብራቱን ለመጠገን የተሠሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
ደ/ር ኤፍሬም፡- የተበላሸውን የትምህርት ሥርዓት ለመቀልበስ በለውጡ መንግስት የፖሊሲ ለውጥ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ይሁን እንጂ በራሱ የማይተማመን ዜጋ ከተፈጠረ በኋላ መልሶ ለማስተካከል በጣም ከበድ ነው የሆነው፡፡ በሂደት መስተካከሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የትምህርት ሥራ እንደ ፋብሪካ ውጤት ሲበላሽ ማሽን ተቀይሮ ወድያው የሚመረት ሸቀጥ ባለመሆኑ ረጅም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በሂደት ነው ውጤቱ የሚታየው፡፡
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፈተና ሥርዓቱ ተቀይሯል፡፡ ለዚህም ነው በቀድሞ ሥርዓት የተማሩ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል የደረሱ ተማሪዎች ሲፈተኑ ውጤት እያስመዘገቡ አይደለም፡፡ በ2015 እና 2016 ዓ.ም እንደሚታወቀው ውጤት በጣም ያሽቆለቆለ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናም ዜሮ ማምጣት ልማድ የሆነ ይመስላል፡፡ ድሮ 100 በመቶ ያልፍ የነበረ ተማሪ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 8 ዓመት ተምሮ አንድም ተማሪ ሳያልፍ ይቀራል፡፡ 12ኛ ክፍልም በተመሳሳይ 12 ዓመት አስተምሮ አንድም ተማሪ ሳያሳልፉ የቀሩ ትምህርት ቤቶች እንደ ዞን፣ ክልል እና ሀገር የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል የማይባል ነው፡፡
ይሄን ሥርዓት ለመቀየር ብዙ ጥረት፤ ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ተማሪው፣ መምህራኑ፣ ወላጅም እና የሁሉንም ማህበረሰብ ቅንጅት ይፈልጋል፡፡ በተለይ መምህራን ከአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ጋር ያለመዋሃድ ነገሮች ይታያሉና በፍጥነት መስተካከል አለበት፡፡
ንጋት፡- ወደዚህ ዘርፍ አመራር ሆነው የመጡበትን ሁኔታ ቢያስታውሱን?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- ካለኝ ልምድ በመነሳት የትምህርት ሥርዓቱ ከገባበት ችግር አንፃር ትምህርቱ ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት ተጥሎብኝ ህዝቡ ኃላፊነት እንደሰጠኝ ይሰማኛል፡ ፡ ነገር ግን ወደ ተግባር ሲገባ ብዙ ችግሮች አሉ፡ ፡ ችግሮቹ ደግሞ የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ ህዝቡን በማሳተፍ ለውጥ ለማምጣት እየሞከርን ነው፡፡ በሂደት ስብራቱ መጠገኑ ባይቀርም ጊዜ ይፈልጋል።
ንጋት፡- በትምህርት ዘርፍ ብዙ እንደመስራትዎ የታዘቡት እና መስተካከል አለበት የሚሉት ነገር ምንድን ነው?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- በርካታ ነገሮች መኖራቸውን መጥቀስ ቢቻልም ዩኒቨርስቲ በቆየሁባቸው ጊዜያት 3 እና 4 ዓመት የቆየን ተማሪ አለማስመረቅ ማለት ብክነት ነው ተብሎ አልፎ እንዲወጣ ይደረግ ነበር፡ ፡ ለዚህ ሁሉም መምህራን ባይባሉም የብቃትና የፍላጎት ማነስ የሚታይባቸው በርካታ መምህራን በመኖራቸው ብቁ ዜጋ እንዳይኖር የሚያበረታታ ሁኔታ እየበዛ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ከተማሪም አንፃር ሲታይ በድሮ ጊዜ ተማሪው መምህሩን ያከብራል፡፡ አንድ ክፍለ ጊዜ መቅጣት እንደ ነውር ይታይ ነበር፡፡
