በደረጀ ጥላሁን
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ታረቀኝ መናሞ ይባላሉ፡፡ ትውልድና እድገታቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን አንሌሞ ወረዳ ነው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የንግድ ሥራዎችን በመስራት ይታወቃሉ፡፡ አሁን ላይ የግብርና ግብአት አቅርቦትና አገልግሎት ማዕከላትን በመክፈት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በግብርና ግብዓት አቅርቦትና ስለሚሰሯቸው ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ!
ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ታረቀኝ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፦ የሥራ አጀማመርዎ እንዴት ነበር?
አቶ ታረቀኝ፦ ገና ወጣት ሳለሁ የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት እሞክር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንዳሰብኩት ቀላል አልነበረም፡፡ ሙከራዬን በመቀጠል ከማውቃቸው ሰዎች የተለያዩ እቃዎችን በማምጣት ገበያ ላይ አንጥፌ መሸጥ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያም ሀላባ ከተማ በመሄድ ከቦነሻ ሀላባ እንዲሁም ከሻሸመኔ በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጥ ቡና በመግዛት እሸጥ ነበር፡፡ በመቀጠልም በኬኒያ በኩል የሚገቡ የውስጥ ሱሪ፣ ጆሊ ጁስ የመሳሰሉትን እያመጣሁ በመሸጥ የተወሰነ ከሰራሁ በኋላ ወደ ልብስ መሸጥ ሥራ ገባሁኝ፡፡ እንዲህ እያልኩ የህንፃ መሳሪያ ሱቅ በመክፈት እና ሌሎችንም እየሰራሁ ቆይቻለሁ፡፡
ሥራዬን እየቀያየርኩ በመቀጠል የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን በመግዛት እና በመሸጥ እንዲሁም አገልግሎት በመስጠት እሰራ ነበር፡፡ በዚህ ሥራ ብዙ ነገር አይቼበታለሁ። ጥቅም ቢኖረውም ጉዳቱም ከፍተኛ ነበር። የመጋጨትና የመገልበጥ አደጋ ይደርሳል። እነዚህን ሁሉ አልፌ የተሻለ ሥራ ፍለጋ በሚል ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ፓስፖርት አወጣሁኝ፡፡ ከሀገር ወጥቼ ሥራ ለመስራት ያሰብኩት ሀሳብ ከአንድም ሁለቴ በቀጠሮዬ መሰረት ብገኝም ሳይሳካ በመቅረቱ ተመልሼ እንደቀድሞው የተለያዩ ሥራዎችን መስራቴን ቀጠልኩኝ፡፡
ንጋት፦ አሁን እየሰሩት ያለውን ሥራ እንዴት ጀመሩት?
አቶ ታረቀኝ፦ በ2012 ዓ.ም በሀዲያ ዞን አሊሞ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት በግብዓት አቅርቦት ዙሪያ ሥልጠና እንደሚሰጥ ተነገረኝ፡፡ ለሥልጠናው የሚያስፈልገውን መስፈርት በማሟላት ተካፈልኩኝ፡፡ ለሶስት ጊዜያት ሥልጠናውን ከተካፈልኩ በኋላ ቅጽ እንድሞላ ተደረገ፡፡ በወረዳው 17 ሰዎች ይህን ቅጽ ሞልተው ነበር፡፡ የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቼ ወደ ሥራ የገባሁት ግን እኔ ነኝ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በግብርና ግብአት አቅርቦት ሥራ ለመስራት ፍላጎቱ የነበረኝ ቢሆንም ሁኔታዎች ባለመመቸታቸው ነበር ሌላ ሥራዎች እሰራ የነበረው፡፡ አሁን ግን ይህ ፍላጎቴ በመሳካቱ ሥራውን በፍላጎትና በፍቅር እየሰራሁ እገኛለሁኝ፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርቼ ሰርቻለሁ፡፡ በጥቅም ደረጃ እነዚህ ሥራዎች ሊበልጡ ይችላሉ፡፡ ትልቁ እርካታዬ ግን ያለምኩትን ሥራ መስራቴ ነው፡፡ በዚህም ሥራ ህብረተሰቡን በተለይም አርሶ አደሩን ማገልገሌ ያረካኛል፡፡
ንጋት፦ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት ማዕከሉ ዓላማ ምንድ ነው?
አቶ ታረቀኝ፦ አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን የግብርና ግብአቶች በሙሉ እንዲያገኙ ማስቻል አንደኛው ነው፡፡ ሌላው የግብርና ግብአት ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ግብአት መጠንና ወቅቱን የጠበቀ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ምርትንና ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ ዘላቂነት ያለው ልማት ማረጋገጥ ነው፡፡ እንዲሁም የግብርና ግብአት ምንጮችን በማስፋትና አቅምን በመገንባት አስተማማኝ የአሰራር ስርአት በመፍጠር ለአርሶ አደሮች የግብአት ፍላጎት ማሟላት ነው፡፡
ንጋት፦ የአገልግሎት ማእከሉ ተግባር ምንድ ነው?
አቶ ታረቀኝ፦ ፎንቆ የግብርና ግብአት አቅርቦትና አገልግሎት ማእከል ለአርሶ አደሩ የተለያዩ ጸረ ተባይ እና ጸረ አረም መድሐኒቶችን፣ የአትክልት ዘሮች፣ የተለያዩ አነስተኛ የእርሻ መሣሪያዎች፣ የምርጥ ዘር ዓይነቶችን እንዲሁም የእንስሳት መድሐኒቶችና የእንስሳት መኖና ፉርሽካ የመሳሰሉትን ያቀርባል፡፡ በዚህ የአገልግሎት ማእከል የሚጠቀም ሁሉ በተቻለ መጠን ረክቶና ተደስቶ እንዲሄድ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ በዚህም ብዙዎቹ እርካታቸውን ይገልጹልናል፡፡ ‹‹በቤታችሁ መድሐኒት አይጥፋ›› ይሉናል፡፡ ትልቁ እርካታዬ ታዲያ ይህ ምርቃት ነው፡፡ በምንሰራው ሥራ የሽያጭ ሰራተኞችም ሆኑ የቤተሰብ አባላት ሁሉ አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
እንደሚታወቀው ለአርሶ አደሩ ለሥራው አስፈላጊ ከሆኑት ውስጥ ግብአት ዋናው ነው፡፡ ለዚህም የማእከሉ በቅርበት መኖር ግብአቶችን በቀላሉ እንዲያገኝ ያግዘዋል። የማእከሉ ባለሞያዎች ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ባሉበት አካባቢ በመሄድ እና ጉብኝት በማድረግ ችግሮች ካሉ ለመፍታት ይሠራል፡፡ ለዚህም ከወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ባለሞያዎች ጋር በመቀናጀት እየሰራን ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በየማእከላቱ በሚገኙ የሥልጠና ማእከላት በአመት ሁለት ጊዜ በቋሚነት ለሞዴል አርሶ አደሮች፣ በወረዳና በከተማው አስተዳደር ሥር ለሚገኙ ግብርና ባለሞያዎች እንዲሁም የየቀበሌ ሊቀመንበሮችን በማሳተፍ በግብአት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በዚህም ሥልጠና በአንድ ዙር ከ50 አስከ 60 የሚሆኑ ሰልጣኞች ይሳተፋሉ፡፡
ንጋት፦ የአገልግሎታችሁ ተደራሽነት ምን ያህል ነው?
አቶ ታረቀኝ፦ አገልግሎት የምንሰጠው በፎንቆ ከተማ አስተዳደር እና አሌሞ ወረዳ በሚገኙ ሁለት የግብርና ግብአት አገልግሎት ማእከላት እና በሶስተኛውና በቅርቡ ሥራ በጀመረው ማእከል ነው፡፡ በእነዚህ ማእከላት የአሌሞ ወረዳ ብቻ ሳይሆን በአጎራባች ዞኖች ከምባታ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ የሚገኙ ወረዳዎች አገልግሎቱን ያገኛሉ፡፡ ደስታችን ተጠቃሚዎች በማእከላችን መጥተው የሚፈልጉትን ማግኘት መቻላቸው ነው፡፡
አሁንም በማእከላችን የተለያዩ ምርጥ የበቆሎ ዘሮች እያሰራጨን ሲሆን በተለይ በዞኑ በተሰጠን ውክልና ደኬ 777 በቆሎ ምርጥ ዘር በብቸኝነት እያከፋፈልን እንገኛለን፡፡ እንዲሁም ከግንቦት አጋማሽ በኋላ ደግሞ ስንዴ፣ ጤፍ እና ገብስ ምርጥ ዘሮች ለተጠቃሚዎች ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ ደኬ 777 በቆሎ ምርጥ ዘሮች ለማግኘት ከአጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ በርካታ አርሶ አደሮችን እያስተናገድን እንገኛለን፡፡
ንጋት፦ የግብርና ግብአትን የምታመጡት ከየት ነው?
አቶ ታረቀኝ፦ የግብርና ግብአት አቅርቦትን በተመለከተ ቀደም ሲል በዘር አቅርቦትና ሌሎች ግብአቶች ለማከፋፈል እውቅና ከተሰጣቸው ድርጅቶች እናገኛለን፡፡ የምርጥ ዘር ድርጅቶች፣ ኬሚካል አስመጪዎችና ከሌሎችም በማስመጣት ለአርሶ አደሩ እናቀርባል፡፡ በአንዳንድ ግብአቶች ላይ እጥረቶች የሚታይ በመሆኑ በበቂ መጠን እንድናገኝ ቢሰራ ጥሩ ነው፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት የሚያደርጉትን ክትትል አጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም ነው፡፡ በአንዳንድ ግብአቶች ላይ እጥረት ሲፈጠር አርሶ አደሩን ከሥራው እንዳያስተጓጉለው በተቻለን አቅም ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን፡፡
የምናቀርበው ምርጥ ዘር ትክክለኛ ስለመሆኑ አርሶ አደሩ እንዲያውቀው የሰርቶ ማሳያ እርሻ አለን፡፡ በዚህም የተለያዩ ዘሮችን በመዝራት ውጤቱን እንዲመለከቱ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም የግብርና ባለሞያዎች ከማእከሉ ሰራተኞች ጋር በቅንጅት ሰርተው ያሳያሉ፡፡ ይህም አርሶ አደሩ ምርጥ ዘሩ ምን ያህል ውጤት እንዳለው ለመገንዘብ ይረደዋል፡፡
ንጋት፦ ሥራው ስኬታማ እንዲሆን የተደረገ እገዛ ካለ?
አቶ ታረቀኝ፦ ለግብርና ሥራ ውጤታማነት በሀገር ደረጃ እየተሰራ ያለው ሥራ የሚያስመሰግን ነው፡፡ አሁን ለደረስንበት ደረጃ በተለይ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ከፍተኛ እገዛ አድርገውልናል፡፡ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሰው ሀይላችን በቂ እውቀት ኖሯቸው እንዲሰሩ ለማስቻል በተለያዩ ጊዜያት ሥልጠናዎችን በመስጠት ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል፡፡ የምንሰራውን ሥራ የተቋሙ አመራሮችና ሞያተኞች በተለያዩ ጊዜያት በማእከላችን በመገኘት ያሉብንን ችግሮች በመከታተል ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ግብርና ሚንስቴር፣ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሁም የዞንና የወረዳ ግብርና መዋቅሮች የሚያደርጉት ሞያዊ ክትትልና እገዛ ለሥራችን ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጎልናል፡፡
ከዚህ ሌላ ከተለያዩ ባንኮች ጋር አብረን እየሰራን ሲሆን በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ባስፈለገኝ ጊዜ ያለምንም ማመንታት የሚስተናግደኝ በመሆኑ ለሥራችን መቀላጠፍ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡
ንጋት፦ የወደፊት አቅዳችሁ ምንድ ነው?
