በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚከሰት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ገበያ የማረጋጋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚከሰት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ገበያ የማረጋጋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ፡፡
ሸማቹ የህብረተሰብ ክፍል ዕቃ በሚገዛበት ወቅት በተለጠፈው የዋጋ ዝርዝር መሰረት መገበያየት እንደሚገባም ተጠቁሟል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አይናለም ይርዳው እንደተናገሩት፤ በከተማ አስተዳደሩ በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ ተግባራትን መከላከል እንዲቻል ግብረ ሀይል ተቋቁሞ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም የአረፋ በዓል ገበያን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ነጋዴዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ እንደ ከተማ አስተዳደሩ በ6ቱም ቀበሌያት የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች የዋጋ ዝርዝራቸው ለሸማቾች ግልጽ በሆነ ሁኔታ እንዲታወቅ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ በዚያ ልክ እንዲገበያይ በየደረጃው ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ በማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው ኃላፊው የተናገሩት።
በአሁን ጊዜ ባጋጠመው የምርት እጥረት ምክንያት በአንዳንድ ምርቶች ላይ መጀመሪያ ከነበረበት የዋጋ ጭማሪ መኖሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ ያልተገባ ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊው አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሸማቹ የህብረተሰብ ክፍል ዕቃ በሚገዛበት ወቅት በተለጠፈው የዋጋ ዝርዝር መሰረት መገበያየትና ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙ ለተመደቡ አካላት ጥቆማ እንዲያደርሱ ኃላፊው አሳስበዋል።
በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት የሸማቾች ጥበቃና ድጋፍ ቡድን መሪ ወ/ሮ አበባ ተመስገን በበኩላቸው፤ ገበያውን ማረጋጋት እንዲቻል እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ወርደው ተግባራትን ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በመሆን ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳሉ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በመንግሥት ድጎማ የሚመጣው ዘይት በወቅቱ እንዲደርስ ባደረግነው ጥረት ዘይት መጥቶ በሸማች ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ እንዲደርስ አስፈላጊውን መረጃ የማሟላት ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ ለአረፋ በዓል እንደሚደርስም ገልፀዋል።
አንዳንድ ያነጋገርናቸው ሸማች የከተማው ነዋሪዎች፤ በመንግሥት በኩል ገበያን ለማረጋጋት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በመንግሥት ድጎማ የሚቀርበው ዘይትና ስኳር በሚፈለግ ጊዜ ያለመድረስ ችግር እንዳለና በበዓል ምክንያት ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር በተያየዘ በአንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን ተናግረዋል ።
ዘጋቢ፡ ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ መነጋገር ያስፈልጋል – አቶ አንተነህ ፍቃዱ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ግንቦት 26/2017 ዓ.ም
የኣሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የሴቶች ሚናን በተመለከተ የጋራ ውይይት በጂንካ ከተማ ተካሄደ