አሁን ላይ የተፈጠረው ተማሪ ግዴለሽ የሆነ መጽሐፍና ደብተር በአግባቡ የማይዝ ነው፡፡ በእኛ ጊዜ አስታውሳለሁ መጽሐፍ እንዳይበላሽ በሲሚንቶ ወረቀት እየለበድን ነበር የምንይዘው፡፡ ትላልቅ የሚባሉ መጽሐፍቶችን ተሸክመን ወደ ክፍል እንሄድ ነበር፡፡ አሁን ላይ መጽሐፍት ይዞ መምጣት የሚጠየፍ፤ ይዞ የሚመጣውን ደግሞ እንደ ጅል የሚቆጥሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ይህን ሁኔታ ለመቀየር ብዙ ጥረት ይፈልጋል። ከዛ ውጭ ውጤቱ ላይ እንደሚታወቀው የፈተና አስተዳደሩ ሲቀየር 12ኛ ክፍል የሚሳካላቸው ልጆች ቁጥራቸው ትንሽ ስለሆነ ሌላው ተማሪ ተስፋ የመቁረጥ ነገሮች አሉ፡፡ እኔም ተምሬ ጨርሼ ውጤት አይመጣ ይሁን በሚል ስጋት ስደትን አማራጭ ያደረጉ በርካቶች ናቸው፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ ስደት ያለው በአጭር ጊዜ ተለውጠው ሲያዩ ደግሞ ትምህርት ምን ያደርጋል? በአቋራጭ ገንዘብ ለምን አላገኝም? የሚል አስተሳሰብ እንደ ዞን እና ክልል ብሎም እንደ ሀገር እየጎላ ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ አንድ ክፍል ውስጥ ከ1 እስከ 3 ተማሪ በማህበራዊ ጉዳዮች ምክንያት ሊቀር ይችላል፡፡ አሁን ግን ተቃራኒ ነው የሆነው፤ 100 ተማሪ ባለበት 10 እና 20 ተማሪ ክፍል ሊመጣ ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ገብተናልና ይህን ችግር መቅረፍ ያስፈልጋል። ይህ ግን በአንድ ጀንበር አይስተካከልም ጊዜ ይፈልጋል፡፡
ንጋት፡- እንደ ዞን በትምህርት ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ምን እየሰራችሁ ነው?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- እንደ ዞን ከችግሩ ተነስተን ያቀድናቸው ዕቅዶች አሉ፡፡ አንድ ተማሪ ተመዝግቦ ለምን ወደ ትምህርት ቤት አይመጣም? በአግባቡ ለምንድ ነው የማይማረው? እና የትምህርት ፍላጎት ለምን ቀነሰ? የሚሉ ጉዳዮች በጥናት ተለይተው እንደ ክልል ጭምር እየተሠራ ነው፡፡ እኛም እንደ ዞን የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በመምህራን ላይ መሠራት ያለበት እየተሠራ ነው፡፡ እንዲሁም በተማሪዎች ላይ መሠራት ያለበት እየተሠራ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ውጤቱን ለመቀየር ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ዘንድሮም በተመሳሳይ ተሠርቷል፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ካመጡ ሌላው በራሱ ተፍጨርጭሮ ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ እና ለሌላው ሞዴል እንዲሆን እየተደረገ በመሆኑ ቀስበቀስ እያገገመ ይሄዳል፡፡ አንድ ተማሪ ከሥር መሠረት በእውቀት ለማነፅ ቅድመ አንደኛ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አልነበሩም፡፡
