“የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር አመጋገብ የማዕዘን ድንጋይ ነው” – ዶክተር ያደሳ ተገኔ
የዛሬ የንጋት እንግዳችን ዶክተር ያደሳ ተገኔ ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስነ ምግብ የትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በስኳር በሽታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከ25 በላይ ጥናቶችን በአለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ በቆይታችን ስለ ስኳር በሽታና አመጋገብ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጋብዘናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡- ውድ ጊዜዎትን ሰጥተው ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ያደሳ፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- እራስዎትን በማስተዋወቅ እንጀምር?
ዶክተር ያደሳ፡- ተወልጄ ያደኩት በምዕራብ አርሲ ዶዶላ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቴን በትውልድ አካባቢዬ ተከታትያለሁ፡፡ በመቀጠል በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በነርሲንግ ሙያ ተከታትያለሁ፡፡ እንዲሁም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በህብረተሰብ ጤና /የጤና መኮንን/ የመጀመሪያ ድግሪዬን ወስጃለሁ። ሁለተኛ ድግሪዬንም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በስነ ምግብ ዘርፍ ተከታትያለሁ፡፡
ከዚያ በኋላ በሀዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ9 አመታት ያህል አስተምሬያለሁ፡፡ ከዚያ በፊት በነበረኝ ስራ ልምድ በሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ አርቤጎና ጤና አጠባበቅ ጣቢያ በባለሙያነትና በጤና ጣቢያ ኃላፊነት ለአራት አመታት አገልግያለሁ፡፡ ከዚያ በመቀጠል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሁለት አመት ካስተማርኩ በኋላ የትምህርት እድል አግኝቼ በአውሮፓ የሶስተኛ ወይም ፒ.ኤች.ዲ ድግሪዬን በህብረተሰብ ጤና ወስጃለሁ፡፡ ጥናታዊ ጽሁፌንም በኤች.አይ.ቪ ህሙማን አመጋገብ ስርአታቸውና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደ ደም ግፊት እና ስኳር በሽታዎች ዙሪያ ነበር የሰራሁት፡፡ በህብረተስብ አቀፍ አገልግሎትና በምርምር ስራዎች በአለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ከ25 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን አሳትሜያለሁ። ጥናታዊ ጽሁፎቹ የሚያጠነጥኑት በስኳር በሽታ፣ በደም ግፊት፣ በኤች.አይ.ቪ እና አመጋገብ ዙሪያ ላይ ነው፡፡
በአጠቃላይ በስራ አለም ላይ 21 አመት አገልግያለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ህብረተሰብ አቀፍ ትምህርት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
ንጋት፡- ስኳር በሽታ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ያደሳ፡- የስኳር በሽታ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፉ ከሚገኙ በሽታዎች ውስጥ አንዱ ነው። ስኳር በሽታ ማለት ሰውነታችን የደም ስኳርን በትክክል መጠቀም አለመቻል ሂደት ነው፡፡ በሰውነታችን የደም ስኳርን እንዲጠቀም የሚያስችል ኢንሱሊን የሚባለው ንጥረ ነገር ሰውነታችን ስኳርን በአግባቡ እንዲጠቀም ወይም ደግሞ ሴሎቻችን ስኳርን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ንጥረ ነገርን በበቂ ሁኔታ አለማምረት ነው፡፡ ሰውነታችን የደም ስኳርን በትክክል ሳይጠቀም ሲቀር የሚከሰት የሜታቦሊክ ችግር ነው፡፡
መንስኤው በግልጽ ባይታወቅም በተፈጥሮ የሰውነት ክፍል ውስጥ የሚመነጨው ኢንሱሊን በበቂ ሁኔታ አለመመንጨት፣ ኢንሱሊኑ በተለያየ ምክንያት ሲጎዳ ማመንጨት ሲያቆም እና በቂ ኢንሱሊን መንጭቶ በአግባቡ ባለመሥራቱ ምክንያት ሊከሰት የሚችል በሽታ ነው፡፡
የኢንሱሊን ሥራ ከምግብ የሚገኘውን ግሉኮስ ወይንም ስኳር ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ተሰራጭቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው። ሰውነት በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር ሲሳነው ቋሚ የሆነ የስኳር መጨመር ይከሰታል። ይህም የስኳር ሕመምን ያስከትላል።
ንጋት፡- የስኳር በሽታ መንስኤ ምክንያቶች እንዴት ይገለጻሉ?
