በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በማህበረሰብ ተሳትፎ የ52 ኪሎ ሜትር የመንገድ ልማት ስራ መከናወኑ ተገለፀ

በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በማህበረሰብ ተሳትፎ የ52 ኪሎ ሜትር የመንገድ ልማት ስራ መከናወኑ ተገለፀ

ለዚሁ ተግባር የሚውል 60 ሚልዮን የሚጠጋ ገንዘብ ከወረዳው ነዋሪዎችና ከባለሃብቱ መሰብሰቡንም ተመላክቷል።

የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቱ ተክሌ በመንግስት በጀት ከሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ባሻገር በገጠርና በሃገሪቱ በተለያዪ ከተሞች ከሚኖሩ ከወረዳው ተወላጆች እና ባለሃብቱን በማስተባበር በተያዘው በጀት አመት ከማህበረሰቡ ተሳትፎ ለመንገድ ስራ 64 ሚልዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

በተያዘው የበጀት አመት በባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 52 ኪሎ ሜትር የአፈር ስራ መሰራቱንና ከዚህም አብዛኛው መንገድ ጠጠር የማልበስ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።

በዚህም የወረዳው አብዛኛው ቀበሌያት ከወረዳ ማዕከል እና ቀበሌ ከቀበሌያት እንዲሁም መንደሮችን ከመንደሮች ጋር በመንገድ መሠረተ ልማት ማስተሳሰር መቻሉን አውስተዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ በመንገድ ግንባታ ስራ በአርያነት የሚጠቀስ ታሪክ ያለው ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህ ደግሞ የእኖር ወረዳ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኡስታዝ አብዱልዋሪስ ሙደሲር እና ወ/ሮ ረውዳ ንዳ የጎምሸ ቀበሌ፣ እንዲሁም ተማሪ ሃምዛ ኑሩ የአጋሬ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ በሰጡት አስተያየት ለረዥም ጊዜያት ሲጠይቁት የነበረውን የመንገድ ልማት ተሰርቶ ለአገልግሎት በመዋሉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ከዚያ ቀደም በነበረው የመንገድ እጦት ምክንያት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድርባቸው እንደነበር የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ ያመረቱት ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ እና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፣ ሚፍታ ጀማል-ከወልቂጤ ጣቢያችን