ከመሀረብ መንካት እስከ ኦሎምፒክ ሪባን ማቋረጥ

ከመሀረብ መንካት እስከ ኦሎምፒክ ሪባን ማቋረጥ

በአንዱዓለም ሰለሞን

አገሬን አየሁዋት ሰው ሀገር ሰማይ ላይ
ከኦሎምፒክ ህዋ ከዓለማችን በላይ
ቀስተ ደመና አስራ፣ መቀነት ቀንታ
በወግ ተቆጣጥራ፣ የዓለምን ተርታ
አገሬን አየሁዋት፣ ሰማይ ወጥታ አትላንታ፤

በማራቶን ዳገት ሩጫ ጎልጎታ፡፡
ግጥሙ ነፍሱን ይማረውና ደራሲ ነብይ መኮንን በአትላንታ ኦሎምፒክ የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉ አትሌቶቻችን ከቋጠረው የስንኝ ቋጠሮ የተቀነጨበ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1996 አትሌቶቻችን አትላንታ ላይ በድል ሲደምቁ፣ በተወዳጁ የማራቶን ስፖርት ታላቅ ገድል የፈጸመች አንዲት አትሌት የቡድኑ አባል ነበረች፤ ጀግናዋ አትሌት ፋጡማ ሮባ፡፡

የአትሌቷ የአትላንታ ድል በእርግጥም ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነበር፡፡ ለምን ቢሉ፤ እርሷ በማራቶን የሩጫ ውድድር ለሀገራችን ሴት አትሌቶች ፈር ቀዳጅ ነችና፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ድሉ የሀገር ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት ጭምር ያደረጋት ነበር፡፡ ለዚህም ነው አትሌቷ ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት የማራቶን አሸናፊ ካስባላት ድል በኋላ እንዲህ በማለት የተናገረችው፡-
“ይህ ድል የተለየ የሚሆነው ለእኔ ብቻ አይደለም፤ ለሀገሬና ለመላው የአፍሪካ ሴቶች እንጂ፡፡”

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ፣ በአንድ ወቅት በሰጠችው ቃለ ምልልስ ላይ በሀገሯ በማራቶን ዓርአያ የሆነቻት ሴት አትሌት ስለመኖሯ ስትጠየቅ እንዲህ በማለት ነበር የመለሰችው፡-
“ከሴቶች ማንም አልነበረም፡፡ የማውቀው ሁላችንም ስለእሱ ስንሰማ ያደግነውን አበበ ቢቂላን ብቻ ነበር፡፡ ልጆች ሳለን በራዲዮ የእርሱን ስም እንሰማ ነበር፡፡ ተማሪዎችም ስለእሱ ያወሩ ነበር” ብላለች፡፡

የውድድሩ እለት፣ በአሜሪካዋ ከተማ የነበረው የዓየር ጸባይ ሞቃታማና ጭጋጋማ ነበር፡፡ በዚያ ላይ በውጣ ውረድ የተሞላ የመሮጫ መስመር፡፡ ውድድሩ የሚካሔድበት ጎዳና 31 በመቶ ዳገታማ፣ 33 በመቶ ቁልቁለታማ ሲሆን የተቀረው 36 በመቶ ነበር ከዚህ ነጻ (ሜዳማ) የነበረው፡፡ ከዚህ ባሻገር፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፉ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ከመወዳደሪያው መም ፊት ለፊት ተሰልፈው ነበር፡፡ ስፔንን፣ ሩሲያን፣ ጃፓንን እና አሜሪካን የወከሉት አትሌቶች ከፍ ያለ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት አግኝተው ነበር፡፡ ከአፍሪካ ኬንያ በቲጋላ ላውሮፔ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በፋጡማ ሮባ ተወክለዋል፡፡

በዚህ የተነሳ፣ ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት በተገመተውና አውሮፓዊያን አትሌቶች ከተሳታፊዎቹ ግማሹን ቁጥር በያዙበት በዚህ ውድድር፣ ድሉ ሳይታሰብ ለአፍካና ለአፍሪካዊያን ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ በድንቅ ልጇ በወርቅ ተሸለመች፡፡

ሩጫው እንደተጀመረ ጀርመናዊቷ ዑታ ፒፒግ መምራት ጀመረች፡፡ ከ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ በኋላ፣ አምስት ተወዳዳሪዎች ማለትም ሩሲያዊቷ ቫሌንቲና ዮጎሮቫ፣ የእኛዋ ፋጡማ ሮባ፣ ሩማኒያዊቷ ሊዲያ ሲሞን፣ ጀርመናዊቷ ዶሬ ሔይንግ እና ፖርቱጋላዊቷ ማኑኤላ ማቻዶ መሪዋን አትሌት ተከትለው፣ በጥሩ ብቃት ከፊት ተገኙ፡፡

17ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ፋጡማ ጀርመናዊቷን አትሌት (ፒፒግን) በመቅደም የመሪነቱን ስፍራ ያዘች፡፡ 20ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ደግሞ ከሚከተሏት አትሌቶች በ6 ሰከንዶች ቀድማ መምራት ጀመረች፡፡ በዚህ ጊዜ ጃፓናዊቷ ዩኮ አሪሞሪ እና ፒፒግ ወደኋላ ቀሩ፡፡

ውድድሩ 30ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ሲደርስ፣ ፋጡማ ከሚከተሏት አትሌቶች ያላት ልዩነት እየሰፋ ሄደ፡፡ ከተፎካካሪዎቿ በ61 ሰከንድ ልዩነት ላይ ትገኝ የነበረችው አትሌቷ፣ ለብቻዋ ወደፊት ትገሰግስ ጀመር፡፡ 40ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ከምትከተላት አትሌት በ105 ሰከንድ ልዩነት የምትሮጠው ጀግናዋ አትሌት፣ በመጨረሻም ውድድሩን 2:26:05 በመፈጸም የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቃች፡፡ ይህም በወቅቱ በስፖርቱ የሀገሯን ክብረ ወሰን የያዘችበት ሰዓት በመሆን ተመዘገበ፡፡ በ1992 የባርሴሎና ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው ሩሲያዊቷ የጎሮቫ 2:28:05 በመግባት የብር ሜዳሊያውን ስትወስድ፤ አሪሞሪ ውድድሩን 2:28;39 በመፈጸም ለጃፓን የነሀስ ሜዳሊያ አስገኘች፡፡

ሀገራችን በማራቶን በሌላ ድል ታሪክ ሰራች። ሳቅና ደስታም በኢትዮጵያ ምድር ሆነ! ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ፤ የነብይ መኮንን ስንኞች የሚታወሱት፡-
“አገሬን አየሁዋት ሰው ሀገር ሰማይ ላይ
አረንጓዴ ለብሳ፤
ዐደይ ተከናንባ፤
ደሞም ደማም ኩታ፡፡”
በወርሀ ህዳር 1973 ወደዚህች ምድር ለመጣችው አትሌት ድሉ ታላቅ ቢሆንም፣ እንዲህ በቀላሉ የተገኘ ግን አልነበረም፡፡ በስፖርቱ በብዙ ውጣ ውረድ አልፋ፣ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን ተሻግራ ነበር ይህን ጣፋጭ ድል ለማጣጣም የበቃችው፡፡ ይህም አርዓነቷን ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርገው ነው፡፡

በልምምድ ወቅት ጥሩ እንደምትሰራ በአሰልጣኞቿ የተመሰከረላት፣ ግን ደግሞ በውድድሮች ላይ ከልምምዷ በተቃራኒ ውጤት ለሚርቃት፣ የመሮጫ ጫማ ተቸግራ ከሌላ አትሌት በመዋስ እስከመሮጥ ደርሳ ለነበረችው አትሌት በእርግጥም ድሉ ከስኬትም በላይ ነበር፡፡

በቀድሞ አርሲ ዞን፣ ሌሙና ቢልቢሉ ወረዳ፣ ሁሉሌ ካራ በሚባል ቦታ ተወልዳ ያደገችው ይህች ጀግና አትሌት፣ ስፖርቱን የጀመረችው በታዳጊነቷ በትምህርት ቤት ሳለች ነበር፡፡ “በወቅቱ ስለስፖርቱ ምንም ግንዛቤ አልነበረኝም፤ የስፖርት አስተማሪያችን በስፖርት ክፍለ ጊዜ ከሚያሰራን ስፖርት ውጪ” የምትለው አትሌት ፋጡማ፣ “የመሀረቧ ጨዋታ” የስፖርቱ ጅማሬዋ መሆኗን ትናገራለች፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፦