ዶክተር ያደሳ፡- የስኳር በሽታ እንደ ሌሎቹ በሽታዎች ምክንያቱን ይሄ ነው ብለን ልንጠቅሰው የምንችለው ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ለበሽታው ሊዳርጉ ወይም ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህንን ከማውራታችን በፊት የስኳር በሽታን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ይህም አንደኛ ደረጃ የስኳር አይነትና ሁለተኛ ደረጃ የስኳር አይነት ብለን ማየት እንችላለን፡፡
የመጀመሪያው አይነት የስኳር በሽታ በአብዛኛው በለጋ እድሜ ክልል ላይ ወይም ህጻናትና በአመዛኙ ከ30 አመት እድሜ ክልል በታች የሚከሰት ነው፡፡ ነገር ግን በሌላኛው እድሜ ክልል ላይ አይታይም ማለት አይደለም፡፡ በማንኛውም እድሜ ክልል ሊከሰት ይችላል ግን በአብዛኛው በለጋ እድሜ ክልል ላይ የሚከሰት የስኳር በሽታ አይነት ነው፡፡ ምክንያቱን ግን ይሄ ነው ብለን ልንገልጽ ባንችልም በሳይንስ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ህጻን ልጅ እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ብቻ መጥባት እንዳለበት ይመከራል፡፡ ነገር ግን ከስድስት ወር በፊት ከእናት ጡት ወተት በተጨማሪ የሚሰጡ ነገሮች ባዕድ ናቸው፡፡
ለምሳሌ አንድ ህጻን የከብት ወተት ከስድስት ወር በፊት ቢጀምር ባዕድ ነው የሚሆንበት፡፡ ሰውነታቸው ለዛ ባዕድ ነገር መከላከያ ማዘጋጀት ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ሰውነታቸው ለዚያ ባዕድ ነገር መከላከያ በሚያዘጋጅበት ጊዜ በስህተት ከእናት ጡት ወተት ጋር ሲጋጭ ኢንሱሊን የሚያመርተውን ሴል ያጠቀዋል፡፡ የኢንሱሊን ማምረቻ ሴሉ በሚጠቃበት ጊዜ የኢንሱሊን ምርቱ ይቀንሳል፡፡ በዚህ ጊዜ የመጀመሪያው ደረጃ የስኳር በሽታ ሊከሰት ይችላል የሚባል ነገር አለ፡፡ ነገር ግን ምክንያቱ ይሄ ነው ተብሎ እንደ ወባ ፣ ቲቪና እንደ ኤች.አይ.ቪ ልንገልጸው አንችልም፡፡
ወደ ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ ስንመጣ የሚያባብሱ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ መሆን ይህም ማለት የአንድ ሰው ክብደት ለቁመት ሲካፈል ውጤቱ ከ24.9 በላይ ከሆነ የክብደት መጠኑ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ጊዜ ለስኳር በሽታ የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ይሆናል፡፡
በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአመጋገብ ስርዓት የተስተካከለ አለመሆን፣ ለምሳሌ የምንመገባቸው ምግቦች በውስጣቸው የሚይዙት የጉሉኮስ መጠን ከፍተኛ ከሆነ፣ ወይም ሰውነታችንን የማያዳክሙ ምግቦች ለአብነትም የተፈተጉ ምግቦች፣ ነጫጭ ምግቦች ሰውነታችን በቀላሉ ወደ ስኳር መቀየር ይችላል፡፡ ከአመጋገባችን አንጻር ሰውነታችን በቀላሉ ወደ ስኳር የሚቀይራቸውን ምግቦች የምናዘውትር ከሆነ ክብደታችን ይጨምራል። በሰውነታችን የሚኖረው የደም ስኳር መጠን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ እነዚህ እንደ አባባሽ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ ምክንያቶችን ይሄ ነው ብለን ማስቀመጥ ባንችልም አባባሽ ምክንያቶቹ ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡
ንጋት፡- ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ ቅባት የበዘባቸው ምግቦች ማለትም ጮማና ስጋ ነክ ነገሮች ለስኳር በሽታ አባባሽ ምክንያት ሊሆን ይችላሉ?
