የመስዋዕትነትበዓል

በመለሠች ዘለቀ

የኢድ አል አድሃ (አረፋ ) በዓል በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ነው። በዓሉ በእምነቱ አስተምህሮ መሠረት ነብዩ ኢብራሂም የአላህ ትዕዛዝን ለመፈጸም በፍጹም ትህትና እና ታዛዥነት ልጃቸው እስማኤልን ለመስዋዕትነት ያቀረቡበት ነው።

በዚህ መሰረት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የአረፋ በዓል በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስርዓቶች ይከበራል፡፡ የበዓሉን አመጣጥና ሀይማታዊ አከባበር በተመለከተ ከቤተ እምነቱ የሀይማኖት መሪዎች ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ ሼህ አባስ ያሲን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ አባል እና የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ የአረፋ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጣም የተከበረ ትልቅ በዓል ነው፡፡ የአረፋ በዓል ከነብዩ ኢብራሂምና ከእስማኤል ጀምሮ ሲከበር የነበረ በዓል እንደሆነም አስረድተዋል።

ስለ በዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ ሲገልጹ፡- የዒድ አል-አድሃ ታሪካዊ ዳራ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያቀረቡበትና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጃቸውም ታዛዥነትን ያሳየበት መታሳቢያ በዓል ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዒስማኢልን ያገኙት በእርጅና ዘመናቸው ነው፡፡ ታላቅ ሚስታቸው ሳራ ለፍሬ ባለመብቃቷ አላህ ያለ ዘር አታስቀረኝ፤ እኔን የሚተካ ሷሊህ የሆነ ልጅ ስጠኝ በማለት ዱዓ እንዳደረጉ ያብራራሉ፡፡

በዚሁ መሰረት በሳራ ፈቃደኝነት ሐጀራ የምትባለውን የቤት ሰራተኛቸውን አገቡ፡፡ ሐጀራም ዒስማኢል የተባለ ልጃቸውን ወለደችላቸው፡፡ ይህ ልጅ በአላህ ፈቃድ በመካ ከተማ እንዲያድግ የተወሰነ ስለነበረ ኢብራሂም ሐጀራን እና ዒስማኢልን ወደ ዐረቢያ ከተማ ወሰዷቸው፡፡  

ዒስማኢል ካደገ በኋላ ደግሞ አላህ ልጅህን እንድትሰዋ ታዘሃል የሚል ራዕይ በህልማቸው አሳያቸው፡፡  ስለዚህ ኢብራሂም በህልማቸው ያዩትን በዝምታ አላለፉትም፡፡ ፈጣሪያቸውን በመታዘዝ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው ኢስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ አላህ ያዘጋጀውን ሙክት በግ መስዋዕት ያደረጉበት በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም እንደሚከበር ሼህ አባስ ያሲን ያስረዳሉ። 

የበዓሉ እንድምታ የሰው ልጅ ለፈጣሪና ለወላጅ መታዘዝን፣ መስዋዕትነትና፣ ከፍላጎቶች ሁሉ የፈጣሪን ፍላጎት ማስቀደምንና ሰው ከሰው እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር ያለውን ትስስርን የሚያስተምር በዓል ነው፡፡  የሰው ልጅ መስዋዕቱን ለፈጣሪ በማቅረብ ወደ ፈጣሪ የሚቀርብበትና ከሰው ሁሉ ጋር ያላውን መልካም ግንኙነት የሚያጠናክርበት ቀን ነው፡፡

የአረፋ በዓል የጋራ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች የሚበለጽጉበት፣ አብሮነት፣ መደጋገፍ፣ መረዳዳትና መተሳሰብ የሚጎለብቱበት ነው፤ በእለቱም እነዚህ ሃይማኖታዊ እሴቶች ጎልተው የሚስተዋሉበት ነው፤ አቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን በማገዝ የሚከበር ነው። የመረዳዳት በዓል በመሆኑም በእለቱ ያለው ለሌለው ያካፍላል በዚህም የፈጣሪውን ትዕዛዝ ይፈጽማል።

በዓሉ ከዚህም ባለፈ፤ የእምነቱ ተከታዮች ጥፋት ካለባቸው ለጥፋቱ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ትክክለኛ መንገድ የሚመጡበት ነው። አደምና ሀዋ ከገነት ወጥተው ተለያይተው ረጅም ጊዜ ከቆዩ በኋላ አረፋ በሚባል ተራራ ላይ እንደተገናኙ የእስልምና አስተምሮ እንደሚያስረዳ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ አመቱን በሙሉ ተራርቀው የቆዩ ሰዎች በአረፋ በዓል ይገናኛሉ፡፡ የተጣሉሰዎችም ካሉ የአረፋን በዓል ምክንያት በማድረግ ታርቀው የአረፋን በዓል በአንድ ላይ ያሳልፋሉ፡፡ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት፣ ማህበራዊ ትስስሩና ቤተሰባዊነት የሚንጸባረቅበት በዓል ነው የአረፋ በዓል፡፡

የአረፋ በዓል ሲከበር በህይወት ያለው ሰው ብቻ ሳይሆን ሙታንም ጭምር የሚታሰቡበት ነው፡፡

ለሙታንም ፈጣሪ ምህረት እንዲሰጣቸውና ገነት እንዲያገኙ ዱአ የሚደረግበት ቀን ነው፡፡ ከብቶችም ጭምር መስክ የማይወጡበትና እቤት ሆነው የሚቀለቡበት፣ ህጻናትም አዲስ የተገዘላቸውን ልብሳቸውን ለብሰው ደስታቸውን የሚገልጹበት በዓል ነው፡፡

የሲዳማ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢና የሀዋሳ ከተማ የቡና ቅምሻ ሀምዛ መስጂድ አስተዳደር ሼህ ኢስማኤል ስራጅ በበኩላቸው አደምና ሀዋ ከገነት ወጥተው ለረጅም ዘመናት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ በአራፋት ተራራ ላይ መገናኘታቸው የሚዘከርበት በዓል ነው ሲሉ ተናግረዋል። የሃጂ ተጓዦች ከሚከውኗቸው አበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱና ወሳኙ የአራፋት ተራራን መውጣት ነው።

እንደ እሳቸው ገለጻ በዓል በሁለት አይነት መልኩ ይከበራል፤ አንደኛው ሃይማኖታዊ መስፈርቶችን ጠብቆ ወደ መካ በመሄድ የሚደረግ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ነው። የሃጂ ተጓዦች ከሚከውኗቸው አበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱና ዋንኛው የአራፋት ተራራን መውጣት ነው። አቅማቸው የፈቀደላቸው ሙስሊሞች ቢያንስ በሕይወት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ቅድስቲቱን ምድር መካን በሐጅ ሥርዓት መካፈል ይጠበቅባቸዋል።

ከመካ በስተምሥራቅ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘውን ቅዱስ ተራራ መመልከትና ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶችን በዚያው መፈጸም እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ያዛል። በዚያም ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስም ቅዱስ ቁርአን እያነበቡ፣ ፈጣሪን እያወደሱና እና የምህረት እጁን እንዲዘረጋ እየለመኑ ይቆያሉ። የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ቀን ከብት የማረድ ግዴታም እንዳለበት ያብራራሉ።

ሁለተኛው ወደ መካ ለመሄድ ዕድልን ያላገኙ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሙስሊሞች የዒድ ሶላት ሥርዓትን በአንድነት በአደባባይ በደመቀ ሁኔታ ያከብራሉ። ከሶላት በኋላ አቅም ያላቸው ሰዎች በግና ሌሎች እንስሳትን በማረድ አቅም ለሌላቸው ጎረቤቶቻቸው በማካፈል በዓሉን በጋራ ያሳልፋሉ።

ሙስሊሞች የመስዋዕትነት በዓሉን አረፋ እርድ በመፈጸም፣ በጋራ በመጸለይ እና ከፈጣሪ ምህረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን ያሳልፉታል። የአረፋ በዓል በቅድስቲቱ ምድር መካ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የእምነቱ ተከታዮች ቋንቋ ሳይገድባቸው፣ የቆዳ ቀለም ሳይለያቸው፣ ስፍራና ማንነት ሳያግዳቸው በአንድ አይነት አለባበስ በአንድነት በመሰባሰብ ጥያቄያቸውን ለፈጣሪ የሚያቀርቡበት ነው።

በየቤቱ አቅም እንደፈቀደ ምግብ አዘጋጅቶ ከዘመድ ወዳጅ ከጎረቤት ጋር መብላት መጠጣትም በዚህ በዓል የተለመደ ነው። ለኢድ አል አድሃ አንድ ሰው ከሚያርደው ከብት አንድ ሲሶውን ብቻ እንዲወስድ፤ አንድ ሲሶውን ለችግረኞች፣ የተቀረውን አንድ ሶስተኛውን ለጐረቤት እንዲሰጥ የሃይማኖቱ አስተምሮ ያዛል ሲሉ ያብራራሉ።

የአረፋ ቀናቶች በምድር ላይ ካሉ ቀናቶች ሁሉ እጅግ የተከበሩ ቀናቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ቀናቶች በጾም፣ በሶላትና መልካም ተግባራን በማድረግ ማሳለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ለ1 ሺህ 446ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የእምነቱ መሪዎች፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ መረዳዳትን በዓል ሲመጣ ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ባህል ሊያደርጉት ይገባል ብለዋል፡፡ ለራሳቸውም ሆነ ለወገኖቻቸው የአብሮነት፣ የመደጋገፍ፣ የመረዳዳት እና የበጎነት ተምሳሌት እንዲሆኑ አበክረው መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