እንዲሁም ደግሞ ግብዓት ያልተሟላላቸው ናቸው፡፡ ቤተ ሙከራ ያልተደራጀ፣ ቤተ-መጽሐፍቶቹ በአግባቡ ያልተደራጁ ናቸው፡፡ ስለዚህ በየቦታው ተደራሽ ለማድረግ ህንፃው ተቀምጧል እንጂ የተደራጀ አይደለም፡፡ ውስጡም ሳቢ አይደለም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ህዝቡን በማስተባበር ዕቅድ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየሰራን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ክልልም ሆነ ሀገር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ትምህርት ለትውልድ በሚል እሳቤ አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ለማድረስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተሠራ ነው፡፡ ከዛ ውጭ መምህራንም የክረምት ሥልጠናዎችን መውሰድ ጀምረዋል፡፡
ሌላው ችግር የሚስተዋልበትን የትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህራን፣ ሱፐር ቫይዘሮች እና አመራሩ በግለሰቦች ፍላጎት የሚመደቡበት አሰራር በማስቀረት ለውጥ ለማምጣት እየተሞከረ ነው። በዘንድሮ ዓመት በተቻለ መጠን በትምህርት ሥርዓቱ መሠረት የትምህርት ቤት አመራር መስተካከል አለበት ተብሎ በውድድር ነው ርዕሰ መምህርና ሱፐርቫይዘር የተመደበው። የመጀመሪያ ድግሪ እና በማስተርስ ደረጃ የተማሩ ናቸው የሚመደቡት፡፡ በዚህ መልኩ እንደ ማዕከላዊ ክልል እና እንደ ዞን ይህ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ አሁን ላይ ትምህርት ቤቶችን ሳቢ ለማድረግ የሚፍጨረጨር አመራር አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ችግር በአንድ ጊዜ በመቅረፍ ሙሉ ማድረግ ላይቻል ይችላል፤ ግን እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ አመራር ከተስተካከለ ደግሞ ሁሉም ይስተካከላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን መምህራንም ላይ ሪፎርም ይሠራል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ስለዚህ መምህራንም እየበቁ ከግብዓት አንፃር የሚታዩ ክፍተቶች እየተስተካከሉ ሄደው ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በሂደት መልሶ ለመጠገን በዚህ ልክ በትኩረት ለመሥራት እየተሞከረ ነው፡፡ ለዚህም ከተማሪ ወላጅ የጀመረ ማህበረሰብ አቀፍ ውይይት እየተደረገ ይገኛል። በዚህም ትምህርት አይጠቅምም የሚለውን አስተሳሰብ መቅጨት ተችሏል፡፡
ንጋት፡- የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ ትምህርት ወሳኝ ቢሆንም የሚስተዋለውን የተቀጣሪነት ፍላጎት ላይ የሚሉን ነገር ካለ?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- አንድ መታወቅ ያለበት ነገር የተማረ ሁሉ ይቀጠራል ተብሎ አይታሰብም። መንግስት ላይ የሚኖረው መዋቅርም በቁጥር የተገደበ ነው፡፡ ነገር ግን የግሉ ዘርፍ የተመረቀውን የመቀበል አቅሙ እያደገ መምጣት አለበት፡፡ ሰው በግሉም ሠርቶ ለማትረፍ ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ፖሊሲው ላይ የተቀመጠው ከታች ዕድሜ ጀምሮ እስከ 18 ዓመት የመማር ግዴታ አለበት።
ወላጅም እንዲያስተምር ይገደዳል፡፡ ሀገር ባልተማረ ሰው መበልፀግ አትችልም፡፡ ገንዘብ የያዘ ይመስለዋል እንጂ ያለትምህርት ሰው ሙሉ አይሆንም፡፡ ትምህርት ለሁለንተናዊ ዕድገት አስፈላጊ ስለሆነ ትኩረት ተሰጥቶ የትምህርት ስብራት መጠገን አለበት፡፡ መጠገን የሚችልበት ዕድል አለ ብዬ አስባለሁ፡፡
ንጋት፡- የኢድ-አል አድሃ አረፋ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ምን እንድምታ አለው?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- የአረፋ በዓል አላህ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ መታዘዛቸውን ተከትሎ ሳያመነቱ ለፈጣሪ የነበራቸውን የእምነትና የፍቅር ጥግ ያሳዩበት ቀን ነው፡፡ በወቅቱ ልጃቸውን ለመስዋትነት ሲያቀርቡ ፈጣሪ በምትኩ የበግ ሙክት አዘጋጅቶ መሰዋት የተደረገበትን በማስታወስ የሚከበር ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው በዓላት አንዱ ነው፡፡ የኢድ-አል አደሃ አረፋ በዓል በአለም አቀፍ ደረጃ ህዝበ ሙስሊሙ የሚያከብረው በዓል ነው፡፡
ንጋት÷ የማይረሱት የበዓል ትውስታ ይኖር ይሆን?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- ቅድም እንዳልኩት አብዛኛውን ጊዜዬን ትምህርት ላይ በማሳለፌ በዓልን ብዙ ጊዜን ያሳለፍኩት ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከየትኛውም ጥግ የመጣ ተማሪ አንድ ላይ በዓሉን የሚያከበርበት ነው፡፡ ሁሉም እንደ እህትና ወንድም ነው የሚተያየው፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ ሞቅ አድርገን ነው የምናከብረው፡፡ አስታውሳለሁ አንዴ ትልቅ መድረክ አዘጋጅተን ስናከብር የመድረክ መሪ ነበርኩ፡፡ ያን ቀን በዓል በመጣ ቁጥር አስታወሰዋለሁ፡፡
ዩኒቨርስቲ ላይ በጀማ (በግሩፕ) ማክበሩ ልዩ ትዝታ አለው፡፡ እንደ ገጠመኝ ያው ብዙ ጊዜ በዓል ሲመጣ እጅ ያጥራል፡፡ ተማሪ ሲኮን ደግሞ ችግሩ ይብሳል። የሆነ ችግር ሲመጣ አላህ ይረዝቃል (ሲሳይን ይለግሳል) የሚባለው እውነት ነው፡፡ አንድ ቀን ምን ሆንኩ ለበዓል 2 ቀናት ቀርቶት እኔ ግን እጄ ላይ ምንም አልነበረም፡፡
አንድ ዘመዴ መሬት ሊሸጥ ከደላላዎች ጋር ሲያወራ እኔም አጋጣሚ ሆኖ አብሬው ነበርኩ። በመሀል ደላላዎቹ ተጣሉ እኔም ሽማግሌ ሆኜ ላስታርቃቸው መሀላቸው ገባሁ፡፡ ንትርኩ እየተባባሰ ሲሄድ በጣም ጨነቀኝ፡፡ ብዙ የወከባ ልምዱም የለኝም፡፡ ድንገት ፖሊሶች ቢመጡ ምን ይባላል እኔ ትምህርት ላይ ነው ያለሁት፤ እኔንስ አብረው ቢወነጅሉኝ ብዬ ጥዬ ልሄድ ስል 30 ሺህ ብር እንድይዝላቸው ሰጡኝ፤ ገንዘቡን ጭራሽ ስይዝ ፈራሁ፡፡ በመጨረሻ ተረጋግተው 30 ሺህ ለአምስት ሰው ሲያከፋፍሉ እኔንም ተካፋይ አደረጉኝ እና 6 ሺህ ብር ሰጡኝ፤ አላመንኩም፤ እንዳይጠፋ ብዬ በግ የገዛሁበትን ሁኔታ አስታውሳለሁ፡፡
ንጋት፡- እንኳን አደረሳችሁ ማለት የሚፈልጉት አካል ካለ እድሉን ልስጥዎ?
ዶ/ር ኤፍሬም፡- ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1ሺህ 446ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ-አል አድሃ አረፋ በዓል አደረሳችሁ፡፡ በመቀጠል ቤተሰቦቼን፣ እናቴን አሚና ሁሴን፣ ወላጅ አባቴን ዘለቀ መሀመድ፣ ባለቤቴን ወ/ሮ ሙናጃ ቢላል እና ልጆቼን እንኳን አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ንጋት፡- በድጋሚ ጊዜዎን ሰውተው ለቃለመጠየቁ ፍቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሠግናለሁ።
ደ/ር ኤፍሬም ፡- እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ
More Stories
የመስዋዕትነትበዓል
የኢድ-አል-አድሃ በዓል አከባበር
ዓለማት ለምን እና እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ እየጣሩ ያሉት የ30 አገራት ሳይንቲስቶች