ዶክተር ያደሳ፡- በህብረተሰብ ውስጥ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች ይኖራሉ አመጋገብን በተመለከተ፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ወደ ህብረተሰቡ የሚደርሱ የተሳሳቱ መረጃዎች አሉ፡፡ ጮማ በምንጠቀምበት ጊዜ ሰውነታችን ጮማ ለመፍጨት የሚጠቀመው ኢነርጂ ብዙ ነው፡፡ ሰውነት በተለያዩ መንገድ ነው ሀይል የሚያወጣው፤ አንዱ በእንቅስቃሴ ሌላኛው ምግብ በመፍጨት፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ነጭ ዳቦ ሲበላና ጮማ ሲበላ እኩል ሀይል አያቃጥልም፡፡ ጮማ የሚበላ ሰው ብዙ ኢነርጂ ያቃጥላል፡፡ ነጭ ዳቦና ለስኳርነት የቀረቡ ስኳርንም ጨምሮ የተጠባበሱ ምግቦች በቀላሉ ወደ ስኳርነት የመቀየር እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ጮማ የራሱ የሆነ ጎጂ ጎን አለው፡፡ ነገር ግን ለመፈጨት ብዙ ኢነርጂ ስለሚፈልግ ወደ ስኳርነት የመቀየር እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሰውነታችን ጮማን ወደ ስኳርነት ከመቀየር ይልቅ የእህል ምግቦችን መቀየር ይቀለዋል፡፡
ከስጋና ስጋ ነክ ነገሮች የበለጠ የእህል ምግቦች በተለይም የተፈተጉና ነጫጭ እንዲሁም ከፋብሪካ የወጡ ምግቦች የስኳር በሽታን ሊያባብሱ ይችላሉ።
ንጋት፡- ሁለተኛውን አይነት የስኳር በሽታን አመጋገብን በማስተካከል በተለይም በቀን ሁለት ጊዜ ስጋና ጎመን ብቻ በመብላት ማጥፋት ይቻላል የሚባል ነገር አለ፡- ይህ በሳይንስ እንዴት ይደገፋል?
ዶክተር ያደሳ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እኔም ይህንን ለማብራራት ይህንን እድል ስላገኘሁ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ሰዎች ብዙ ጊዜ በባህሪያችን በራሳችን ስኬት መስመር ላይ ነው ነገሮችን የምንፈርጀው፡፡ ይህንን ጥያቄ አንድ የጤና ባለሙያ ብትጠይቂው አዎ ብሎ ላይመልስልሽ ይችላል፡፡ ይህንን ጥያቄ ደግሞ የስነ-ምግብ ባለሙያዎችን ብትጠይቂው አዎ ልክ ነው ብሎ ሊመልስልሽ ይችላል፡፡
የእኔ ምላሽ ደግሞ ሰውነታችን ከስኳር ነክ ነገሮች መቀነስ ከቻልን የስኳር በሽታንም መቀነስ እንችላለን፡፡ ስጋ ነክ ነገሮችና ቅጠላቅጠል ምግቦች ወደ ስኳርነት የመቀየር እድላቸው ዝቅተኛ ስለሆነ መጠኑን መቀነስ ይቻላል፡፡ ያ ማለት ግን ከሰውነታችን የስኳር በሽታ ሙሉ ለሙሉ እናጠፋለን ማለት አይደለም፡፡ አንድ የስኳር ታካሚ በቀን ሁለቴ በመብላት ብቻ መቆጣጠር አይቻልም፡፡
ብዙዎች አመጋገብን በማስተካከል ከስኳር በሽታ ድኜያለሁ በማለት ህክምናውን የማቋረጥ ነገር ይስተዋላል፡፡ አመጋገብ ስኳርን ያስተካክላል ትክክል ነው፡፡ ያ አመጋገብ የቆመ እለት በሽታው ድጋሚ ይቀሰቀሳል፡፡ በዛ ልክ እድሜ ልካችንን የምንቀጥል ከሆነ የስኳሩን መጠን መቆጣጠር እንችላለን፡፡ መድሃኒትም ሙሉ ለሙሉ የስኳር በሽታን አያድንም፡፡ ልክ የመድሃኒቱን ስራ አመጋገብን በማስተካከል መተካት እንችላለን ማለት ነው በሌላ አባባል፡፡ ሊዘነጋ የማይገባው ነገር ቢኖር የማያቋርጥ የህክምና ክትትል፣ የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አብሮ መሄድ ሲቻል ነው ውጤታማ መሆን የሚቻለው፡፡
ንጋት፡- የስኳር በሽታና አመጋገብ እንዴት ይገለጻሉ?
