በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ

በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ

ለወጣቶቹ 161 ሄክታር መሬት መሰጠቱን የወረዳው ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት አስታውቋል።

የዛላ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ሞነ፤ በወረዳው በ2017 በጀት ዓመት 4 ሺህ 600 ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ልየታ ተደርጎ 97 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑትን በሶስቱ ዕድገት ተኮር ዘርፎች ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል ብለዋል።

ለዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ዋስትና እንዲሆኑ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው ተደራጅተው ወደ ሥራ ለገቡ ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለወጣቶች በገጠር ዘርፍ ሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው በአንድ ቀን ጫጩት፣ በእንቁላል ጣይ ዶሮ፣ በበሬ ድለባ፣ በፍየል እርባታና ማሞከት፤ በአርቲ እና በቆሎ ሰብሎች ልማት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለእነዚህ ወጣቶች 161 ሄክታር መሬት ተሰጥቷቸው እንቅስቃሴ በመጀመር ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በበሬ ድለባ ከተደራጁት ወጣቶች መካከል ወጣት ትንቢተ ቲፌ፣ አምስት አባላት አራት በሬዎችን በማድለብ በሶስት ወር 200 ሺህ ብር ትርፍ ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።

በበቆሎ እርሻ የተሰማሩት ወጣቶችም በተሰጣቸው 2 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ከ85 ኩንታል በላይ ምርት እየጠበቁ መሆናቸውን የሜላ ካይሻ አንድነት ዲቻ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት የሱፍ ቦላዶ ገልጿል።

ወጣት ጊዳ ጋሻው በአርቲ ልማት በመሳተፍ ማህበራቸው የተሻለ ምርትና ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁሟል።

የወጣቶችን የስራ እንቅስቃሴ የጎበኙት የዞኑ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ አመራሮችና ባለሙያዎች በወረዳው ወጣቶችን ወደስራ ለማስገባት የተጀመረውን ተግባር አድንቀዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን