“ሥራህ ለራስህ አለቃ ነው” – ወ/ሮ መስታወት መስቀሌ
አንድ ሰው ህይወቱን ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ዋጋ መክፈሉ ግድ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ ውጣ ውረዶች ማሳለፍ ይጠይቃል፡፡ በተለይ ደግሞ የተለያዩ ጊዜያዊ ፍላጎቶቻንን ወደ ጎን በመተው በዓላማ ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡
የዛሬዋ እቱ መለኛችን ራሷንና ቤተሰቧን ለመርዳት ስትል ከገጠር ወደ ከተማ መጣች። ከዚያም ከተቀጣሪነት ተነስታ በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ የራሷን “የሴቶች የውበት ሳሎን” መክፈት የቻለች እንስት ናት፡፡
ምንም እንኳን በልጅነቷ የልጆች እናት ብትሆንም ቀጣይ የሕይወት ታሪኳን እሷ እንደፈቀደችልኝና ከዕድሜዋ አኳያ አንቺ ለማለት ተገድጃለሁ፡፡ ቆይታችንን እንደሚከተለው ላካፍላችሁ፡፡
ወ/ሮ መስታወት መስቀሌ ትባላለች። የተወለደችው በወላይታ ዞን አረካ ከተማ ነው፡፡ በልጅነቷ መስቀል ሲደርስ የአካባቢዋ ሰዎች ወደ ከተማ ሄደው ራሳቸውን ቀይረው ቤተሰቦቻቸውን ሲረዱ ትመለከት ነበር፡፡
በልጅነቷ እያየችና እየሰማች ያደገችውን ያህል እሷም ሕይወቷ ተቀይሮ ቤተሰቦቿን ለማገዝ ከአረካ መውጣት ነበረባት፡፡ የምታውቃቸው ሰዎች ስለነበሩ ጉዞዋን መጀመሪያ ያደረገችው ወደ ሻሸመኔ ነበር፡፡ በዚያ ብዙም ስላልተመቻት ከሻሸመኔ ወደ ዲላ አመራች፡፡
መስታወት ራሷን ለመለወጥ ዲላ ከተማ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ጠንክራ መስራት ጀመረች። በስራ ላይ እያለች ከአንድ ሰው ጋር በስራ አጋጣሚ ተዋወቀች፡፡ ከዚያ ሰው ጋር ስለነበራት ግንኙነትና ወደ ሀዋሳ የመጣችበትን አጋጣሚ ስትናገር፦
“ዲላ በምሰራበት ጊዜ የአሁኑን ባለቤቴን ተዋወቅኩት፡፡ በጊዜ ሂደት ትውውቃችን ውሎ እያደረ በሁለታችንም ዘንድ እየጠነከረ ሲመጣ በአንድ ጣራ ስር ጎጆ ቀልሰን በጋራ ለመኖር ከስምምነት ደረስን፡፡ እሱ ሀዋሳ ይኖር ስለነበረ ትዳር መስርቼ ከዲላ ወደ ሀዋሳ ከተማ ከባለቤቴ ጋር አንድ ላይ መኖር ጀመርን” ስትል አጫውታናለች፡፡
“ሀዋሳ ከገባሁ በኋላ ሥራ አልነበረኝም። ከባለቤቴ ጋር ተነጋገርን፡፡ ‘ለምን የሴቶች የውበት ሳሎን ሙያ አትሰለጥኚም?’ የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔም በሀሳቡ ተስማማሁ። የሴቶች የውበት ማሰልጠኛ ገብቼ ሙያውን መሰልጠን ጀመርኩ፡፡
“ከዚያም ሙያውን በጣም እየወደድኩት መጣሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገርም ለውጦችን አመጣሁ፡፡ በወቅቱ ከእኔ ጋር ከጀመሩ ሰልጣኞች ይልቅ ፈጣን ለውጥ አሳየሁ፡፡ ሥራ ወዳድ እና ጎበዝ መሆኔን የተመለከተው አንድ የፀጉር ቤት ባለቤት እሱ ጋር ተቀጥሬ እንድሰራ ጥያቄ አቀረበልኝ” ስትል ወደ ሴቶች የውበት ስራ የተቀላቀለችበትን አጋጣሚ ታስታውሳለች፡፡
