ሽምግልና እና ሰርግ ሲምታታ

ሽምግልና እና ሰርግ ሲምታታ

በኢያሱ ታዴዎስ

በሀገራችን ሚያዚያ ከጥር በመቀጠል የሰርግ ወር ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ ጊዜ ታዲያ የሰርጉ ድምቀትና ግለት አይጣል ነው። ያላገቡ እንዲያገቡ፣ ያገቡ ደግሞ ጋብቻቸውን እያስታወሱ ሐሴት እንዲያደርጉም የሚጋብዝ ነው። ቅዳሜና እሁዶች በየመንደሩ በሚደኮኑ ድንኳኖች፣ መንገዶችም በሰርግ መኪኖች ይሞላሉ። በአጠቃላይ የሰርግ አጀብ የበዛበት ወር ነው፡፡

እኔም ወሩን መነሻ አድርጌ ወቅቱ የሰርግ እንደመሆኑ በግሌ የታዘብኳቸውን ትዝብቶች በጥቂቱ በዚህ እትም ላስቃኛችሁ ወደድኩ፡፡

አሁን አሁን በጋብቻ ጥምረት ውስጥ ሰርግ ሶስተኛ አማራጭ እየሆነ መጥቷል፤ ማለቴ ከመተጫጨት ስርዓት (የታገቢኛለሽ ጥያቄ) እና ከሽምግልና በኋላ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማህበረሰባችንም ሁለት ዓይነት መልክ የተላበሰ ነው የሚመስለው፡፡

በአንድ ጎኑ የኑሮ ውድነቱ አቅሙን ከሚገባው በላይ እየተፈታተነው እንደሆነ ሲያማርር ይሰማል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ እንደ ሰርግ ያሉ ስርዓቶችን ትዝብት ውስጥ እስከሚገባ ድረስ ድል አድርጎ በመደገስ ሲፈጽም ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ነባራዊ የሀገሪቱ ሁናቴን ያገናዘበ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡

ለማንኛውም ወደ ነጥቤ ስመለስ ከሰርግ ይልቅ ወደ ሰርጉ የሚያንደረድሩ ዝግጅቶች ድምቀታቸው እየበዛ መጥቷል፡፡ በዘመኑ ቋንቋ “ፕሮፖዛል” የተሰኘው የመተጫጨት ስርዓት ወጪው ከሰርግ የማይተናነስ ሆኗል፡፡

በአንድ ታዋቂ ዘመናዊ ሆቴል ሰርፕራይዝ አድራጊው ሰው (የታገቢኛለሽ ጥያቄ ፍቅረኛውን የሚጠይቀው) የእሱንና የፍቅረኛውን ወዳጆች አሰባስቦ እሷ በማትጠራጠርበት መልኩ ሁሉን አሰናድቶ ይጠብቃታል፡፡

ለዚሁ ዝግጅት ደግሞ ከሆቴል አዳራሽ ኪራይ ጀምሮ ለምግብ፣ ለመጠጥ፣ ለኬክ፣ መድረክ ለማስዋብ፣ ለፎቶግራፍ እና ቪዲዮ፣ እንዲሁም ለሌሎች ተያያዥ ነገሮች የሚወጣው ወጪ ቀላል አይደለም፡፡

በዚያ ላይ የታዳሚዎች ቁጥር በራሱ በርከት ያለ መሆኑ አይቀርም፡፡ ቀላል ነው የተባለው ይሄ ዝግጅት ታዲያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ ይደረግበታል፡፡ አቅም አለው የተባለው አስከ ግማሽ እና ለአንድ ሚሊየን የተጠጋ ብር ወጪ ማድረጉ አይቀርም፡፡

አስቡት እንግዲህ ይህ ሁሉ ሽርጉድ ገና ከሽምግልና አስቀድሞ ላለ የመተጫጨት ስርዓት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ ሰፋ ብሎ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጣይ የሚሆነው የሽምግልና ስርዓት ነው፡፡

የሽምግልናው ደግሞ ይብሳል፡፡ “ሰርግ ነው ወይስ ሽምግልና!” ያስብላል፡፡ አሁን አሁንማ ፋሽን እየሆነ መጥቷል፡፡ ለጋብቻ የታጨው ወንድ በዛ ያሉ ሽማግሌዎችን በመምረጥ ወዳጆቹን አክሎ ዳጎስ ያለ ጥሎሽ አሸክፎ ወደ ስፍራው ይሰድዳል፡፡

በሽምግልናው በጥሎሽነት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች አብረው ይላካሉ፡፡ ይህ ግዴታ ደግሞ የሚጠበቀው ከወንዱና ከቤተሰቦቹ ነው። የሴቷ ቤተሰቦች በበኩላቸው የሰርጉ ዕለት በሚቆረጥበት የመጨረሻው ሽምግልና ወቅት፣ ሽማግሌዎችንና ሌሎች ወንዱን ወክለው የሚታደሙትን፣ እንዲሁም በሴቷ ወገን የሚገኙ ቤተሰብና ወዳጆችን ሁሉ ሰፋ ባለ ዝግጅት ያስተናግዷቸዋል፡፡

በዚህ ወቅት የሴቷ ወዳጆች እና ሰፈርተኞች ሁሉ ሳይቀር በዝግጅቱ ስለሚጠሩ በሰርግ ጊዜ ከሚሰናዳው ባልተናነሰ ሰፋ ያለ ድግስ ይሰናዳል፡፡ ድንኳን ባይደኮንም ቤት እንደምንም ተሰማምሮ እድምተኞችን እንዲያስተናድግ ይደረጋል፡፡

