“የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ወደ ኢንደስትሪ ለማሻገር እየተሰራ ነው” – የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት

በካሡ ብርሃኑ

የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን እንደ ሃገር የታሰበውን ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ የመሻገር ውጥን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በሚሰራባቸው የሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚገኙ ከ322 በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕይዞች ጨምሮ የግል ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ የሚያሰችሉ ውጤታማ ሥራዎችን እየተሰሩ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገርማሜ ጋሩማ እንዳሉት ግብርናን ማሻገር/ትራንስፎርም ማድረግን ዓላማ አድርጎ መቋቋሙን አስታውሰው በመደበኛው የግብርና ሥራ ብቻ ዕቅዱን ማሳካት ስለማይቻል የዘርፉን ችግሮች በመለየትና በመፍታት ለሚመለከተው አካል የማስተላለፍ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

የሃገሪቱን 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መተዳደሪያ ግብርና መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ምርታማ ሆኖ ወደተሻለ ምዕራፍ ያልተሸጋገረው ለምንድን ነው የሚለውን በመፈተሸ በስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ሰሊጥና መሰል 11 ሰብሎች በመለየት እንደየክልሎቹ ነባራዊ ሁኔታ ዕቅዱ መተግበር መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የተለዩትን ሰብሎች ምርታማነት ለመጨመር በሚደረገው ጥረት 98 በመቶ የሚሆኑ አርሶአደሮች በተበጣጠሰ ትንንሽ ማሳ ላይ የሚዘሩት የተለያዩ ሰበሎች የዘርፉ ተግዳሮት እንደነበር ገልፀው ይህን ለመቀየር የክላስተር/ኩታገጠም አሰራርን እንዲተገብሩ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ማሳያ ያሏቸውን ተከታዪን ነጥቦች ጠቅሰዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ሥራ ሲጀምር ምንም ያልነበረውን የክላስተር አሰራር በማስለመድ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ አርሶአደሮች ማሳቸውን በኩታ ገጠም ማረሳቸውን እና ከ11 ሚሊየን ሄክታር በላይ ማሳ በአሰራሩ መሸፈኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ አሰራር በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ እምርታ እንዲመዘገብ እያደረገ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር በላይ አስተዋፅኦ ማድረጉን በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት በሰራቸው ሥራዎች የግብርና ዘርፍን አጠቃላይ ምርታማነት ማሻሻል ያስቻሉ 14 ፕሮጀክቶች በመተግበር የአርሶአደሩን ችግር ማቃለል መቻሉንም አመላክተዋል፡፡

ግብዓት የሚያቀርቡ፣ የኤክስቴንሽን ድጋፍ የሚሰጡ፣ ግብርናን በዘመናዊ መሳሪያዎች ማከናወን የሚያስችሉ የሚካናይዜሽን ማሽነሪዎችን የሚያቀርቡ እና ግብርና ቢዝነስ መሆኑን በመረዳት ሃገር ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያደርጉ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የሚስተዋሉ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር እጥረትን፣ የገበያ ችግር እና ከግብርና ግብዓት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የዕዳ አከፋፈል ችግርን መቅረፍ ያስቻለ ሥራ መሰራቱን እና በየሰብል ዓይነቱ የተመዘገበው ምርታማነት የተቋሙ ሥራ በስኬት የታጀቡ ሰለመሆናቸው ማሳያ ናቸው ሲሉ አንስተዋል፡፡ በዚህም ስንዴ ከነበረበት 30 ወደ 50 ኩንታል በሄክታር እንዲሁም 150 የነበረውን የአቮካዶ ምርታማነት በክላስተር አንዲመረት በማድረግ ወደ 450 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ይህን አፈፃፀም የግብርና ሚኒስቴር በመውሰድ በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች እንዲስፋፋ በየደረጃው ያሉ መዋቅሮችን በመጠቀም ውጤታማ ሥራ እየሰራ መሆኑን እና ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እያሳካ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በቀጣይም በ11 ሰብሎች የተጀመረውን ሥራ በማሳደግ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለሃገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርገውን ቡና ጨምሮ እንሰት፣ ዶሮ እርባታ እና የእንስሳት መኖ በማካተት ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

ይህን በማሳካት ግብርናውን ወደተሟላ ለውጥ በማሸጋገር በሃገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና  ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ብቻ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል፡፡

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል የአግሪ-ቢዝነስ ቡድን መሪ አቶ ተሰማ ሂርባዬ በበኩላቸው በግብርና ዘርፍ ያሉ አካላትን የእሴት ሰንሰለት በማጠናከር ውጤታማ እንዲሆኑ መደገፍ እና የማገዝ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመው የግል ሴክተሩ በተለይም ማህበራትና ኢንተርፕራይዞች ተሳትፎ እንዲያድግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አርሶአደሩ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በአቅራቢያቸው ማግኘት መጀመራቸውን ገልፀው በቀጣይም ዘርፉን ይበልጥ ማዘመን የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመተግበር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በኢኒስቲትዩቱ የአግሪሀብ ፕሮጀክት የኢንተርፕራይዝ የንግድ ሥራ ልማት እና ማጎልበቻ ከፍተኛ ባለሞያ ዶ/ር ሽመልስ አልታዬ በአንፃሩ የግብርና ዘርፍን ወደተሟላ ለውጥ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ተቋሙ የማይተካ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ኢንተርፕራይዞች፣ የግል ባለሃብቶች እና መንግስትን በማቀናጀት በተሰራው ሥራ የሚታዩ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል፡፡

በሲዳማ 55፣ ደቡብ ምዕራብ 35፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ 124 እና በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ 85 ኢንተርፕራይዞችና ማህበራት በተደረገላቸው ድጋፍ በተሰማሩበት የሥራ አማራጭ ውጤታማ በመሆን የግብርና ዘርፍ እንዲሻሻል የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ሰለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞቹ አሰራራቸውን በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት መሥጠት እንዲችሉ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንደሰጣቸው አስታውሰው ይህም የታለመውን የግብርና ዘርፍ የማዘመን ውጥን ዕውን ለማድረግ እያገዘ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ኢንተርፕራይዞቹና ማህበራቱ ሥራ ሲጀምሩ ከነበሩበት የግብዓት አቅራቢነት በተጨማሪ የተሟላ የሜካናይዜሽን አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል ማሽነሪ ማስመጣት የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን እና የዘር ብዜት የሚያከናውኑ ዩኒየኖችም ዘመናዊ ማሽን በመጠቀም የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ማርካት መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በሰራቸው ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች በርካታ ናቸው የሚሉት ዶ/ር ሽመልስ አርሶ አደሩ ግብዓት ለማግኘት ይጓዝ የነበረውን ከ35 ኪ.ሜ በላይ መንገድ በማስቀረት በአማካይ ከ3 እስከ 5 ኪ.ሜ በማውረድ አርሶ አደሩ ሙሉ ትኩረቱን ማሳው ላይ የሚያደርግበትን ሁኔታ መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ምርታማነትን ይበልጥ በማሳደግ እንደ ሃገር የተያዘውን ከግብርና መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ ኢንደስትሪ መር የማሸጋገር ውጥን ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