በካሡ ብርሃኑ
“ዝቅ ብሎ የሠራ ቀና ብሎ ይሄዳል” የሚል ፅኑ አቋም አላቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከትንሽ የሰፈር ውስጥ ሱቅ ጀምሮ ያገኙትን ሥራ ሲሰሩ ያደጉት፡፡ ቤተሰባቸው ለንግዱ ዓለም ቤተኛ ቢሆኑም እሳቸው ግን ‹ለትምህርት ትኩረት ስጥ› በሚል ተፅዕኖ ምክንያት የልባቸው መሻት የሆነውን የንግድ ሥራ በልጅነታቸው መሰማራትና ማሳደግ አልቻሉም ነበር፡፡
መደበኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ኮሌጅ ሲገቡ ግን አንድ ውሳኔ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ከቤተሰብ የሚመጣውን ተፅዕኖ በመጋፈጥ የግል ሥራቸውን መጀመር ቀዳሚ ዕቅዳቸው አደረጉ። ነገር ግን የኮሌጅ ትምህርት ካጠናቀቁም በኋላ ያሰቡትን ነገር ማሳካት አልቻሉም፡፡ ይልቁንስ የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጣሪ በመሆን ዓመታትን ለማስቆጠር ተገደዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ዛሬ ለደረሱበት ስኬት ያበቃቸውን ሥራ የጀመሩት፡፡
የዛሬው ባለታሪካችን አቶ ተፈሪ በርዛ ይባላሉ በ1973 ዓ.ም በጋሞ ዞን፥ ምዕራብ አባያ ወረዳ ወዬ ባረና በምትባል የገጠር ቀበሌ ነው የተወለዱት። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በዚሁ ቀበሌ በሚገኝ ትምህርት ቤት እስከ ሦስተኛ ክፍል ተከታትለዋል፡፡
ሁለገብ የስራ ሰው የሆኑት አባታቸው በእርሻ እና ንግድ ሥራ የተሰማሩ ስለነበሩ ሥራቸውን ለማስፋት ወደ ብርብር ከተማ መግባታቸውን ተከትሎ ከ4ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት ብርብር ከተማ ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡
ምንም እንኳን አባታቸው በንግድ ሥራ ውጤታማ ሆነው ለብዙዎች የተረፈ አዱኛ ቢያካብቱም ልጆቻቸው በትምህርት እንዲገፉ ነበር ፍላጎታቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚመኙትን በንግድ ሥራ የመሰማራት ፍላጎት ገድበው አባታቸውን በማገዝ ልጅነታቸውን አሳለፉ፡፡
ይህን መሻታቸውን በልባቸው ይዘው የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው ሃዋሳ መምህራን ኮሌጅ ተቀላቀሉ፡፡ በኮሌጁ ኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ተመድበው በ1996 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ ይሁን እንጂ እንደተመረቁ እጀምረዋለሁ ያሉትን የንግድ ሥራ መጀመር አልቻሉም። ይልቁን በሲዳማ ክልል ሀገረ-ሠላም ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ተመድበው የሥራ ዓለምን በመምህርነት ተቀላቀሉ፡፡ በሀገረ-ሠላም ለሁለት ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ ጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ ዘፍኔ ከተማ ወደሚገኝ ትምህርት ቤት በማቅናት ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ2001 ዓ.ም የመንግስት ሥራ ለማቆም ወሰኑ፡፡
ውሳኔያቸውን እውን ለማድረግም ከትዳር አጋራቸው ጋር በመነጋገር ብርብር ከተማ መለስተኛ ሱቅ በመክፈት ጀመሩ፡፡ “ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍፃሜህ እጅግ ይበዛል” የሚለውን አምላካዊ ቃል በመተማመን ለዓላማቸው ስኬት ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡
የመንግስት ሥራ ለቀው የግል ሥራ መጀመራቸውን የተመለከቱ ብዙዎች “እነዚህ ሰዎች አበዱ እንዴ” ሲሉ ውሳኔያቸው ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ ሞክሩ፡፡ “ባልና ሚስት ከአንድ ምንጭ ይቀዳሉ” እንደሚባለው ሆነና ሚስት የባልን ጥረት በማድነቅ ከጎን ሆና በማበርታት አጋርነቷን በተግባር ማሳየት ጀመረች፡፡
ይህ መተሳሰብ ፍሬ አፍርቶ ሱቁን ወደ ህንፃ መሳሪያ በማሳደግ የስኬት መንገዳቸውን አሰፉ። በመቀጠልም ከጎኑ የጽሕፈት መሳሪያ መደብር በመክፈት ሁለት አሉ፡፡ ይሄኔ ውሳኔያቸውን የተጠራጠሩ ቤተሰቦቻቸው ሳይቀር በመደገፍ ያበረታቷቸው ጀመረ፡፡
አባትም ልጃቸው በትምህርት ብቻ እንዲዘልቅ የነበራቸውን ፍላጎት በመተው የእሳቸውንም ሥራ ደርቦ እንዲሰራ ኃላፊነት በመሥጠት አበረቱት፡፡ አደራውን የተቀበለው ባለታሪካችን አቶ ተፈሪም የተሰጣቸውን መክሊት በማትረፍ በከተማው አንቱ ከሚባሉ ባለሃብቶች ተርታ መሰለፍ ቻለ፡፡
