የአሥም በሽታ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ተገለፀ

የአሥም በሽታ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ተገለፀ

በቤተልሄም አበበ

ለአስም በሽታ ተጋላጭነት ያላቸውን ቀስቃሽ ነገሮችን በማስወገድ በሽታውን መከላከል እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያ አስታወቁ፡፡

በሀዋሳ ከተማ የሩሃማ መካከለኛ ክሊኒክ የህክምና ማዕከል ባለቤት እንዲሁም የህጻናት ስፔሻሊስት እና የልብ ህክምና ንዑስ ስፔሻሊስት ዶ/ር ንጉሴ ጫንያለው በተለይ ለንጋት ጋዜጣ እንደገለጹት፣ አስም የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን የአየር መተላለፊያ ቧንቧን በማጥበብ ለትንፋሽ ማጠር የሚያጋልጥ እና በዋናነትም የመቆጣት ምልክትን የሚያስከትል የመተንፈሻ ችግር ነው፡፡

ስፔሻሊስቱ የአስም አልያም የአየር መተላለፊያ ቧንቧ ችግር ከስድስት ዓመት ህጻናት አንስቶ እስከ ትልልቅ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ዜጎችን የሚያጠቃ መሆኑን አንስተው በተለይም ህጻናትን የሚያጠቃው በተፈጥሮ በዘር ሐረግ ግንድ እና ከባቢያዊ በሆነ በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

አክለውም አጣዳፊ እና የቆየ የተባሉ የአስም አይነቶች መኖራቸውን ጠቅሰው አጣዳፊው በህክምና መጥፋት የሚችል እንደሆነና ሌላኛው ደግሞ በህክምና ታግዞ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱ የቆዳ፣ የአፍንጫ፣ የአይን እና የምግብ አለርጂ በአስም በሽታ ለመያዝ አጋላጭ እና ምቹ ሁኔታዎች ስለመሆናቸውም ነው ዶ/ር ንጉሴ ያብራሩት፡፡

ዜጎች የመተንፈሻ አካላት የአየር ቧንቧ ችግር በራሳቸው ላይ መፈጠሩን ማረጋገጥ እንዲችሉ ደረቅ አልያም አክታ ያለው ሳል፣ የደረት መጨነቅ እና ህመም፣ የትንፋሽ ማጠር እና መፍጠን፣ የሰውነት መዛል እና ከፍተኛ ላብ ማላብ ምልክቶቹ መታየት ሲጀምሩ ወደ ህክምና ተቋማት በመጓዝ ጤናቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የአስም በሽታ ምርመራን አስመልክተው በሰጡት ገለጻ፣ የስድስት ዓመት ህጻናት በቂ ኦክሲጂን ወደ ውስጥ መሳብ ስለማይችሉ ለበሽታው መነሻ ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል በአለርጂ በተጠቁ ሰዓት የተለያዩ የቀለም ሽታዎች፣ የቤት ውስጥ እና የአበባ ብናኝ፣ ሽቶ እና ዶድራንት ቀስቃሽ ነገሮች መሆናቸውን በመገንዘብ የህክምና እርዳታ እንደሚሰጣቸው ጠቅሰዋል።

በተቃራኒው ደግሞ ትላልቆች ሳንባቸውን በማድመጥ፣ የደም ምርመራን በመፈጸም እና የአየር የመተንፈሻ ምርመራ በማካሄድ የጤና ችግሮቻቸውን እንዲያውቁ ይደረጋሉም ነው ያሉት ሰፔሻሊስቱ፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ እናቶች በእርግዝና ወቅት አደንዛዥ ዕጽ የሚጠቀሙ ከሆነ ከጽንሰታቸው ጀምሮ ያሉ ሁኔታዎች ህጻናቱን ለአስም በሽታ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸውም ገልጸዋል፡፡

የአስም በሽታ በዘር ሐረግ ከአባት ወደ ልጅ ሃያ አምስት በመቶ የመተላለፍ አቅም እንዳለው አንስተው፣ ነገር ግን ከአንዱ ወደ ሌላው በትንፋሽ አማካኝነት የሚተላለፍ እንዳልሆነም ዶ/ር ንጉሴ አስረድተዋል፡፡

የአየር ቧንቧን የሚከፍቱ፣ ብግነትን፣ አለርጂን የሚቀንሱ መድኃኒቶችን በመውሰድ እና የአስም በሽታ ቀስቃሾችን በማስወገድ ችግሩን ማከም እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

የአስም በሽታ ስርጭትን አስመልክቶ በዓለም ጤና ደርጅት ዘንድ እንደተተነበየው ከሆነ የከተሞች እና የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ የአስም ተጠቂዎች ቁጥር ተስፋፍቶ 450 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቂ ማድረጉ በመረጃው ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጆርናሎች የተጠኑ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ዘጠኝ በመቶ የሚደርሱ ህጻናት እና በተመሳሳይ ስምንት በመቶ የሚጠጉ አዋቂዎች በአስም በሽታ ተጠቂ እንደሆኑም መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