እሷም ጥያቄውን ተቀበለች፡፡ በወቅቱ ለሴቶች የውበት ሳሎን የሚከፈለው ከፍተኛ ደመወዝ 6 መቶ ብር መሆኑን አጫውታናለች። ጀማሪ ተቀጣሪ ሆና ነገር ግን ከፍተኛ ደመወዝ እየተከፈላት የሴቶች የውበት ሳሎን ሥራውን መስራት ጀመረች፡፡
“መጀመሪያ የተቀጠርኩበት የውበት ሳሎን ለ6 ወራት ከሰራሁ በኋላ ሁልጊዜ የተሻለ ነገር እፈልግ ስለነበር የተሻለ ቤት ማፈላለግ ጀመርኩ። ከምኖርበት ቤት ቅርብ በሆነ አንድ የውበት ሳሎን በ4 መቶ ብር ተቀጠርኩኝ” ትላለች፡፡
የወር ክፍያው አልቀነሰም ወይ? ብዬ ላነሳሁላት ጥያቄ ስትመልስ፦
“ሌሎቸ ጥቅማ ጥቅሞች ስለነበሩት ደመወዝ ቀንሼ ነው የተቀጠርኩት፡፡ በተለይም ደግሞ ሹሩባ ሲሆን ከባለቤቱ ጋር እኩል ነው የምካፈለው፡፡ ሁለት መቶ ብር ከሆነ ክፍያው አንድ መቶ ብሩን እኔ ነበርኩ የምወስደው፡፡
“ከዚያም ሥራውን በሚገባ ለመድኩት። ብዙ ሰው ተዋወቅኩበት:: ማበረታቻ ጉርሻ ይበረከቱልኝ ጀመር፡፡ እዚህ ቤት እየሰራሁ የመጀመሪያ ልጄን አረገዝኩ፡፡ ይህ ጊዜ ለእኔ በጣም ከባድ ነበር፡፡ የሴቶች የውበት ሳሎን ሥራ እና እርግዝና በጣም አስቸጋሪ ነው” ስትል ሁኔታውን አስታውሳናለች፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆና ሥራ ወዳዷ መስታወት ድካም፣ የእርግዝና ስሜቶችና ሌሎች ተገዳሮቶችን ተቋቁማ እስከ 8 ወር ድረስ በመስራት ለመውለድ አንድ ወር ሲቀራት ስራዋን አቋርጣለች፡፡
ወልዳ ከተነሳች በኋላም ወደ ሥራ የገባችበትን አጋጣሚ ስታስታውሰን፦
“1 ዓመት ከስድስት ወር ድረስ ወደ ሥራ አልተመለስኩም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ሰፈር ውስጥ አንድ የሴቶች የውበት ሳሎን ነበር፡፡ ስለምግባባቸው አንዳንዴ ወረፋ ሲበዛባቸው እየሄድኩ እነሱ ጋር እሰራ ነበር” ትላለች፡፡
የራሷን የሴቶች የውበት ሳሎን የከፈተችበትን አጋጣሚ ደግሞ ስታጫውተን፦
“የመጀመሪያ ልጄ ሁለት ዓመት ሲሞላው ወደ ህጻናት ማቆያ በማስገባት በቋሚነት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ፡፡ ሁለት የተለያዩ ፀጉር ቤቶች ከሰራሁ በኋላ ለምን የራሴን አልከፍትም የሚል ሀሳብ መጣልኝና ጉዳዩ ላይ ማሰላሰል ጀመርኩ።
“ተቀጥሬ እየሠራሁ ለውበት ሳሎን የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ቀስ በቀስ በሂደት እየገዛሁ አስቀምጥ ነበር፡፡ ብዙም ሳልቆይ የራሴን ‘መስቲ የሴቶች የውበት ሳሎን’ በመክፈት የዛሬ 7 ዓመት ሥራ ጀመርኩ፡፡” ትላለች፡፡
ተቀጥሮ መስራት እና በግል ሥራ ፈጥሮ ስለመስራት ልዩነቱን ስትናገር፦
“በጣም ልዩነት አለው፡፡ በራስህ ስትሰራ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ “ሥራህ ለራስህ አለቃ ነው፡፡” ነጻነት አለው፤ ገቢ ይጨምራል፤ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ እድል ትፈጥራለህ እና ሌሎችም ብዙ ልዩነቶች አሉ” በማለት ጥቅሙን አስረድታናለች፡፡
