የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በ3መቶ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አዲስ የውሃ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ በሀዲያ ዞን የሾኔ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በ3መቶ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አዲስ የውሃ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ በሀዲያ ዞን የሾኔ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አጥረት ለተለያዩ ችግሮች መዳረጋቸውን አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በከተማው በላሎ ገርቤ እና አረንቻ ቀበሌያት ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ላለፉት ረጅም ዓመታት ከፍተኛ እጥረት መኖሩን አንስተው የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ረጃጅም ኪሎሜትሮችን ለመጓዝ እንደሚገደዱ ተናግረዋል ።

ንጽህናቸው ያልተጠበቁ ወራጅ ወንዝና የታቆሩ ውሃዎችን በመጠቀም እነርሱም ሆነ ቤተሰቦቻቸው ለተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታዎች ሲዳረጉ መቆየታቸውንም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል ።

በቅርቡ በአካባቢያቸው የተገነቡ ጥቅት የውሃ ቧንቧዎች የችግሩን መጠን ቢቀንስም ከነዋሪዎች ከፍላጎት አንፃር ገና መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የችግሩ ሰለባ በሆኑ በእናቶችና በሴቶች እንዲሁም በህፃናት ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል ።

በአሁኑ ወቅት የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግር ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ የሚገኘው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን በማውሳት በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ዉሃ በፍጥነት እንዲዳረስ ጠይቀዋል ።

የሾኔ ከተማ አስተዳደር ውሃ አገልግሎት ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተሰማ ሄገኖ በከተማው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ፕሮጀክቶች ከ20 ዓመታት በፊት የተገነቡ በመሆናቸው አሁን ካለው የህዝብ ፍላጎት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ገልፀዋል ።

የከተማው የዉሃ አቅርቦት ከ35 ከመቶ ያልዘለለ መሆኑን ያነሱት ስራ አስኪያጁ ይህንንም ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ የሚያስችል ከ3መቶ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አዲስ የውሃ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮጀክቱም 1ነጥብ 6ሚሊዮን ሊትር መያዝ የሚችል ሁለት ግዙፍ የውሃ ታንከሮች ግንባታ ፤4 አዲስ ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ 40 ኪ.ሜ የውስጥ ለውስጥ መስመር ዝርጋታ ሌሎች የማጠቃለያ ስራዎች በመገባደድ ላይ ያለ ሲሆን ስራውም በአሁኑ ወቅት 92 ከመቶ መሻገሩን አቶ ተሰማ አስረድተዋል ።

የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበራ በዶሬ በበኩላቸው አስተዳደሩ የህብረተሰብን መሠረታዊ ችግሮችን ችግሮችን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በጋራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ህብረተሰቡን በማስተባባር እና በ”ማችንግ ፈንድ” ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኝ ሲሆን ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ስጀምር የከተማውን የውሃ ሽፋን ከፍ በማድረግ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከንቲባው አቶ አበራ አብራርተዋል።

ዘጋቢ ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን