በበዓላት ሰሞን የትራንስፖርት እጥረት፣ የታሪፍ ጭማሪና የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት እየሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ገለፀ
በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ተገልጋዮችም በበዓላት ሰሞን የሚያጋጥመው የትራንስፖርት እጥረትና የታሪፍ ጭማሪ ህብረተሰቡን ላላስፈላጊ እንግልት የሚዳርግ በመሆኑ ተገቢው የቁጥጥርና የመከላከል ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የአረፋ በዓል በስልጤ ልዩ ድምቀት የሚሰጠው፤ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የብሄረሰቡ ተወላጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ በመያዝ ወደ አካባቢያቸው የሚመጡበት ነው።
የስልጤ ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እዮብ ሙስጠፋ እንዳሉት፤ የአረፋ በዓልን ለማክበር ከሀገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመጡ በርካቶች በመሆናቸው ይህንን ታሳቢ በማድረግ እንግዶች የሚተላለፉባቸዉ የጠጠር መንገዶችን የማደስ፣ ብልሽት ያለባቸውን መንገዶች የመጠገንና ለትራንስፖርት አመቺ ያልሆኑ መንገዶችን የማስተካከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በበዓሉ የተሽከርካሪ እጥረት እንዳይገጥምና የእንግዶች ጉዞ ጤናማ እንዲሆን ከማህበራት፣ ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የአረፋ በዓልን ለማክበር እንግዶች ወደ ዞኑ የሚገቡት በበዓሉ ዋዜማ ላይ በመሆኑ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት እና እንግዶች እንዳይጉላሉ በዞኑ ባሉ በሁሉም መናኸሪያዎች የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ምርመራ የማድረግ፣ የትራንስፖርት ፍሰቱን የማሳለጥ፣ የታሪፍ ጭማሪ እንዳይኖር የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ እዮብ፤ ከትራፊክ ፖሊስ፣ ከመንገድ ደህንነት ባለሙያዎችና ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እንግዶችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
በበዓላት ሰሞን በመመሪያ ከተቀመጠው የትራንስፖርት ታሪፉ ውጭ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድና የማስተማር፣ እንግዶች ከሚመጡበት ከአዲስ አበባ ጀምሮ ከአጎራባች ዞኖች ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንግዶች በዓሉን ለማክበር በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ሁሉም ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ: ሙጂብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በሆሣዕና ከተማ የሚገነቡ ሆቴሎች የከተማውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ከተማው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) ገለፁ
በደቡብ ኦሞ ዞን በሣላማጎ ወረዳ በሌማት ትሩፋት በቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት ድጋፍ በዶሮ እርባታ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ
በጎፋ ዞን ከ950 ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩ ተገለጸ