የኢድ-አል-አድሃ በዓል አከባበር
በፈረኦን ደበበ
በዓላት ምዕመናንን አንድ በማድረግ ደስታ የሚሰጡ እንደመሆናቸው የኢድ-አል-አድሃ በዓልም በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የተቀመጡ መርሆዎችን ተከትሎ ለዕምነቱ ተከታዮች መተሳሰብና ፍቅርን ያጎናጽፋል፡፡
በሌላ መጠሪያው “የመስዋዕትነት” በዓል ተብሎ የሚታወቀው ኢድ ለሦስትና አራት ቀናት በተከታታይ የሚከበር ሲሆን በየዓመቱ በተወሰኑ ጊዜያት መዋሉም ምዕመናን በጉጉት እንዲጠባብቁት ያደርጋል፡፡
በተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱና ከኢድ አል ፈጥር በኋላ ጥቂት ወራትን ቆይቶ የሚመጣው ኢድ አል አድሀ “ትልቅ” ወይም “ታላቅ” በዓል የሚል ሲያሜም አለው፡፡
በአንዳንድ የአከባበር ሥርዓቶች ከኢድ አል ፈጥር ጋር ተመሳሳይነት ያለው በዓሉ መነሻውም ነብዩ ኢብራሂም ለፈጣሪ ካቀረበው መስዋዕትነት እና በወቅቱ አላህ ከሰጠው ምላሽ ጋር ተገናኝቷል፡፡
ኢድ-አል-አድሀን ደማቅ ከሚያደርጉ ባህሪያት መካከል የአከባበር ሥርዓቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል በዕለቱ የሚደረጉ ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡ ጠዋት ላይ ጸሎታቸውን ለማድረስ ወደ መስጂድ ወይም ሌሎች የመስገጃ አደባባዮች የሚተሙ ምዕመናን በደማቅና አዳዲስ ልብሶች መዋብ የተለመደ ነው፡፡
ለእርድ እንዲሆን የደረሱ እንስሳት ሲመረጡ እንደ በግ፣ ፍየል፣ በሬ እና ግመል ያሉት ቅድሚያውን ይወስዳሉ፡፡
ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱና ሠራተኞችም በዕረፍት ላይ የሚያሳልፉበት ይህ በዓል “ፈጣሪ ለኢብራሂም ከሰጠው ትዕዛዝና ተስፋ ጋርም የተገናኘ ሆኗል” ነቢዩ መሀመድ እንደተናገሩት፡፡
የበዓሉ አከባበር ዋና መንስኤ ወደ ሆነው ጉዳይ ከገባንም ይህ ለአላህ መታዘዝ በሚያስገኘው መልካም ዕድል ላይ ያተኩራል፡፡ ብዙ ጸሀፊዎች የበዓሉ ዋነኛ መንስኤ መስዋዕትነት ነው ብለው ሲያቀርቡ፤ ሀሳቡም ኢብራሂም ልጁ እሥማኤልን መስዋዕት ለማድረግ ከተመኘው ተግባር ጋር ይገናኛል፡፡
በዚህ ጊዜ አላህ ለእሱ ሌላ በረከት አዘጋጀለት፡፡ እሥማኤልን ባዘጋጀው ምትክ የእርድ በግ መስጠቱም እምነት ምን ያህል የተሻለ ተስፋ እንደሚያስገኝ ያመለክታል፡፡ በቅዱስ ቁራን ምዕራፍ 37 ላይ የተመለከተው ይህ ታሪክ ከሌላው የእምነቱ ምሰሶ ጋር እንተቆራኘም ጸሀፊዎቹ አመልክተዋል፡፡
የእምነቱ አምስተኛ ምሰሶ የተባለውና “የሀጂ ጉዞ” ተብሎ የሚታወቀው የመስዋእትነት ሥነ-ሥርዓት መብቃትን ተከትሎ የሚደረግ ሲሆን ጉልበትና ገንዘብ ያለው ሙስሊም በህይወት ዘመኑ ማለፍ ያለበት ደረጃም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በጉዞውም በሳውዲ ዓረቢያ የሚገኙ ቅዱስ ቦታዎች፤ ማለትም መካና መዲና በመጎብኘት እርካታ ያገኙበታል፡፡
ቀጥሎ የሚነሳው የበዓሉ ማክበሪያ ቀንን የሚመለከት ሲሆን ይህም እንደ ሌሎች የእስልምና በዓል አከባበር ዘይቤዎች ጨረቃን ተከትሎ መሆኑ የራሱን ተጽዕኖ ያደርጋል፡፡ ቀኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲለዋወጥ አስተዋጽኦ ሲኖረው በዱሀ- አል- ሂጂራ 10ኛው ቀን እንዲውልና ለአራት ቀናት እንዲቆይም አድርጎታል ተብሏል በአንዳንድ ድረ-ገጾች፡፡
ዘንድሮን ጨምሮ ኢድ ለሚከበርባቸው ቀናት መለዋወጥ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች እነዚህ ሲሆኑ የማክበሪያ ጊዜውንም በየዓመቱ ከ11 ቀናት በኋላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከዚህ አንጻር ጊዜው እ.ኤ.አ. በ2022 በአማካይ ከሀምሌ 9 ጸሀይ መግቢያ እስከ ሀምሌ 10 ጸሀይ መግቢያ ሆኖ ለብዙ ቀናት እንደሚቆይም ነው የተነገረው፡፡
ቀጥሎ የሚነሳውና የበዓሉን አብይ ገጽታ የሚያሳየው ማህበራዊ መስተጋብሩ ሲሆን ድሆች፣ አቅመ ደካሞችና በተለያየ ዓይነት ችግር ውስጥ የሚገኙት ታሳቢ ባደረገ መልክ መከበሩ ደስታን ይፈጥራል፡፡
ለዚህ አንድ ማሳያ ለበዓሉ ተብሎ የታረደው ሥጋ ለሁሉም እኩል እንዲደርስ የሚለው መርህ ተጠቃሽ ሲሆን ያላቸው ለሌላቸው በማጋራት በአንድነት ስሜት የሚያከብሩበት ነው፡፡
አዳዲስ ልብሶችን በመልበስ ቤተሰብ ከዘመድ አዝማድ ጋር የሚገናኙበት በዓል ሥጦታ በመለዋወጥና በእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫዎችም ይደምቃል፡፡
አሁን አሁን በስፋት እየተከናወኑ ያሉ የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎችም የኢድ- አል- አድሃ እና የኢድ- አል-ፍጠር በዓላት ማሳያዎች ሲሆኑ ዲጂታል የሆኑ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረኮችን ጨምሮ ጤናና ሌሎች የመሠረተ-ልማት ግንባታ ሀሳቦች ተግባራዊ ይደረጉበታል እንደ ህጻናት፣ ወላጅ ያጡና አካል ጉዳተኛ ወገኖችን መደገፍ ጨምሮ፡፡
More Stories
የመስዋዕትነትበዓል
ዓለማት ለምን እና እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ እየጣሩ ያሉት የ30 አገራት ሳይንቲስቶች
“የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ወደ ኢንደስትሪ ለማሻገር እየተሰራ ነው” – የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት