“ትዕግስት ለሾፌሮች ትልቅ መሳሪያ ነው” ሾፌር ሞገስ ለገሠ
በጋዜጣው ሪፖርተር
በአሽከርካሪነት ሙያ ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ሙያ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሠሩ ሲሆን ጎን ለጎንም ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡
በ1977 ዓ.ም በነበረው ድርቅ በአሶሳ እና በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለተፈናቃዮች ትምህርት ይሰጡ ነበር፡፡ በሀዋሳ እርሻ ልማት፣ እንዲሁም ሠራተኛና ማህበራዊ ላይ አመራር ሆነው ያገለገሉ ሲሆኑ የቀበሌ ፀሐፊም ሆነው አገልግለዋል፡፡
በሙያቸው ወደ 54 ዓመት እንዳገለገሉና በአገልግሎታቸው ምንም አይነት የትራፊክ አደጋ እንዳላደረሱ የሚናገሩት ባለታሪካችን ያላቸው ልምድ ብዙ ትምህርት ሰጪ ገጽታ ስላለው ልናጋራችሁ ወደድን፡፡
አቶ ሞገስ ለገሠ ይባላሉ:: ተወልደው ያደጉት በሀረር ከተማ አማሬሳ በሚባል ሰፈር ሲሆን ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደ ደረሰ ሀረር ጀማሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 3ኛ ክፍል ተከታትለዋል።
ከዚያም በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ትምህርት ቤት እስከ 6ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ ወላጅ አባታቸው በሥራ ምክንያት ወደ ድሬዳዋ ሲቀየሩ እሳቸውም ድሬዳዋ በመሄድ ልዑል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል፡፡
ወደ ሹፍርናው ዓለም እንዴት እንደገቡ ሲገልፁም፡- አባታቸው ከጥቁር አሜሪካዊ ዶክተር ጋር በህክምና ሙያ ይሠሩ እንደነበር ጠቅሰው ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ድሬዳዋ ሲመጡም ለዶክተሩ አርባ ምንጭ ላይ መሬት ሰጥተዋቸው ኑሯቸውን አርባ ምንጭ ከተማ አደረጉ፡፡
“አባቴ ሊሄድ ሲል እኔም ተከትዬ የመሔድ ጉጉት አደረብኝ፡፡ ዶክተሩም እኔን በጥቅማ ጥቅም ይደልለኝ ነበር፡፡ በልጅነቴ ገንዘብ አስለምዶኝ ስለነበር ለትምህርቴ ትኩረት አልሰጥም ነበር፡፡ አባቴ አርፈህ ትምህርትህን ተማር ቢለኝም እምቢ አሻፈረኝ አልኩት፡፡ ሰፈራችን ለሀረማያ ቅርብ ስለነበር ሀይቅ ገብቼ እሞታለሁ ብዬ አስፈራራሁት፡፡
“አቋሜን የተመለከተው ዶክተሩ እኔን የበለጠ ያጓጓኝ ነበር፡፡ ትምህርትህን ትማራለህ ወይስ ሾፌር ትሆናለህ አለኝ፡፡ በዚያን ጊዜ መኪና ብርቅ ስለነበር ደስ ብሎኝ መኪና እማራለሁ አልኩት፡፡
“ትምህርቴን ከ8ኛ ክፍል አቋርጬ ከዶክተሩ ጋር ወደ አርባ ምንጭ አቀናን። ከዚያም ፈረንጆች ስለነበሩ የሹፍርና እውቀት ከእነሱ ቀሰምኩኝ፡፡ በድሮ ጊዜ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አልነበረም፡፡ በልምድ ነበር ሙያው የሚገኘው::” ሲሉም ወደ ሙያው እንዴት እንደ ገቡ ገልፀውልናል፡፡
ሥራ የጀመሩት በኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በአርባ ምንጭ ዋጅፎ እርሻ ልማት በትራክተር ነጂነት ነበር፡፡ በዚህ ሥራ ለ2 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የሰርቪስ መኪና ተሰጥቷቸው ይሠሩ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ደቡብ እርሻ ልማት ኮርፖሬሽን ተዛወሩ፡፡ እዚያ የተወሰነ ጊዜ ካገለገሉ በኋላ ሀዋሳ እርሻ ልማት ገቡ፡፡
በሀዋሳ እርሻ ልማት ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል፡፡ ጡረታ የወጡት በ2001 ዓ.ም በ60 ዓመታቸው ነው፡፡ ጡረታ ከወጡ በኋላ 15 ቀን ብቻ ነበር ያረፉት። ጡረታ ወጣሁ ብለው ቁጭ አላሉም። ከጡረታ በኋላ በተለያዩ የግልም ሆነ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከቀላል እስከ ከባድ መኪና አሽከርክረዋል፡፡ ሲኖትራክ ገና ወደ ሀዋሳ ሲገባ ከአዲስ አበባ ሥልጠና አግኝተው ሠርተዋል፡፡ ከዚያ የሀዋሳ ከተማ አውቶብስ ሲገባም የጀመሩት አቶ ሞገስ ናቸው፡፡
አሁን ላይ በኢታብ ሳሙና ፋብሪካ እየሰሩ ሲሆን በዚያም ለ10 ዓመታት አገልግለዋል። አቶ ሞገስ ሥራ ወዳድና ኃላፊነት የሚሰማቸው ሠራተኛ ናቸው፡፡ ለረጅም ዓመታት በአሽከርካሪነት ሲቆዩ ምንም አደጋ አላደረሱም፡፡
ሥራና ሰዓት አክባሪ፣ እንዲሁም የተሰጣቸውን የድርጅቱን መመሪያዎችን በሙሉ በጥንቃቄ የሚተገብሩ ናቸው፡፡ በእርሻ ልማት እየሠሩ በጥንካሬያቸው ብዙ የምሥጋና ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ለአደጋ ያልተጋለጡበትን ምክንያት እንዳነሱት ከሆነም፡-
“ድሮ መኪና አይበዛም ነበር፡፡ መንገዱም ምቹ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ አርባ ምንጭ ለመድረስ 5 ቀን የሚፈጅ በጣም አስቸጋሪ መንገድ ነበር፡፡ ጭቃ ሲይዘን ጫካ ውስጥ እናድር ነበር፡፡ ሙሉ እቃ ጭነን፤ ማብሰያ ምግብ ይዘን ነበር የምንሄደው። አሁን ላይ መንገዱም ምቹ ነው፡፡ የመኪና ብዛቱም ሥፍር ቁጥር የለውም፡፡ አደጋውም እንደዛው ይበዛል፡፡
“አንዳንድ አሽከርካሪዎች ብዙ ጊዜ ጥንቃቄ አያደርጉም፡፡ ጥንቃቄ ከተደረገና ህግ ከተከበረ አደጋዎች ሊደርሱ አይችሉም። ድሮ በልምድ ነበር መኪና የምንነዳው። አሁን ላይ ማሰልጠኛዎች ተበራክተዋል። ግን ትምህርቱን/ስልጠናውን በተገቢው መንገድ የሚማረው ጥቂት ነው፡፡ መንገድ ትራንስፖርት የሚሰጠውን ትምህርት በተገቢው ተምሮ ካለፈ በኋላ ሲነዳ ልክ እንደ ትምህርቱ መንዳት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
“መንጃ ፈቃድ አገኘሁ ተብሎ እንደ ልብ የሚወጣ ከሆነ፣ መጠጥ ጠጥቶ የሚነዳ ከሆነ፣ ጫት በመቃም እንዲሁም በግዴለሽነት ካሽከረከሩ አደጋ መድረሱ አይቀርም፡፡” ሲሉ አቶ ሞገስ ይናገራሉ፡፡
“እኔ ሁልጊዜ ጥንቃቄ አደርግ ነበር። በተጨማሪም ትዕግስት ለሾፌር ከፍተኛ መሳሪያው ነው፡፡ እኔ ተጠንቅቄ ስነዳ ሌላው ደግሞ ዘው ብሎ ሊገባ ይችላል፡፡ ያንንም በትዕግስት ነው የማሳልፈው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን አደጋ እንዳይደርስ የረዳኝ ትዕግስትና ጥንቃቄ ማድረጌ ነው፡፡” ሲሉ ተሞክሯቸውን አጋርተውናል፡፡
እንደው ሙያውን ይወዱታል ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፡-
“ሙያውን እወደዋለሁ ግን አንዳንዴ ለምን ትምህርቴን አቋረጥኩ ብዬ እፀፀታለሁ። በተለይ ቤተሰብ ጥየቃ ወደ ሀረር ስሄድ። ሞገስ መጣ ሲባሉ በጣም የምግባባቸው ጓደኞቼ ሊጠይቁኝ የሚመጡ አሉ የተባሉ ዘመናዊ መኪና ይዘው ሳይ እቆጫለሁ፡፡ ከኔ ጋር የተማሩ ምክትል ሚኒስትር የሆኑ አሉ፡፡
“ከረጅም ቆይታ በኋላ ትምህርቴን ለመማር ወስኜ ነበር፡፡ ነገር ግን ካርድ ስላልነበረኝ ድጋሚ ከ8ኛ ክፍል በሀዋሳ ታቦር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር ጀመርኩኝ፡፡ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል በታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማርኩኝ። ከዚያ ከሥራው ጋር ስላልተመቸኝ ድጋሚ ለማቋረጥ ተገደድኩኝ፡፡” ሲሉ ለመማር ያደረጉትን ጥረት ይናገራሉ፡፡
“ትምህርቴን በአግባቡ ተምሬ ባለማጠናቀቄ ብቆጭም በሕይወቴ ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ በአሽከርካሪነት ሙያዬም እንዲሁ ደስተኛ ነኝ፡፡” ሲሉም ይናገራሉ፡፡
ለትራፊክ አደጋ መበራከት መንስኤዎቹ ምን ይሆኑ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፦
“አሁን ላይ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ድሮ ለምሳሌ ከ1 እስከ 3ኛ ደረጃ ነበር መንጃ ፈቃድ የሚሰጠው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ እስከ 5ኛ ድረስ ነው፡፡ አንድ ሰው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ አጠናቆ ሳያወጣ 5ኛ መንጃ ፈቃድ ያወጣል፡፡
“አንድም አደጋ የሚበዛው በዚህ ነው። የትንሽ መኪና አዟዟር ይለያል፡፡ ከትንሽ መኪና ተነስቶ ከፍ እያለ ቢሄድ እውቀት ይኖረዋል፤ አደጋውም ይቀንሳል፡፡ መንጃ ፈቃድ ድሮ እንደዚህ አይሰጥም ነበር፡፡
“ፈታኙ ራሱ ነው መንጃ ፈቃድ የሚሠጠው፡፡ ስራ አስኪያጁ ይፈርማል፤ ፈታኙ ይሰጣል፡፡ ሲሰጥ ቃል አስገብቶ ነው፡፡ ‘ስማ ተፈትኛለሁ ብለህ የጥንቃቄ ጉድለት ብታደርስ በህይወት ላይ፣ በንብረት ላይ ብዙ አደጋ ታደርሳለህ፡፡
“ስለዚህ ፈተና ለመፈተን ጥንቃቄ እንደምታደርገው ሁሉ ሥራ ላይ ስትሆንም ጥንቃቄ ማጉደል የለብህም፡፡ ከተዘናጋህ ህይወትህ ይቀጠፋል’ ይለዋል፡፡ ይህን ሁሉ ምክር ሰጥቶ፣ ከወንበሩ ተነስቶ መልካም ምኞቱን ገልጾ ነው መንጃ ፈቃዱን የሚሰጠው፡፡ ዛሬ እንዲህ አይነት ምክር የለም፡፡
“ድሮ መኪና ብዙ ባይኖርም ጥንቃቄ ይበዛል፡፡ ለምሳሌ እኛ መሥሪያ ቤት በሦሥት ፈረቃ ነው የምንሠራው፡፡ ማታም ጭምር እንሠራለን፡፡ ማታ ማታ መንገዱ ባዶ ነው። አንዳንዴ በባዶ ሜዳ አደጋ ይደርሳል። ምክንያቱ ደግሞ ጠጥተው ስለሚያሽከረክሩ ነው፡፡ የተቀመጠ የመንገድ ስነ-ስርዓት አለ። አንድ ሾፌር የተማረውን የመንገድ ስነ- ስርዓት ማክበር አለበት፡፡
“ሌላው የእግረኛ ማቋረጫ (ዜብራ) ማክበር ነው፡፡ ይህ የመንገደኞች መተላለፊያ ነው፡፡ ችግሩ ሾፌሮች ላይ ብቻ አይደለም። እግረኞችም ህግን ይጥሳሉ፡፡ ዜብራ ላይ ቆመው ስልክ ያወራሉ፡፡ ይህ ድርጊት ሾፌሮችን ያናድዳል፡፡ ሲናገሯቸው የሚሠጡት መልስ አጉል ነው፡፡ እና ፍሬቻ ወደ ቀኝ አሳይቶ ወደ ግራ የሚያዞር አለ፡፡ ያም የከፋ አደጋ ነው። ሾፌሩ ሺህ ጊዜ ጥንቃቄ ቢያደርግ አደጋ መድረሱ አይቀርም፡፡ እግረኛውም ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡
“ጎማ በረረ ሲባል ብዙ ጊዜ እንሰማለን። ይህ ታድያ የሚከሰተው ቀድሞ ሾፌሩ መኪናውን ባለመፈተሹ ምክንያት ነው፡፡ መኪናውን ከማስነሳቱ በፊት የመኪና ዘይት ማየት፣ የራዲያተር ውሃ መፈተሽ፣ ጎማዎቹ ዝቅ ማለታቸውን አለማለታቸውን፣ የጎማ ብሎኖቹን ማየት አለበት፤ ድንገት ሊላላ ይችላል፣ የዝናብ መጥረጊያውንና ስፖኪዮም ማየት አለበት፡፡
