በመዘርጋት ላይ ያሉ የመስኖ አውታሮች ሲጠናቀቁ ምርታማነት ይበልጥ እንደሚያሳድጉ ተገለጸ

በመዘርጋት ላይ ያሉ የመስኖ አውታሮች ሲጠናቀቁ ምርታማነት ይበልጥ እንደሚያሳድጉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመዘርጋት ላይ ያሉ የመስኖ አውታሮች ሲጠናቀቁ በክልሉ የሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ምርታማነት ይበልጥ እንደሚያሳድጉ የክልሉ መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እና ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በመቀናጀት በወላይታ ዞን የሚገኘውን የጭሮ መካከለኛ መስኖ ዝርጋታ ያለበትን ደረጃ ተመልክቷል።

በ462 ሚሊዮን 255 ሺህ ብር በደቡብ ኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመገንባት ላይ የሚገኘው ፕሮጀክቱ ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ1ሺህ በላይ ሔክታር መሬት ከማልማትም በተጨማሪ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በመፍጠር ለዓሳ ሐብት ልማት የሚኖረው ጠቀሜታ የላቀ መሆኑ ታውቋል።

በክልሉ በማሌ ወረዳ የሚገኘው የጉዶ በዞ እና በቡሌ ወረዳ የሚገኘው የአላ ዲቻ አነስተኛ የመስኖ ዝርጋታ ሥራዎች ተጠናቅቀው ለህብረተሰቡ ጥቅም እየሰጡ መሆናቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖ እና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ምክትልና የመስኖ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጥላሁን ጠቁመው፥ በመዘርጋት ላይ ያሉ የመስኖ ሥራዎች ሲጠናቀቁ የኢኮኖሚያ ተጠቃሚነትን ይበልጥ የሚያጠናክሩ በመሆናቸው በትኩረት እየተመራ ነው ብለዋል።

በቀድሞ ክልል መዋቅር የተጀመሩ የመስኖ አውታሮችን ለማጠናቀቅ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የጥናትና ዲዛይን ሥራ እየተሠራ መሆኑን አቶ ተመስገን ገልጸው፥ በውሃ ሐብት እና ሊለማ የሚችል ምቹ መሬት ያለበት ክልል እንደመሆኑ የመስኖ ዝርጋታ ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በበጀት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በክልሉ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ወጪ 9 የመስኖ ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም የቢሮ ምክትል ሀላፊው አብራርተዋል።

ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባምንጭ ጣቢያችን