“በእኔ ተስፋ የነበራት እናቴ ብቻ ነበረች” – ወጣት ሹኩሪ ኢብራሂም
በጋዜጣው ሪፖርተር
በሥራ አጥነት እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚፈተኑ አካል ጉዳተኞች በርካቶች ናቸው። ይሁንና አካል ጉዳተኝነታቸው ከህልማቸው ሳይገድባቸው አስቸጋሪ ፈተናዎቻቸውን ተጋፍጠው ለስኬት የበቁም ቁጥራቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ከእነዚህ መካከል የዛሬው የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን ይጠቀሳል፡፡ ትልቅ ቦታ የመድረስ ህልም ስለነበረው በልጅነቱ ረዥም መንገድ በዱላ ድጋፍ እየተጓዘ ነበር የሚማረው፡፡ ይህም ከበርካታ ተግዳሮቶቹ መካከል አንዱ ነው።
ስሙ ሽኩሪ ኢብራሂም ይባላል። ትውልድ እና ዕድገቱ ሀላባ ዞን ምዕራብ ጎርጣንቾ ቀበሌ÷ ልዩ ስሙ ወርቾ በሚባል የገጠር መንደር ነው፡፡ በልጅነቱ እንደ እኩዮቹ ከሰፈር ልጆች ጋር እየቦረቀ ይጫወት ነበር። ይሁን እንጂ ባልታወቀ ምክንያት እግሩ ላይ ጉዳት ደረሰበት፡፡
ድንገት ወድቆ እናቱ ሊያነሱት ሲሉ ግራ እግሩ አልዘረጋ እንዳላቸው ሲናገሩ ሰምቷል፡፡ ዘግይተው ወደ ህክምና ወስደውት ስለነበር ምክንያቱን መለየት አልቻሉም፡፡ ዶክተሮቹ በጊዜ ህክምና ቢያገኝ ተስፋ ይኖረው ነበር፥ በማለት እናቱ የነገሩትን ያስታውሳል፡፡
ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በ1997 ዓ.ም ትምህርት ቤት የገባ ሲሆን፥ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ሀላባ ዞን፥ አልቆጫ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡
በነበረበት አካባቢ ከ8ኛ ክፍል በላይ ትምህርት ቤት ስላልነበረ ከገጠር ወደ ከተማ እየተመላለሰ ነበር የሚማረው፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙ እንግልቶችን አሳልፏል፡፡ መመላለሱ ሲከብደው ችግሩን እንዲቀርፉለት የሚመለከታቸውን አካላት ድጋፍ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኝም፡፡
ይሁን እንጂ፥ በጎ ሰዎች አይጠፉምና ከቀበሌው ሊቀመንበር አቶ አህመድ አደም ጋር የሚገናኝበት አጋጣሚ ተፈጠረ። እየተመላለሰ መማሩን ሰምተው ከተማ ላይ ቤት ስለነበራቸው አንድ ክፍል ቤት እንደሰጡት ገልፆ 9ኛ ክፍልን ያለ እንግልት መማሩን አጫውቶናል፡፡
ሽኩሪ ገና በልጅነቱ ነበር ኑሮን ለማሸነፍ ይተጋ የነበረው፡፡ ገጠር እያለ የሰፈር ልጆችን ፀጉራቸውን አስተካክሎ ገቢ ያገኝ ነበር፡፡ ያ ልምድ ዳብሮ ከተማ ሲገባም ፀጉር ቤቶች ላይ በትርፍ ሰዓቱ እየሰራ መጠነኛ ክፍያ ማግኘት ጀመረ። በሚያገኘው ገንዘብ የቤት ኪራይ እየከፈለ 10ኛ ክፍልን ሀላባ መሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡
የ10 ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ጥሩ ውጤት አመጣ፡፡ ቀጥሎ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን እየተከታተለ በወላጆቹ አቅም ውስንነት ምክንያት ለማቋረጥ ተገደደ፡፡ ወላጅ አባቱ በልጅነቱ ነበር የሞቱት፡፡ እናቱ ደግሞ ምንም የገቢ ምንጭ አልነበራቸውም፡፡
ከ11ኛ ክፍል ወደ ኋላ ተመልሶ በ10ኛ ክፍል ወጤት በዲፕሎማ መርሃ-ግብር ለመማር ወሰነ፡፡ ተወዳድሮም አለፈ፡፡ ከዚያም ሀላባ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ለ4 ዓመታት ተከታትሎ በ2010 ዓ.ም መመረቅ ችሎዋል፡፡
“የሰፈር ሰው ሁሉ ተስፋ ቢቆርጥብኝም፥ እንደ እባብ አፈር ልሼ ህይወት ዘርቻለሁ። ዛሬ ላይ ለቁም ነገር በቅቻለሁ፡፡” ሲል የተናገረው በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡
“የሀላባ ዞን የአስተዳደር ፀሃፊ ሆኜ እየሰራሁ ነበር። ነገር ግን ፎቅ ላይ ስለነበር ምድር ይሻለዋል ብለው፥ ሀላባ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ላይ የመዝገብ ቤት ባለሙያ ሆኜ እየሠራሁ 7 ዓመታትን አስቆጥሬያለው” ሲል ቢሮ ላይ ልዩ እንክብካቤ እንደሚያደርጉለት ጭምር አጫውቶናል፡፡