በስፖርት ክፍለ ጊዜ የስፖርት አስተማሪያቸው መሀረብ ይዞ መሀል ሜዳ ላይ በመቆም በተቃራኒ አቅጣጫ በመሮጥ ቀድሞ መሀረቧን የነካ አሸናፊ የሚሆንበትን ጨዋታ ያጫውታቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ፤ ፋጡማ ከሴቶች ተማሪዎች ባሻገር ወንዶችንም በመቅደም ታሸንፍ ነበር፡፡ ይህም በትምህርት ቤት ውድድሮች እንድትሳተፍ አስቻላት፡፡ ከትምህርት ቤት ወደ አውራጃ፣ ከዚያም ወደ ክፍለ ሀገር እያለች፣ አንድ ቀን ራሷን አዲስ አበባ፣ ጃንሜዳ አገኘችው፡፡ ከዚያም ወደፌደራል ማራሚያ ቤቶች ስፖርት ክለብ ገባች፡፡

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ከሀገር ውስጥ ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮችን ማድረግ የጀመረችው፡፡ ያም ሆኖ፤ ባደረገቻቸው የመጀመሪያዎቹ የማራቶን ውድድሮች ውጤታማ ለመሆን አልቻለችም ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የቤልጄሙ ውድድር በወቅቱ የነበራትን ተስፋ ያሟጠጠና ጽናቷን የፈተነ ነበር፡፡ ከውድድሩ በኋላ፤ “ሁለተኛ ማራቶን አልሮጥም” ብዬ ነበር የምትለው አትሌቷ፣ ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ አሰልጣኝ ወልደ መስቀል ኮስትሬ ሀሳቧን እንድትቀይር እንዳደረጓት ታስታውሳለች፡፡

ሀሳቧን መቀየር ብቻም አይደለም፤ ከ15 ቀናት ልምምድ በኋላ ለዓለም ዋንጫ ውድድር ወደ ኖርዌይ ተላከች፡፡ አሁንም ግን ማሸነፍ አልቻለችም፡፡ በሞሮኮ ማራካሽ በተካሔደው ውድድር ግን ድል ቀናት፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ በሮም ሌላ ድል የተቀዳጀችበትን ውጤት አስመዘገበች፡፡ ይህም ለአትላንታ ኦለምፒክ ሀገሯን ወክላ እንድትወዳደር አስቻላት፡፡ በዚያም ታላቁን ገድል ፈጽማ እነሆ ከኢትዮጵያ አልፋ የአፍሪካ ኩራት ለመሆን በቃች፡፡

ብርቱዋ አትሌት፤ የአትላንታውን ድል ስታስታውስ የማትረሳው አንድ ገጠመኝ አላት፡፡ ከውድድሩ ጅማሮ በፊት አሰልጣኞቿ ለጥቂት ጊዜ ረፍት ለማድረግ ጋደም ባሉበት እንቅልፍ ጣላቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም ፋጡማ ውድድሩ ወደሚካሔድበት ስታዲየም የሄደችው ዘግይታ ነበር፡፡ ስታዲየም ስትደርስ አትሌቶቹ አሟሙቀው ጨርሰው ውድድሩን ለመጀመር እየተዘጋጁ ነበር፡፡ በዚህ ጥሩ ያልሆነ አጋጣሚ ውስጥ አልፋ፣ በጥድፊያ ወደ ውድድሩ ብትገባም ድሉ ግን የእርሷ ነበር፡፡

ያ ባይሆን ኖሮ ምናልባትም ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ካገኘቻቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች አንድ ይቀነስ ነበር፡፡ እርሷም የአፍሪካ ኩራት መባሏ ብቻም ሳይሆን ለበርካታ የሀገራችን አትሌቶች አርዓያ መሆኗ ይቀር ነበር፡፡ ምናልባትም እኛ የዚያ ዘመን ሰዎች በወቅቱ ያጣጣምነውን ያን ደስታ እንነጠቅ፣ የአሁኑ ትውልድም ይህን በወርቅ ቀለም በደማቁ የተጻፈ ታሪክ አያውቅም ነበር፡፡ ምናልባትም ነብይ መኮንንም እነኚህን ስንኞች ባልጻፈ ነበር፡-
“አገሬን አየኋት በሰው ሀገር ሰማይ፣
በሰው ሀገር ፀሀይ፤
አገሬን አየሁዋት ሰማይ ወጥታ አትላንታ
አየሩን ለውጣው በኢትዮጵያዊ ሽታ
ሰማይ ጥግ አትላንታ
በማራቶን ዳገት ሩጫ ጎልጎታ፡፡”

“ካደረኳቸው ከሁሉም የማራቶን ውድድሮች፥ በኦሎምፒክ ያደረኩት ታላቅ ግምት የምሰጠው ነው” የምትለው አትሌት ፋጡማ፣ ቀጥሎ 3 ጊዜ (ከ1997 እስከ 1999) በተከታታይ ባለድል የሆነችበትን የቦስተን ማራቶን ትጠቅሳለች፡፡