በዚህ ወቅት ነው ዛሬ ከእኛ ጋር ለመገናኘት ምክንያት የሆነውን የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት የሚከፍቱበት ዕድል የተፈጠረው፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲቲዩት ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመነጋገር በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ተገቢ የሆነ የግብርና ግብዓት የሚያቀርብ ድርጅት ለማቋቋም ማስታወቂያ አወጣ፡፡
ማስታወቂያውን የተመለከቱት ባለታሪካችንም አመለከቱ፡፡ መስፈርት ላይ የተመሰረተውን ውድድር በማሸነፍ በ500 ሺህ ብር ካፒታል በ2013 ዓ.ም ብርብር የግብርና ግብዓት አቅርቦት ማዕከል በመመስረት የአካባቢውን አርሶአደር የሚጠቅምና የእሳቸውንም ገቢ የሚያሳድገውን ሥራ መሥራት ጀመሩ፡፡
ሥራውን ሲጀምሩ የአንድ ዓመት የሠራተኞችን ደመወዝ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሸን ኢኒስቲቲዩት የደቡብ ማዕክል ድጋፍ እንዳደረገላቸው በቆይታችን ነግረውናል፡፡ ኢኒስቲቲዩቱ አንድ አባት ልጁን እንደሚደግፍ ነው የደገፈኝ የሚሉት አቶ ተፈሪ በእነሱ ድጋፍና ክትትል እዚህ ደርሻለሁና ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“ከዚህም ባለፈ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በማመቻቸት የእኔንም ሆነ የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ውጤታማ እንድንሆን አድርጓል፡፡ በማዕከሉ የግብርና እና እንስሳት ጤና ባለሙያዎች እንደመኖራቸው ዕውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ተደጋጋሚ የሥልጠና መድረኮችን በማመቻቸት ደግፏል፡፡
ተቋሙ ገበያ ከማፈላለግ ጀምሮ ከተለያዩ ድርጅቶችና አስመጪዎች ጋር በማገናኘት ትልቅ ሥራ ሰርቷል የሚሉት አቶ ተፈሪ፥ ይህም አርሶ አደሩ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በጊዜ የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅታቸው የተለያዩ ኬሚካሎችን በማቅረብ በአካባቢው በስፋት የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ጨምሮ የሰብል ምርታማነት እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ይላሉ፡፡
የማዕከሉ መከፈት ከዚህ በፊት የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት የነበረውን ረጅም ውጣ ውረድ ከማስቀረት ጀምሮ ጥራታቸው የተረጋገጠ ግብዓት በተመጣጣኝ ዋጋ በቅርበት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ይህም የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ በመቆጠብ ሙሉ ትኩረታቸውን ሥራቸው ላይ እንዲያውሉ አግዟል፡፡ ከዚህም ባለፈ ማዕከሉ በሚያቀርባቸው የቦቆሎ፣ የጤፍ፣ የስንዴና መሰል ሰብሎች ምርጥ ዘር የአካባቢው አርሶ አደር ምርታማነት እንዲሻሻል በማድረግ የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ ነው ሲሉ በልበ-ሙሉነት ይናገራሉ፡፡
ይህን የማለታቸው ምክንያት ሲያስረዱም፦ ማዕከሉ ግብዓቶችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ማሳቸው ምን ያህል ስፋት እንዳለው፣ የአፈሩን ዓይነትና ሌሎች ሁኔታዎች ወርዶ በማየት አስፈላጊውን ሙያዊ ምክርና ድጋፍ መስጠቱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሥራው ሰፊ ከመሆኑ አንፃር ከፍ ያለ ካፒታል ቢፈልግም እሳቸው በ500 ሺህ ብር የጀመሩት ሥራ ዛሬ ካፒታሉ ወደ 20 ሚሊየን ብር አድጎ ለተጨማሪ የኢንቨስትመንት ሥራ መነሻ ሆኗል ሲሉ ማሳያ ያሏቸውን ሥራዎች ጠቅሰዋል፡፡
ከግብርና ግብዓት አቅራቢ ማዕከሉ በተጨማሪ በከተማው በካፌና ሬስቶራንት ዘርፍ በመሰማራት ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በዚሁ ከተማ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት መሥጠትን ታሳቢ ያደረገ ባለሦስት ወለል (G+3) ህንፃ በመገንባት ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ ራዕያቸውን በማሳካት ጎዳና ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የስኬት ምስጢሬ ብለው የሚጠቅሱት የተለየ ነገር ካለ ቢነግሩን የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው የሰጡን ምላሽ ለሌሎቻችን ትምህርት የሚሆን ነው፡፡ “የራስ ጥረት የስኬት ቁልፍ ነው” የሚል አቋም እንዳላቸው በማንሳት ሕይወታቸው በዚሁ መርህ መቀየሩን ያነሳሉ፡፡
