ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የንግዱ ማህበረሰብ የድርሻውን እንዲወጣ የካፋ ዞን አስተዳደር ጥሪ አቀረበ
”የብልጽግና ጉዞአችንና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና” በሚል መሪ ቃል ዞን አቀፍ የነጋዴዎች ዉይይት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፤ ለኢኮኖሚው ዕድገት የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ምርት ማሸሽና ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ በንግዱ ማህበረሰብ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መሆናቸውን ያብራሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህ ድርጊት በቀጣይ ሊታረም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ነጋዴዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ማህበረሰቡም የግብይት ስርዓቱን በዲጂታል ማከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስፋፋት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠንና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ መንግስት ነዳጅ፣ መድኃኒትና መሰል ግብዓቶች ላይ ድጎማ እያደረገ መሆኑን አንስተው፤ ይህንንም በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ ኃይሌ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በምታደረገው ርብርብ ውስጥ የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ለግብርና ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እየተቻለ ነው ብለዋል::
የዞኑ ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መሸሻ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ እየተደረገ ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማ እንዲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በዞኑ ከ20 ሺህ በላይ ነጋዴዎች መኖራቸውን አብራርተው ህጋዊ አሰራርን በመከተል ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በውይይቱ የተገኙት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ ዕድገት እየታየ መሆኑን አንስተው በቀጣይ የንግዱ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
የህገ-ወጥ ነጋዴዎች መበራከት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ማነቆ መሆኑን በማብራራት ህጋዊ ለማድረግ ተቀናጅተው መስራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ሀብታሙ ኃይሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በጂንካ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡ ህጻናትን ሥራ ዕድል እንዲያገኙ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ ድጋፍ ከ2.6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በከምባታ ዞን ለሀምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ከልማት አጋሮች የሚገኘውን የበጀት ድጋፍ ለታለመለት አላማ በማዋል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