“እና ቅድመ እይታ ያለማድረግ ብዙ ጊዜ ለአደጋዎች ያጋልጣል፡፡ አጠቃላይ የመኪና ክፍሎቹን ትክክል ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ፍጥነት መቀነስ ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ የትራፊክ አደጋ መንስኤዎችን ካላቸው ልምድ በመነሳት ከምክረ ሃሳብ ጋር አካፍለውናል፡፡
አቶ ሞገስ በሥራ ባልደረቦቻቸው ዘንድ ልዩ ባህሪ አላቸው፡፡ ሰው አክባሪ እና ትዕግስተኛ ሾፌር ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ያዩትን መጥፎ ነገር ማሳለፍ አይችሉም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ግን ተወያይተው የመፍታት ልምድ አላቸው፡፡
ሀዋሳ ላይ ፌርማታዎች አልነበሩም። አቶ ሞገስ የሀዋሳ ከተማ አውቶብስ በሚያሽከረክሩበት ወቅት ብዙ ጭቅጭቆች ይገጥማቸው እንደ ነበር አጫውተውናል። ያንን በትዕግስት ነበር የሚያሳልፉት። ህብረተሰቡ ስለ ፌርማታ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲደርሱባቸው÷ ፌርማታ ያስፈልጋል ብለው የሀዋሳን ፌርማታ ያስተከሉትም እሳቸው ናቸው፡፡
“በተለይ የህዝብ ማመላለሻ መኪና ላይ የተለያዩ ችግሮች ይገጥማሉ፡፡ ግን ስሜቴን እቆጣጠራለሁ፡፡ በሰላማዊ መንገድ እነጋገራለሁ፡፡ የለቀኩት መሥሪያ ቤት ሁሉ ‘ለምን ትለቃለህ? ካንተ ብዙ ትምህርት ተምረናል’ ይሉኛል፡፡ በተጨማሪም ቢሮ ላይ የሚሠሩ ብልሹ አሰራሮችን እጋፈጥ ነበር፡፡ በስብሰባዎች ላይ ሀሳቤን በነፃነት እገልጽም ነበር” ሲሉ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር የነበራቸውን መልካም ግንኙነት ገልፀውልናል።
አቶ ሞገስ በ1970 ዓ.ም ወደ ትዳር ዓለም የገቡ ሲሆን 2 ሴት እና 2 ወንድ ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ልጆቻቸውን በቻሉት አቅም አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡
ከልጆችዎ መካከል የእርሶን ሙያ የተከተለ አለ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡-
“የመጀመሪያ ልጄ ግርማ ሞገስ ይባላል። እኔ ፈቃደኛ ባልሆንም በራሱ ፈቃድ የኔን ፈለግ ተከትሎ በሹፍርና ሥራ ተሰማርቷል፡፡ ብዙ ጊዜ ሹፍርና አስተምረኝ ብሎ ያስቸግረኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ፈቃደኛ አልነበርኩም፡፡
“በአንድ ወቅት የግል ድርጅት ውስጥ ይሰራ ነበር፡፡ ግን ቢሮ ላይ ቁጭ ብሎ መሥራት አልፈለገም፡፡ እኔ ሳላውቅ መንጃ ፈቃድ አውጥቶ ነበር፡፡ ሾፌር ከሆነ በኋላ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፤ ጠንካራ ሾፌር እንዲሆን ግን በየጊዜው አስታውሰዋለሁ፡፡” ይላሉ፡፡
ልጃቸውም በሥራው ውጤታማና በሥነ-ምግባሩ የተመሰከረለት እንደሆነ የሥራ ባልደረቦቹ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ የተቀሩት ልጆቻቸውም የጥሩ ሥነ- ምግባር ባለቤት ሆነዋል፡፡
የመልካም ተምሳሌት ሾፌሮችን ያብዛልን እያልን፤ ለሾፌር ሞገስ ዕድሜና ጤና ተመኘን።
More Stories
የዕልፍ ውበት መገኛ ሥፍራ
“እየሠራን እዚያው መኖር ከባድ ነው” – ወ/ሮ ዘነበች ደምሴ
“ምንም ቢገጥመኝ ከፈተና እማራለሁ” – ወጣት አሸናፊ ሙሴ