“ከተለያዩ አካላት ድጋፍ ሊገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ድጋፉን ተጠቅሞ ወደ ውጤት መቀየር የግለሰብ ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ዝቅ ብሎ የሰራ ሰው ቀና ብሎ ይበላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ላይ ቀና ብዬ መሄድ የሚያስችል ስኬት ላይ ደርሻለሁ ብዬ መናገር ብችልም ካሰብኩት አንፃር ብዙ መሥራት ይጠበቅብኛል” ሲሉ ለተሻለ ስኬት አሁንም እየተጉ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በትንሽ የንግድ ሥራ የጀመሩት ሥራ ዛሬ ላይ የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት፣ የካፌና ሬስቶራንት እንዲሁም በዶሮ እርባታ በመሰማራት የኢንቨስትመንት ጎዳናን እንዲያስቡ አድርጎ ለአካባቢው አስተዳደር ሰፊ ቦታ እንዲጠይቁ አድርጓል፡፡ በዚህም የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል በመክፈት በአካባቢው የሚታየውን የዶሮ፣ የከብቶች እና መሰል የመኖ ችግር ለመቅረፍ አስበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ያቀዷቸውን ሥራዎች ተግባራዊ ለማድረግ የፋይናንስ /ካፒታል እጥረት ፈተና እየሆነባቸው መሆኑን ማንሳት እልባት ቢበጅለት መልካም ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ተፈሪ በአካባቢያቸው በሚከናወኑ የበጎ አድራጎት ሥራ ይታወቃሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ከማቋቋም ጀምሮ ለአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ግብዓት በመሥጠት ማሳቸውም ሆነ እነሱ ፆም እንዳያድር ማድረጋቸውን ያነሳሉ፡፡
ከዚህም ባለፈ መንግስት ለሚያቀርባቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎች ድጋፍ በጎ ምላሽ ከሚሰጡ ሰዎች ተርታም ስማቸው ይገኛል፡፡ ለሆስፒታል፣ ለመንገድ፣ ለስታዲየም እና መሰል ሥራዎች ያደረጓቸው ድጋፎች በጉልህ ከሚነሱት መካከል መሆናቸውን ከተበረከቱላቸው የምስክር ወረቀቶች ማየት ችለናል፡፡ መጥቀስ ያልፈለጓቸው በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ስለመኖራቸውም ነግረውናል፡፡
ባለታሪካችን በ2000 ዓ.ም በመሰረቱት ትዳር አምስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን እንደ ቤተሰብ ያላቸው ፍቅርና አብሮነት ተምሳሌት መሆን የሚችል መሆኑን የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡
ከባለቤታቸው ጋር ያለው መግባባት ለስኬታቸው አስተዋፅኦ ማድረጉ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነውና እሳቸውንም አናግረናቸው ነበር። የባለታሪካችን ባለቤት ወ/ሮ ዘማች ዱባ ይባላሉ፡፡ “ሥራ ወዳድና እራሱን ለሥራ የሰጠ ሰው መሆኑ እኔን አበርትቶኝ በመተጋገዝ እዚህ ደርሰናል” ሲሉ የስኬታቸው ሚስጢር መተሳሰብ መሆኑን አንስተዋል፡፡
“ዝቅ ብሎ የሰራ ቀና ብሎ ይሄዳል” ሲሉ ከባለቤታቸው ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያነሱት ወ/ሮ ዘማች፥ ጠንክሮ ሥራን ሳይንቁ መሥራት ለስኬት እንደሚያበቃ ባለቤቴ ማሳያ ነውና ከእሱ ተማሩ›› ሲሉ ባስተላለፉት መልዕክት እኛም ተሰናበትን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
More Stories
“የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ወደ ኢንደስትሪ ለማሻገር እየተሰራ ነው” – የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት
“የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር አመጋገብ የማዕዘን ድንጋይ ነው” – ዶክተር ያደሳ ተገኔ
“ሥራህ ለራስህ አለቃ ነው” – ወ/ሮ መስታወት መስቀሌ