በትንሹ አንድ የሰባ በሬ ተገዝቶ ለጥሬ በላተኛ፣ እንዲሁም ለተለያዩ ዓይነት ምግቦች እንዲዘጋጅ ይደረጋል፡፡ መጠጡም በተመሳሳይ በዓይነት ዓይነቱ ይዘጋጃል፡፡ አቅም አለው ተብሎ የሚታሰብ ቤተሰብ ደግሞ ሁለትና ከዚያ በላይ የሰቡ በሬዎችን ለዝግጅቱ ሊያቀርብ ይችላል፡፡

በዚህ መልኩ የሚስተናገደው የሽምግልና ስርዓት ዝግጅቱ በምግብና በመጠጥ ይድመቅ እንጂ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ መልክ አይኖረውም፡፡

በእርግጥ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከመልካም እሴቶቻችን መካከል ለሽምግልና ስርዓት የምንሰጠው ስፍራ በበጎነቱ የሚጠቀስ ነው። አንዲት ለአቅመ ሔዋን የደረሰችን ሴት በአግባቡ ወጉን በጠበቀ መልኩ ልጃችሁን ስጡን በማለት በክብር ለጋብቻ መጠየቅ ጥንትም የነበረ ጠንካራ እሴት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ በበዛባት በሀገራችን፣ ሽምግልና ላይ የሚወጣው የጥሎሽ እና የድግስ ወጪ መጋነኑ አጉል መንጠራራት እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ እየተለመደ ከመጣ ደግሞ ጥንዶች ደፍረው ወደ ትዳር እንዳይገቡ ጋሬጣ መሆኑ አይቀርም፡፡

ግን ደግሞ ለሽምግልና የሚሰጠው ክብደት ከመጠን እያለፈ መምጣቱ ስጋቱን አያስቀረውም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ከማን አንሼ የሚለውን አስተሳሰብ ማንጸባረቂያ ያደረገም ይመስላል፡፡

ታዲያ ይህን ሁሉ ሂደት አልፎ ደግሞ አይቀሬው ሰርግ ከተፍ ይላል፡፡ ሰርግ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚመጣ ዕድል በመሆኑ ብዙ ጊዜ ሰርገኛውም ሆነ ቤተሰብ አቅምን ሳያገናዝብ በስሜታዊነት የሚከውነው ዝግጅት መሆኑ እሙን ነው፡፡

በተለይም ሙሽራውም ሆነ ቤተሰቡ ተበድሮ መደገሱ አዲስ አይደለም፡፡ ኑሮ ተወደደ በሚባልበት በዚህ ጊዜ እንኳን በየሰፈሩ ድንኳን ተጥሎ፣ አሊያም በየሆቴሉ ድል ያለ ድግስ ሲደገስ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡

ይህ ሲታይ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ሕብረተሰቡ ኑሮ ተወደደ ብሎ ብሶቱን አደባባይ ሳይቀር ማሰማቱ ለይምሰል ነው እንዴ የሚል ሃሳብ በአዕምሮ መጫሩ አይቀርም፡፡ በእርግጥም ያስብላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰርግ የሚደግሱ ሰዎችን ጠጋ ብላችሁ ብትጠይቋቸው ተበድረው እንደ ደገሱና ዕዳ ውስጥ እንደ ዘፈቃቸው ይነግሩዋችኋል፡፡

ሰርገኛውም ቢሆን “መጥኔ ለሰርግ” የሚለው ድግሱን አጠናቅቆ የዕዳ ገፈቱን ከቀመሰ ወዲህ ነው፡፡ ይህ አካሄድ እየከፋ መጥቶ ቤተሰብን ለጭንቀት፣ ባለትዳሮችን ደግሞ ለጭቅጭቅ ሲዳርግ እንመለከታለን፡፡ ባስ ካለ ወደ ፍቺም ሊያመራ ይችላል፡፡

ይህ ሁሉ ስጋት ባለበት ሂደት ውስጥ ነው እንግዲህ የእጮኝነት፣ የሽምግልና እና የሰርግ ድግሶች ሰፋ ባለ መልኩ የሚከወኑት፡፡ ለምን ይህ ሆነ ተብሎ ሲጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ “ስላለው ነው” የሚል ነው፡፡

እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ ገንዘብ ስላለው ብቻ በሰበብ አስባቡ ለድግስ መርጨቱ ማህበረሰባችንን የሚመጥን አይደለም፡፡ ማህበረሰባችን ያለበት የኑሮ ሁኔታ ይታወቃልና፡፡ በዚያ ላይ ድግስ የሚደግሱ ሰዎች ከወጪው የተነሳ ሲያማርሩ እንጂ ሲያመሰግኑ አይታይም።

ይህ ደግሞ እንደ ማህበረሰብ ቆም ብለን መመልከት እንዳለብን የሚያስገነዝበን ነው፡፡ አንድም ጋብቻ አዲስ ቤተሰብ መመስረቻ ተቋም እንደመሆኑ መጠን አዲሱን ቤተሰብ በጤናማ የገንዘብ አያያዝና በፍቅር ልንገነባው ይገባል፡፡

እንደ ማህበረሰብም ትልቁን ተቋም (ጋብቻ) ወጪን ከመሳሰሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ከሚያስገቡ ድግሶች በማዳን መንከባከቡ ሌላው ግድ የሚል አማራጭ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ከሰርግ እኩል ካልሆነ በሚል እሳቤ የሚጋነኑ የእጮኝነት (ፕሮፖዛል) እና የሽምግልና ድግሶች መልካሙን ኢትዮጵያዊ እሴት እንዳይሸረሽሩ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