ዶክተር ያዴሳ፡- ስኳርና አመጋገብ ተነጣጥሎ መሄድ የሌለባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የስኳር በሽታ ዘላቂ መፍትሄ ባይኖረውም በመድሃኒት በአመጋገብና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ መደገፍ ቢኖርበትም ምግብ የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ምክንያቱም የችግሩ ምንጭ ምግብ ነው፡፡ መድሃኒት የምንወስደውም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምናደርገውም ስኳሩን ለመቀነስ ነው፡፡ አመጋገብ ግን አገባብ ላይ ነው የምናስተካክለው መጠኑን አስተካለን የምንበላ ከሆነ ከፍተኛ ውጤት ያስገኛል፡፡ ብቻውን ግን መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ አመጋገብ የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ በየሚዲያው ከስኳር በሽታ ድኜያለሁ እያሉ ምስክርነት የሚሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ተመልሶ ችግር ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላሉ፡፡
ንጋት፡- የስኳር በሽታ ምልክቶቹ ምን ምንድን ናቸው?
ዶክተር ያደሳ፡- የስኳር በሽታ ምልክቶች አሉት፡፡ በብዛት በምልክት የሚገለጸው የስኳር በሽታ የመጀመሪያ ደረጃ አይነት ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ግን ምንም አይነት ምልክት ላያሳይ ይችላል፡፡ ምልክቶቹም ቁስል ቶሎ አለመዳን፣ ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፣ የውሃ ጥማት፣ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት፣ ቶሎ ቶሎ መራብና የመሳሰሉት ናቸው።
ንጋት፡- ስኳር በዘር የመተላለፍ እድሉ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ያደሳ፡- ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ በዘር የመተላለፍ አድሉ አለ፡፡ ነገር ግን ቤተሰብ ላይ ከሌለ በስኳር ላለመያዝ ዋስትና አይሆንም፡፡ አባት ወይም እናት የስኳር በሽተኛ ከሆኑ ልጁ የስኳር በሽተኛ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን በዘር ይተላለፋል ብለን መደምደም አንችልም፡፡ ከአንደኛው ይልቅ ሁለተኛው አይነቱ በዘር የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ቤተሰብ ላይ የስኳር በሽታ ባይኖርበትም ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዘው በልጆች ላይ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡
ንጋት፡- መጨራሻ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካልዎት?
ዶክተር ያደሳ፡- በሀገራችን የስኳር በሽታ ስርጭቱ በጣም እየጨመረ ነው፡፡ ከሁለት አመት በፊት የተጠናው ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ስርጭቱ 6.5 ከመቶ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ችግሩ በጣም እየገፋ መጥቷል፡፡ የአኗናር ዘይቤያችን ካልተስተካከለ ማንም ሰው አደጋ ላይ ነው ያለው፡፡
የስኳር በሽታን ፈጽሞ ማዳን ወይንም እንዳይከሰት ማድረግ ባይቻልም አጋላጭ ምክንያቶችን መቀነስ እንደሚቻል መታወቅ አለበት፡፡ የስኳር ታማሚው በሐኪም የታዘዘለትን መድኃኒት (በተለይ ኢንሱሊን) በየጊዜው ተከታትሎ መውሰድ ይጠበቅበታል።
የስኳር በሽታ አንዴ ከተከሰተ አመጋገባችንን በማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ በመድሃኒት መቆጣጠር እንጂ ማጥፋት ሰለማይቻል እነዚህን ተግባራት ማቋረጥ አያስፈልግም፡፡
በፋብሪካ ታሽገው የሚመጡ እንደ ፓስታ፣ ማኮሮኒ የመሳሰሉ ምግቦች አለማዘውተር ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚህ ባለፈ በየቀጠሮው ጤንነቱን መታየት፣ በሰውነት ውስጥ ያለን የኮሊስትሮል መጠን ክትትል ማድረግ ወይንም መለካት፣ ዓይን፣ እግርን፣ ኩላሊትን፣ ግፊትን በጤና ባለሙያ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
ንጋት፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ያደሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
ዓለማት ለምን እና እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ እየጣሩ ያሉት የ30 አገራት ሳይንቲስቶች
“የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ወደ ኢንደስትሪ ለማሻገር እየተሰራ ነው” – የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት
“ሥራህ ለራስህ አለቃ ነው” – ወ/ሮ መስታወት መስቀሌ