በእግር ኳስ እብደት የተሞሉ ታሪኮች

በኢያሱ ታዴዎስ

ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ እንዳለው የሚነገርለት ተወዳጁ የዓለማችን ቁጥር 1 ስፖርት የሆነው እግር ኳስ፣ የማይታመኑ ገጽታዎችን በማስመልከት ይታወቃል።

ስፖርቱ አስቂኝ፣ ተዓምራዊ፣ አስደሳችና አሳዛኝ ክስተቶች እየተፈራረቁ የሚከሰቱበት መሆኑ ነው የተወዳጅነቱ ምስጢር። በዚህም እልፍ ክስተቶችን ማንሳት ይቻላል።

“ፍሎስ” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድረገጽ በአውሮፓዊያኑ ሰኔ 30/2023 “ሰባቱ የእግር ኳስ የእብደት ታሪኮች” በሚል ርዕስ የመረጣቸውን ክስተቶች ለአንባቢዎቹ አካፍሎ ነበር። እኛም ደግሞ ከሰባቱ የተመረጡትን እናካፍላችሁ።

ሃሪ ማጓየር በአንድ የውድድር ዘመን ከሁለት ክለቦች ጋር ከሊግ ወርዶ ነበር

እንግሊዛዊው የማንችስተር ዩናይትድ የመሃል ተከላካይ፣ እንደ ዛሬው ዝነኛ ከመሆኑ በፊት እምብዛም እውቅና አልነበረውም። ብቻም ሳይሆን ገደቢስ የሚባል ዓይነት ተጫዋች ነበር።

ከአንዱ ክለብ ወደ ሌላኛው በፍጥነት በመዘዋወርም ወደር አልነበረውም። ከሁሉም የከፋው ደግሞ ከሚጫወትላቸው ክለብ ጋር አብሮ በተደጋጋሚ መውረዱ ነው። ተጫዋቹ ከሼፊልድ ዩናይትድ፣ ሁል ሲቲ እና ዊጋን አትሌቲክ ክለቦች ጋር በተለያዩ ጊዜያት የመውረድ አደጋን ለመጋፈጥ ተገዷል።

ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ በአንድ የውድድር ዘመን፣ ከሁለት ክለቦች ጋር በተለያዩ የሊግ እርከኖች መውረዱ ነው። ነገሩ የተከሰተው በ2014/15 የውድድር ዘመን ነበር።

የውድድር ዘመኑን ለእንግሊዙ ሁል ሲቲ በ2 ነጥብ 5 ቢሊየን በመፈረም ነበር የጀመረው። የመጀመሪያ ጨዋታውንም በኢውሮፓ ሊግ የደርሶ መልስ ጥሎ ማለፍ ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታውን በማድረግ ነበር የተጫወተው። በፕሪሚየር ሊጉ ደግሞ ለአራት ወራት ያህል በአንድም ጨዋታ ሜዳ ውስጥ ሲጫወት አልታየም ነበር።

በሰባት ወራት ውስጥ በሁሉም ውድድሮች በሁል ሲቲ 6 ጨዋታዎችን ብቻ ካደረገ በኋላ፣ በዚሁ ውድድር ዘመን ወደ ሻምፒየንሺፑ ክለብ ዊጋን አትሌቲክ በውሰት አቀና። በዊጋን የተሻለ የመሰለፍ ዕድል አገኘ። ነገር ግን የውሰት ተጫዋቹ፣ ቡድኑን ወደ ሊግ አንድ (ታችኛው ሊግ) ከመውረድ ሊታደግ አልቻለም።

ዊጋን ከመጨረሻዎቹ 16 ጨዋታዎች በዘጠኙ ተሸንፎ ከሻምፒየንሺፑ ወረደ። በተመሳሳይ ወደ እናት ክለቡ ሲመለስ ሁል ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዷል። ይህም በወቅቱ ተጫዋቹን ገደቢስ አስብሎት ነበር።

የዚህን ያህል ዕድል ጠማበት የነበረው ተጫዋች ራሱን እያሳደገ በጊዜ ሂደት በ80 ሚሊየን ፓውንድ ታላቁን ማንችስተር ዩናይትድ በመቀላቀል ውዱ ተከላካይ ለመሆን በቅቷል።

ለብሄራዊ ቡድን እና ለክለብ በተመሳሳይ ቀን ለመጫወት የተገደደው ተጫዋች

ስሙ በተጫዋችነትም ሆነ በአሰልጣኝነት ከፍ ብሎ ይነሳል፤ ማርክ ሂውዝ። በተጫዋችነት ዘመኑ ለማንችስተር ዩናይትድ እና ቸልሲ ተጫውቷል። ከዚያም ለባርሴሎና።

በ1987 የክረምት ዝውውር ደግሞ የጀርመኑን ባየር ሙኒክ ተቀላቀለ። የጀርመኑን ክለብ እንዲቀላቀል የረዳው ኡሊ ሆነስ የተባለ ግለሰብ ነበር። ታዲያ ይህ ሰው አንድ ቀን እብደት የሚመስል ሃሳብ አመጣ። ባየር ሙኒክ በዕለቱ በጀርመን ካፕ ከሞንቼግላድባህ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ነበረው።

ማርክ ሂውዝ ደግሞ የዌልስ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች እንደ መሆኑ መጠን በዚያው ዕለት ለዩሮ 1988 ከቼኮዝሎቫኪያ (የአሁኗ ቼክ ሪፐብሊክ) ጋር በሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ የግድ መገኘት ነበረበት።

ኡሊ ሆነስ ከምንም ነገር በላይ ያጓጓው ሂውዝ ለባየር ሙኒክ ሲጫወት ማየት ነበር። ወደ ተጫዋቹም ቀርቦ የብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታ በዕለቱ ስንተኛው ሰዓት ላይ እንደ ሚደረግ ይጠይቀዋል። ሂውዝም ቀን ላይ እንደሚደረግ ይነግረዋል። ይሄኔ “በቃ ግድ የለም ጨዋታውን አድርግ እና ማታ ደግሞ ወደ ጀርመን ተጉዘህ ለባየር ሙኒክ ትጫወታለህ” ብሎ ያሳምነዋል።

በጨዋታውም ዕለት ወደ ቼክ ተጉዘው ሂውዝ የብሄራዊ ቡድን ግዳጁን ተሰልፎ በመጫወት ተወጣ። ጨዋታው እንዳለቀም ኡሊ ሆነስ እያጣደፈው ወደ ጀርመን እንዲጓዝ አደረገው።

ምሽት ላይ ስቴዲየም ሲደርሱ ሙኒክ ከሞንቼግላድባህ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጋምሶ ነበር። ሂውዝም በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ተሰልፎ ተጫወተ። ጨዋታውም በባየር ሙኒክ አሸናፊነት ተደመደመ።

አንድም ጨዋታ ሳያደርግ በአራት ዓለም ዋንጫዎች ላይ የተሳተፈው ተጫዋች

ጁሴፔ ቤርጎሚ ይባላል። አብዛኛውን የእግር ኳስ ሕይወቱን በጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ነው ያሳለፈው። በመሃል ተከላካይነት። ታዲያ ተጫዋቹ ከ18 ዓመቱ ጀምሮ ነበር ለጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት መጫወት የጀመረው።

በአጠቃላይ በ81 ጨዋታዎች ላይ ለብሄራዊ ቡድኑ ተሰልፎ ተጫውቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ በቡድኑ ጥሪ የተደረገለት በ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ነበር። በአንዱም ጨዋታ ሳይሰለፍ ቀረ። በ1986ቱ የዓለም ዋንጫም እንዲሁ ጥሪ ተደረገለት። በዚያም ምንም ጨዋታ ሳያደርግ ተመለሰ።

ጣሊያን ራሷ ያዘጋጀችው የ1990 የዓለም ዋንጫ ተከተለ። እንደ ልማዱ ቤርጎሚ ተጠራ። ነገር ግን አንድም የመጫወት ዕድል ሳያገኝ ቀረ። በ34 ዓመቱ ደግሞ ለ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ድንገተኛ ጥሪ ተደረገለት። አሁንም ለአንዲት ደቂቃ እንኳን የመጫወት ዕድል ሳያገኝ ውድድሩ ተጠናቀቀ።

በአጠቃላይ በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ በጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ተደረጎለት ቢቀላቀልም መጫወት እየናፈቀው ሳይጫወት የቀረ ታሪካዊ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

በሁለቱም እግሮቻቸው የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች

በእግር ኳስ ስፖርት ፍጹም ቅጣት ምት ቀላሉ ግብ ማስቆጠሪያ መንገድ ቢሆንም የአዕምሮ ጥንካሬ እና ስል እግሮች ይጠይቃል። ለዚህም ነው ለዚሁ ዓላማ ተብለው ተጫዋቾች የሚመረጡት።

ፍጹም ቅጣት ምት በሁለቱም እግሮቻቸው (በግራም በቀኝም) መምታት የሚችሉ ተጫዋቾች በእንግሊዘኛው “አምቢፔዳል” (Ambipedal) ተብለው ይጠራሉ።

ታዲያ ከዚሁ መነሻ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በሁለቱም እግሮቻቸው ፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠሩ ተጫዋቾች የቀድሞዎቹ ቦቢ ዛሞራ እና ኦባፌሚ ማርቲንስ ብቻ ናቸው።

ቦቢ ዛሞራ የግራ እግር ተጫዋች ነበር። የፉልሃም ተጫዋች በነበረበት በ2012 ከኒውካስል ጋር በተደረገ ጨዋታ ግን ፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶ በቀኝ እግሩ በመምታት ነበር ያስቆጠረው።

ናይጄሪያዊው ኦባፌሚ ማርቲንስ በበኩሉ በሁለቱም እግሮቹ መጫወት የሚችል ተጫዋች ነበር። በእንግሊዙ ኒውካስል ዩናይትድ ባሳለፈባቸው ሶስት ዓመታት ውስጥ በአንድ ጨዋታ ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት ግቦችን ሲያስቆጥር አንዱን በቀኙ፣ ሁለተኛውን ደግሞ በግራ እግሩ ነበር ያስቆጠረው።

በአንድ ጨዋታ በ3 ግብ ጠባቂዎች ላይ አንድ ተጫዋች ግብ አስቆጥሯል

ሚያዚያ 21/1986፣ 25 ሺህ ተመልካቾች በታደሙበት የአፕተን ፓርክ ስቴዲየም ጨዋታ ባለሜዳው ዌስትሃም እና ኒውካስል ዩናይትድ ተፋጥጠዋል፡፡ ኒውካስል ዋነኛ የግብ ጠባቂውን ማርቲን ቶማስ በቋሚነት አሰልፏል፡፡

ቶማስ ክለቡ ከዚህ ጨዋታ በፊት የነበረበት ግጥሚያ ላይ በትከሻ ጉዳት ምክንያት አልተሰለፈም ነበር፡፡ ሁለተኛው ግብ ጠባቂም ቶማስ ባልተሰለፈበት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ሲጫወት ጉዳት በማስተናገዱ ከዌስትሃም ጋር በነበረው መርሃ ግብር መሰለፍ አልቻለም፡፡

በዚህም ምክንያት ቶማስ ከዌስትሃም ጋር በሚደረገው ጨዋታ ከጉዳቱ ሙሉ በሙሉ ሳያገግም ነበር በቋሚነት የተሰለፈው፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ አጥቂው ኤልቪን ማርቲን ለዌስትሃም የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ፡፡ ቶማስ ግብ አስተናገደ ማለት ነው፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ቶማስ 2 ተጨማሪ ግቦችን ኒውካስሎች በራሳቸው ላይ ግብ ያስቆጠሩት ታክሎበት የጎል ዝናብ ወረደበት፡፡ ከዚህ በኋላ መቀጠል አልቻለም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የኒውካስሉ አማካይ ክሪስ ሄድወርዝ በግብ ጠባቂነት ተሰየመ፡፡ አይምሬው አጥቂ ማርቲን በሄድወርዝም ላይ ግብ አስቆጠረ፡፡ ከአማካይነት ወደ ግብ ጠባቂነት የመጣው ሄድወርዝ በጨዋታ መሃል ግብ ላለማስተናገድ ሲንደረደር የአንገት አጥንቱ ላይ ጉዳት አስተናገደ፡፡

ሄድወርዝ እንደ ምንም ሕመሙን ችሎ ወደ መሃል ስፍራው ተመለሰ፡፡ የኒውካስሉ ፒተር ብራድስሌይ ደግሞ ዘብ የመሆን ተራ ደረሰው፡፡ እሱም ሶስት ተጨማሪ ግቦች አስተናገደ፡፡ በ84ኛ ደቂቃ የተቆጠረችውም የመጨረሻዋ የዌስትሃም ግብ በቀበኛው ኤልቪን ማርቲን የተገኘች ነበረች፡፡ ዌስትሃምም ጨዋታውን 8ለ1 አሸነፈ፡፡ ማርቲንም በ3 የተለያዩ ግብ ጠባቂዎች ላይ ግብ በማስቆጠር ታሪክ ሰራ፡፡