“በእኔ እንዲኮሩ እፈልግ ነበር፤ ተሳክቶልኛል” – መምህርት ትህትና ተረፈ

በአለምሸት ግርማ

ንቁ ማህበረሰብን በማፍራት ሂደት ውስጥ የወላጆች ሚና ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ልጆች በልጅነታቸው ከቤተሰባቸው የሚወርሱት መሰረት ሲያድጉ ቅን አሳቢ፣ ታማኝ፣ ስራ ወዳድ፣ ለሀገር የሚጠቅሙና ለሌሎች ምሳሌ መሆን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። የዛሬዋ እቱ መለኛችንም ከቤተሰባቸው ያገኙት መልካምነትና የራሳቸው ጥንካሬ ተደምሮ ተምሳሌት መሆን ከቻሉ ሴቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። 

መምህርት ትህትና ተረፈ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት ሃዋሳ ከተማ ነው። ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ፤ አንድ ወንድምና አራት እህቶች አላቸው። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሃዋሳ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሃዋሳ ኮምቦኒ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በመቀጠልም ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማናጅመንት፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአካውንቲንግ ኤንድ ፋይናንስ አግኝተዋል። ሁለቱንም ሲጨርሱ በከፍተኛ ማዕረግ ነው የተመረቁት።

በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አጠናቀው በሙያቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀጥረው ማገልገል ጀመሩ። በዚያም ለአራት ዓመታት ያህል አገልግለዋል። በመቀጠልም ለትምህርት ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ፥ ስራቸውን በማቆም በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቀን መርሃ ግብር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መማር ቀጠሉ።

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የተለያዩ ኮሌጆች ላይ በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ከዚያም በተጨማሪ በኢንተርፕሩነርሺፕ ዘርፍ ላይ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ። በተለያዩ መድረኮችም ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ያካፍላሉ። በአንድ የጋርመንት ካምፓኒ ውስጥም ተቀጥረው ይሰራሉ። እንዲሁም “ሮሃ ቱር ኤንድ ኤቨንትስ” የተባለ ድርጅት ያላቸው ሲሆን፤ ከኮቪድ ጀምሮ መስራት የጀመሩ መሆኑንና በ2017 ዓ.ም ከሚሰሩት የጋርመንት ስራ ጋር ስለተጋጨባቸው ለጊዜው ስራውን ማቆማቸውን አጫውተውናል።

በልጅነታቸው ይህን መሆን እፈልጋለሁ ብለው ባይወጥኑም፥ በተሰማሩበት የስራ መስክ ግን ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አጥብቀው ይመኙ ነበር። ወላጅ አባታቸው የአካውንቲንግ ባለሙያ የነበሩ ሲሆን፤ እሳቸውም የአባታቸውን ሙያ ለመከተል የቻሉት በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። አባታቸው ሙያውን እንዲወዱት ከማድረጋቸውም በላይ በሚማሩበት ወቅት የእሳቸው እገዛ እንደነበርም አጋርተውናል።

ሴትነትና ዓላማን ማሳካትን እንዴት ይገልፁታል? የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው እንዲህ ሲሉ መልሰውልናል፦

“ሴቶች ከሴትነታቸው በፊት ሰው መሆናቸው ይቀድማል። ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው ያለሙትን ዓላማ ማሳካት ይችላሉ። እኔ በብዙ መድረክ ችዬ አሳይቻለሁ። እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ከወንዶች ጋር ተወዳድሬ ተሽዬ አሳይቻለሁ። ሴት መሆን በተለይ በዚህ ዘመን ብዙ ፈተናዎች አሉት። ነገር ግን አስቀድመን ማሳካት የምንፈልገውን ወይም መሆን የምንፈልገውን ማወቅ በጣም ይጠቅመናል። እኔ ለምሳሌ ጥሩ ተናጋሪ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። ስለዚህ ያንን በራሴ መሆን እችላለሁ ወይ? የሚለውን ነገር በደንብ አስብበት ነበር። ከዚያ ቤተሰቦቼን፣ የኃይማኖት ትምህርቶችን እሰማለሁ።

“ጥቅም አላገኝበትም ብዬ የማስበው ቦታ ላይ አልገኝም። ያም በብዙ መንገድ ጠብቆኛል የሚል እምነት አለኝ። ሃዋሳ ተወልጄ እንደማደጌ ብዙ ጓደኞች አሉኝ። ቢሆንም ለመዝናናት እንኳን ቢሆን የማይጎዳ ነው ወይ የሚለውን በደንብ አይ ነበር። ያም ለእኔ በጣም ጠቅሞኛል። በተለይ እንደሴት የሁሉም ፈተና ጠባሳ ወይም ጉዳቱ ሴቷ ላይ ነው የሚቀረው። ከፍቅረኛ መለያየትም ቢሆን፣ ልጅ ወልዶ መለያየትም ቢሆን በብዙ መንገድ ጫና የሚፈጥረው ሴቷ ላይ ነው። ሴቶች በተፈጥሮ ብዙ ጫና የሚሸከሙ እንደመሆናቸው መጠን ህይወታቸውን በጥንቃቄ ካልመሩት የሚደርሰው መከራ የከፋ ይሆናል።

“ማንበብ ስለምወድ። የተለያዩ መጽሐፍትን አነባለሁ። የማነበው ልብወለድ እንኳን ቢሆን እንደእውነተኛ ታሪክ አድርጌ ነው የምወስደው። ሴቶች ሲጎዱበትና ሲያለቅሱበት ያየሁትን ነገር እኔ ላይ እንዳይደርስ እጠነቀቃለሁ። ከብዙ ሰው እጠይቃለሁ፤ እማራለሁ። ያም ለህይወቴ ትልቅ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል።

“ቤተሰቦቼ እድለኞች ናቸው። ሁላችንም ጥሩ ደረጃ ደርሰናል። ሶስቱ እህቶቼ ትዳር የመሰረቱ ሲሆን፥ በሙያቸው አንዷ የባንክ ሰራተኛ ናት፤ አንዷ ደግሞ የግል ቢዝነስ አላት። ሌላኛዋ የጤና ባለሙያ ናት። የመጨረሻዋ እህቴ በኢንጂነሪንግ ዘንድሮ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመርቃለች። አንዱ ወንድሜ ደግሞ ኢንጂነር ነው፤  አዲስ አበባ ላይ የራሱ የኮንስትራክሽን ድርጅት ከፍቶ እየሰራ ይገኛል።

ልጆች ውጤታማ እንዲሆኑ ከወላጆች ምን ይጠበቃል? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፦

“ልጆች ውጤታማ እንዲሆኑ ከወላጆች የሚጠበቀው ቀዳሚው ነገር ልጆችን መከታተል፣ ማየትና ማዳመጥ ነው። የኔ ወላጆች በዚህ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። ልጆች ሆነን ያዳምጡን ነበር፤ ዕድል ይሰጡን ነበር። ትልቅ ቦታ እንድንደርስ ያበረታቱንና ግፊት ያደርጉብን ነበር። በሰዓቱ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ለልጆች ደስ ላያሰኙ ይችላሉ። ነገር ግን ያኔ ወላጆቼ እንደዛ ያደረጉት ነገር ዛሬ ለደረስንበት ነገር ዋናውንና ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ነው። አባቴ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ‘የኔ ልጅ የማይሆን ቦታ አትገኝም፤ ትልቅ ቦታ ነው የምትደርሰው’ እያለ በኩራት ሲናገር ኃላፊነትን እየሰጠኝ ነበር። ለእኔ ደግሞ ጠጋ ብሎ እንዳታሳፍሪኝ እሺ! ይለኝ ነበር። እኔም ሁል ጊዜ እንዳታሳፍሪኝ ያለኝን ነገር አስበው ነበር። እናቴም የኔ ልጆች ጎበዞች ናቸው ትል ነበር። ይህም እነሱ ያሉኝ ነገር ጋር ለመድረስ እንድጥር አድርጎኛል። የእነሱ አቋም ሁላችንም የተሻለ ቦታ እንድንደርስ ረድቶናል።