“የሚያውቁኝ ሰዎች በሙሉ ተስፋ ቆርጠውብኝ ነበር። በእኔ ላይ ተስፋ የነበራት እናቴ ብቻ ነበረች፡፡ እንደምችል ሁሌ ጊዜ እየነገረችኝ ነው ያሳደገችኝ፡፡ ትምህርት ቤት ስትገባ ትጠነክራለህ ትለኝ ነበር” በማለትም በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ያስታውሳል፡፡
“እውነት ነው፤ ትምህርት ቤት ስገባ የተለየ ሰው ነበር የሆንኩት፤ ለእናቴ እድሜና ጤና ይስጣት፡፡ ዛሬ ላይ ራሴን በራሴ ማስተዳደር መቻሌ ልዩ ደስታ ይሠጠኛል” ሲል ፈገግታ በተላበሰ ሁኔታ ነበር ስሜቱን የገለፀልን፡፡
በአሁኑ ሰዓት የመንግሥት ሥራ ሰዓትን በማይሻማ መልኩ በትርፍ ጊዜው የራሱን የወንዶች ፀጉር ቤት ከፍቶ እየሠራ ይገኛል። “ረዥም ሰዓት በክራንች ተደግፌ መቆሙ ትንሽ ቢከብደኝም ሥራው ጥሩ ነው፡፡ ደስ ብሎኝ ነው የምሰራው” ሲል ለሥራው ያለውን ፍቅር ገልፆልናል።
“አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም። በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ ምክንያት በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ሊደርስ ይችላል። ጉዳት ካጋጠመ በኋላ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡ የበታችነት ስሜት ሊሰማን አይገባም፡፡ የሚለው ሹኩሪ፥ አክሎም የሰውን እጅ ከመጠበቅ፤ ሥራ ለመሥራት ተነሳሽ መሆን ያስፈልጋል” ሲል ምክረ ሀሳቡን ለግሷል፡፡
“ደግነት እራሱ ይከፍላል” እንዲሉ፥ መልካም ውለታ የዋሉለትን ሰዎች እንደሚከተለው አመስግኗል፦
“ሰው ይሆናል ብላ ትምህርት ቤት አስገብታ ሰው ያረገችኝ እናቴ ናት፤ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆናኛለች ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳት፡፡ እንዲሁም ከብዙ እንግልት ታድጎኝ ቤቱ ቁጭ ብዬ እንድማር ያገዘኝ አቶ አህመድ አደም ለሱም ምሥጋናዬ ይድረስ ብሏል፡፡
“ሌላው የሀላባ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ሙሉ ወጪዬን ችሎ አስተምሮኛል፡፡ በተለይ የኮሌጁ ኃላፊ ዶ/ር ኤፍሬም ዘለቀ ሁል ጊዜ የቸገረኝን በመጠየቅ ከገንዘብ የበለጠ የሀሳብ ድጋፉ ሳይለየኝ ተምሬ ጨርሻለሁ፡፡ ስለ ቀና ትብብሩ አመሠግናለሁ፡፡
“በመጨረሻም ሥራ ፍለጋ እንዳልንገላታ አስበው፥ ተረባርበው ለኔ በሚመች ቦታ ሥራ እንድቀጠር ለተባበሩኝ ሁሉ ምሥጋናዬ ይድረሳቸው” ሲል ምሥጋናውን ለባለውለታዎቹ አቅርቧል።
ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ረዥም ጊዜውን በዱላ ነበር የሚንቀሳቀሰው፡፡ በ2002 ግን አንድ ድርጅት የክራንች ድጋፍ እንዳደረገለት ገልፆ፤ እንደኔ ግንዛቤው የሌላቸው አካል ጉደተኞች ገጠር ላይ በርካታ ናቸው፡፡ እንደ ጉዳታቸው አይነት የሚመጣው ድጋፍና ዕድል ገጠር ድረስ ገብቶ ተደራሽ ቢሆን እና ገጠር ላይ ያሉ አካል ጉዳተኞች በማህበር ቢደራጁ የተለያዩ መረጃዎች ይኖሯቸዋል” በማለት ጠቁሟል፡፡
“እኔ ለምሳሌ ቀድሞ ስለ አካል ጉዳተኞች ማህበር ግንዛቤው አልነበረኝም። አሁን ላይ ግን የሀላባ ዞን አካል ጉዳተኞ ማህበር አባል ሆኜ ብዙ ልምዶችን አግኝቻለሁ” በማለትም ልምዱን ያገኘውን ጠቀሜት ገልጿል።
More Stories
ዓለማት ለምን እና እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ እየጣሩ ያሉት የ30 አገራት ሳይንቲስቶች
“የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ወደ ኢንደስትሪ ለማሻገር እየተሰራ ነው” – የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት
“የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር አመጋገብ የማዕዘን ድንጋይ ነው” – ዶክተር ያደሳ ተገኔ