አቶ ታረቀኝ፦ ለወደፊቱ የያዝነውን ዓላማ ለማሳካት ቅርንጫፍ ማእከሎችን ማስፋት እንፈልጋለን፡፡ ከሁለቱ ማእከሎች ሌላ ሶስተኛው ላፍጦ ሌንቃ በሚባል አካባቢ የተከፈተ ሲሆን አራተኛውን ሆሳእና ከተማ ለመክፈት ፈቃድ አግኝተናል፡፡ ለማእከሉ የሚሆን ቤት የተዘጋጀ ሲሆን የባለሞያ ቅጥር ተደርጓል፡፡ በቅርቡ ግብአት በማስገባት ሥራ የምንጀምር ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዘር ብዜት ሥራ ለመጀመር ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡
እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥራታቸውን የጠበቁ የግብርና ግብአቶችን እና ቴክኖሎጂን በማቅረብ የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻል እንሰራለን፡፡
ንጋት፦ ማእከሎቹ ምን ያህል ሰራተኞች አሉት?
አቶ ታረቀኝ፦ በማእከሎቻችን ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ አድል ተፈጥሯል፡፡ አግሮኖሚስት፣ የእንስሳት ሀኪም፣ የሽያጭ ሰራተኞች እንዲሁም ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ አስራ አንድ ቋሚ ሰራተኞች ሲገኙ እነዚህም በቂ እውቀት ያላቸውና በዘርፉ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ በጊዚያዊነት የሚሰሩ ቁጥራቸው የሚጨምርና የሚቀንስ የተለያዩ ሰራተኞችም ይሳተፋሉ፡፡
በዚህ ሥራ የተሳተፉ ሰራተኞች የተሻለ ሥራ ለመስራት የሚያስችላቸውን እውቀት እንዲጨብጡ በራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት በሂሳብ አያያዝና በሌሎችም ዘርፎች ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም ለሥራው ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው መረዳት ይቻላል፡፡
ንጋት፦ የደረሱበትን የሀብት /የንብረት/ መጠን ቢገልጹልን
አቶ ታረቀኝ፦ ሰው ጠንክሮ ከሰራ መድረስ ያለበት ቦታ ላይ መድረስ ይችላል። ለዚህም ህግና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ተሰርቶ የተገኘን ሀብትም በአግባቡ ከተጠቀምን መለወጥ እንችላለን፡፡ እኔ እስካሁን በሰራሁት ሥራ ቁሳዊ ሀብት አፍርቻለሁ፡፡ አሁኑ ላይ በፎንቆ ከተማ አስተዳደር ነዳጅ ማደያ በማስገንባት ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን ለዚህም ነዳጅ ማምጫ የሚሆን አንድ የነዳጅ ቦቴ መኪና እንዲሁም ሲኖ ገልባጭ ተሸከርካሪ አለኝ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህንፃ መሣሪያ መሸጫ ሱቅም አለኝ፡፡
ንጋት፦ በበጎ አድራጎት ሥራ እንደሚሳተፉ መረጃ ደርሶኛል ይህን እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ታረቀኝ፦ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንሳተፋለን፡፡ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ልማትና ህብረተሰቡን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡ በዚህ መሰረት አቅመ ደካሞችን እንረዳለን፡፡ ለመማር የተቸገሩ ተማሪዎችን የማገዝ ሥራ እንሰራለን። ከዚህ በተጨማሪም በእርሻ ሥራው ላይ ዘር ዘርተው ግብአት መግዛት ያቃታቸውን አርሶ አደሮች እንረዳለን፡፡ ግምባር ቀደም የሆኑ አርሶ አደሮችንም እናበረታታለን፡፡
ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ታረቀኝ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
ዓለማት ለምን እና እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ እየጣሩ ያሉት የ30 አገራት ሳይንቲስቶች
“የግብርናን ዘርፍ በማዘመን ወደ ኢንደስትሪ ለማሻገር እየተሰራ ነው” – የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት
“የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር አመጋገብ የማዕዘን ድንጋይ ነው” – ዶክተር ያደሳ ተገኔ