ወ/ሮ መስታወት የራሷን ሥራ ከጀመረች በኋላ ሁለተኛ ልጇን አረገዘች፡፡ ከሰራተኛ ጋር በመተጋገዝ ሥራዋን መስራት ቀጠለች፡፡ እስክትወልድ ድረስ ሥራ ትሰራ ነበረ፡፡ ይህ ማለት ቀኑን ሙሉ ሥራ ስትሰራ ቆይታ ማታ ወደ ቤት ትገባለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ማታ ከሥራ መልስ ወደ ቤቷ ከተመለሰች በኋላ ሁለተኛ ልጇን የተገላገለችበትን አጋጣሚ መቼም እንደማትረሳው አጫውታናለች፡፡
የሚገርመው ግን ሁለተኛ ልጇን በወለደች በ15ኛ ቀን ሥራ ቦታ በመሄድ መቆጣጠር መጀመሯ ነው፡፡ እስከ ሶስት ወር በዚሁ ሁኔታ ቤት ከቆየች ከሶስት ወር በኋላ ቀለል ቀለል ያሉ ሥራዎች መስራት ጀመረች፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መመለስ ችላለች፡፡
“አሁን ላይ አንድ ሰራተኛ በቋሚነት እየሰራች ትገኛለች፡፡ ነገር ግን ሥራ በሚበዛበትና የበዓላት ወቅት በጊዜያዊነት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች አሉኝ” ስትል ለሌሎች የፈጠረችውን የስራ እድል ተናግራለች፡፡
በተለይም ደግሞ መስታወት ከቤተሰብ ጋር ሥራ አጥ የሆኑ ሁለት ውንድሞቿን በማምጣት አንዱን የሴቶች የውበት ሳሎን ስልጠና እንዲወስድ በማድረግ ራሷ ጋር ቀጥራው መስራት ችሎ ነበር፡፡
እሷ ጋር በሚገባ ልምድ ካካበተ በኋላ የተሻለ ደመወዝ በአዲስ አበባ አግኝቶ መሄዱን እና ሁለተኛው ደግሞ እንጨት ቤት ተቀጥሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ እንደዚሁም ታናሽ እህቷን በዲግሪ ፕሮግራም እያስተማረቻት ነው፡፡
“ሴት ልጅ የባሏን እጅ ብቻ መጠበቅ የለባትም፡፡ በራሷ ጥራ ግራ ከቤት በመውጣት መስራት ይኖርባታል፡፡ ይህ ሲሆን ለጤንነቷም ሆነ ለቤተሰብ ሰላም ወሳኝነት አለው፡፡ ለሁሉም ነገር ባለቤቷን ገንዘብ አምጣ ማለት ይሰለቻል፡፡ ሁሉም ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ሌሎች ሰዎችን የመርዳት አቅም አላቸው ብዬ አምናለሁ” ስትል ምክር አዘል ሀሳቧን ሰንዝራለች፡፡
More Stories
ዓለማት ለምን እና እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ እየጣሩ ያሉት የ30 አገራት ሳይንቲስቶች
“የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ወደ ኢንደስትሪ ለማሻገር እየተሰራ ነው” – የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት
“የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር አመጋገብ የማዕዘን ድንጋይ ነው” – ዶክተር ያደሳ ተገኔ