“በተጨማሪም የልጆችን ፍላጎት መጠበቅ ሌላኛው ነው። የእኔ ቤተሰቦች ሁለቱም የመንግስት ሰራተኞች ነበሩ። ነገር ግን በቻሉት መጠን ፍላጎታችንን ይጠብቁልን ነበር። ሁላችንም የተማርነው በግል ትምህርት ቤት ነው። መዝናናት ባለብን ሰዓት እየተዝናናን ነው ያደግነው። ለምሳሌ እኔ መዘነጥ እወዳለሁ። ስለዚህ የምፈልገውን እንዳደርግ ዕድሉ ይመቻችልኝ ነበር። ወላጆቻችን ያንን ሲያደርጉ ግን በጣም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። የእኛን ፍላጎት ሲያሟሉ የነበሩት የራሳቸውን ፍላጎት ትተውና ራሳቸውን በብዙ ጎድተው ነበር።

“እንድንበረታ ተመክረን፤ ስናጠፋ ተቀጥተን ነው ያደግነው። እኛን ሲያሳድጉ እነሱ ያጡትን ነገር ይነግሩን ነበር። ይሔ ሁሉ የተደረገለት ሰው ደግሞ የሚጠበቅበትን ውጤት የማስገኘት ግዴታ አለበት። እኛም ወላጆቻችን የሚጠብቁን ቦታ ላይ ተገኝተናል። ስለዚህ በእኔ ምክንያት ያጡትን ነገር መካስ የምችለው ጥሩ ቦታ በመድረስ በመሆኑ ደርሼ አስደስቻቸዋለሁ።

በእኔ እንዲኮሩ እፈልግ ነበር፤ ተሳክቶልኛል በማለት የወላጆቻቸውን መልካም ተፅዕኖ በደስታ ተሞልተው ነው የነገሩን። መምህርት ትህትና ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት ናቸው። በፋርማ ኮሌጅና በኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአካውንቲንግና ማናጅመንት መምህርነት በማገልገል ላይ ናቸው።

ቀጣይ እቅድዎት ምንድነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ እንዲህ ሲሉ መልሰውልናል፦

“እግዚአብሔር ቢፈቅድ በቀጣይ የራሴን ካምፓኒ ለመክፈት ተዘጋጅቻለሁ። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ። እነሱ ከእኔ የተሻሉ እና ተፅዕኖ የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ማድረግ እፈልጋለሁ። ለራሴም አሁን ካለሁበት የተሻለ ውጤታማ ለመሆን መስራት እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ቤተሰቦቼ ያላሳጡኝን ነገር በራሴ እንዳላጣው ሁልጊዜ ጥረት አደርጋለሁ።

“ሴቶች ራሳቸውን መውደድ አለባቸው። እኔ ራሴን በጣም ነው የምወደው። ይህንን ቤተሰቦቼም በቅርቤ ያሉ ሁሉም ያውቃሉ። ራስ ወዳድነትና ራስን መውደድ ይለያያል። ስለዚህ ራስን በመውደድ ውስጥ ራስን ማክበር አለ። ራሱን የማይወድ ሰው ለሌላው መትረፍ አይችልም። ራስን መውደድ ማለት ለራስ የተሻለ ቦታ መስጠት ነው። ራሳቸውን ለማሻሻል መማር ካለባቸው ትምህርት ይማሩ፤ መስራት ካለባቸው ይሰሩ ነገር ግን ራሳቸውን ይውደዱ። ራስን መውደድ ወይም መጠበቅ ሜካፕ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ውስጥን መገንባት ነው” ሲሉ ለሴቶች ምክራቸውን ለግሰዋል።