አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የዓለም ኢኮኖሚ
በፈረኦን ደበበ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገራት ላይ ቀረጥ መጣላቸው ለአሜሪካ መልካም ዕድል የሚያመጣ መስሎ ነበር፡፡ ሀገራት ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ በመላክ የብዝበዛ ተግባር መፈጸማቸውን ገልጸው ይህ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
ሀሳባቸው ከምጣኔ ሀብት መነሻ አሳማኝና ለአሜሪካ ጠቃሚ ቢሆንም ፍላጎታቸውን ከማሟላት ረገድ ግን ክፍተት ፈጥሯል፡፡ ጥርጣሬን አስከትሏል፡፡ ወቀሳ እንጂ ሙገሳን ከልክሏል፡፡
ጊዜው አጭር ከመሆኑ አልያም ምክንያቱ ባልታወቀበት ሁኔታ ድባቡ ተቀይሯል፡፡ ቀረጡ የተጣለባቸው ሀገራት ብቻ ሳይሆን አሜሪካ እራሷንም ከኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ያለመታደጉ ብዙዎችን ተስፋ አስቆርጧል፡፡
ዋና የንግድ አጋሮቻቸው ሳይቀሩ በአንድ ጊዜ ማወጃቸው እንደሆነ ባልታወቀበት ምክንያት ፕሬዝዳንቱ የሀገራቸው ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ኃላፊን ከሥልጣን እንዲያባርሩ አነሳስቷል፡፡ ሰሞኑን በኒው ዮርክ ከተማ ዓመታዊ ጉባኤውን ያደረገው የዓለም ገንዘብ ተቋም ትዝብት መንስኤም ሆኗል፡፡
አዎን ተቋሙ በግልጽ እንዳስቀመጠው ከሆነ የታወጀው የቀረጥ ውሳኔ መደበኛ የንግድ ሥርዓቱን አዛብቷል፡፡ ሀገራት አንዱ በሌላኛው ላይ እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግ የንግድ ፍሰቱን አስተጓጉሏል፡፡
የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መንስኤ በመሆን ከ12 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ሥራ እንዲያጡ ካደረገው “ታላቁ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ” በላይ የቀረጥ መጠን ማለፉ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ነው የተገለጸው፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው የገንዘብ ገበያው መረጋጋት እንዳልቻለና ቀደም ብሎ ከተወጣጠረው ገጽታ ወደ ባሰ አዘቅጥ ውስጥ ገብቷል በማለትም ነው ተቋሙ ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት የሚገልጸው፡፡
እንዲህ ዓለምን ከሚያሰጋው የኢኮኖሚ ድቀት በተለየ ሀገራችን እያካሄደች ላለችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አድናቆቱን የለገሰው የዓለም ገንዘብ ተቋም፤ ይህንን እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል ጠቃሚ ምክረ-ሀሳቦችንም ሰጥቷል፡፡ ለሀገራችን ይህ መልካም ዜና ነው፡፡
ሀገራት ዘንድሮና ቀጣይ ስለሚኖራቸው የዕድገት ተስፋ ድርጅቱ ሥጋቱን ሲያስቀምጥ ችግሩ በሀገረ-አሜሪካ ሊበዛ እንደሚችልም አሳስቧል። ባለፈው ዓመት ከነበረው 2 ነጥብ 7 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ የሀገሪቱ ዕድገት ወርዶ 1 ነጥብ 8 በመቶ እንደሚሆንና የንግድ ባላንጣ የሆነችው ቻይናም በተያዘው ዓመት 4 በመቶ በማስመዝገብ ከቀዳሚው ዓመት መቀነሷን አመላክቷል፡፡
ከአሜሪካና ቻይና ባለፈ በዩሮ ዞን ስላሉ 20 ሀገራትና ሌሎችም ያወሳው መረጃው በያዝነው ዓመት 0 ነጥብ 8 በመቶ ያድጋሉ ብሏል፤ ቀጣይ ዓመት ከዚህ በማሻሻል ዕድገታቸውን ወደ 1 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያደርሱ በማስታወቅ፡፡
ይህ ቀመር ቀደም ብሎ በዓመቱ መጀመሪያ ከተያዘው ትንበያ ዝቅ ማለቱን ያስታወቀው የዓለም ገንዘብ ተቋም ሌሎች እንደ ሜክስኮ ያሉ ሀገራትም ተመሳሳይ ቅናሽ በማስመዝገብ በተያዘው ዓመት 0 ነጥብ 3 በመቶ ታስመዘግባለች ብሏል፡፡
ላቲን አሜሪካና ካሪቢያንን በያዙ በ191 ሀገራትም ዕድገቱ በ1 ነጥብ 4 በመቶ ላይ እንደሚሆንና ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እንደሚቀንስ ጠቁሞ ከዚህ በተቃራኒ ለቀጣዩ ዓመት ግን የተሻለ ዕድል እንደሚኖራቸው አመልክቷል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን ነጥብ ባላነሱበት ሁኔታ በቅጽበት ስለተከሰተው ችግር ሲያወሱም ስቷርት ማክንቶሽ የተባሉ አንድ የዓለም ገንዘብ ተቋም ኃላፊ በአግራሞት ተናግረዋል፡፡
“አንድ ፕሬዝዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዴ ባስተላለፉት ውሳኔ እንዲህ ዓይነት ምስቅልቅል ሲወጣ በህይወቴ አይቼ አላውቅም”፡፡ ችግሩ በሳምንታት ጊዜ ብቻ እንዲህ ሆኗል በማለትም ነው ለአልጀዚራ የተናገሩት፡፡
ከሀገር ውስጥና ከዓለም እየደረሰባቸው ባለው ተቃውሞ የተደናገጡ የሚመስሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያወጡትን የቀረጥ ፖሊሲ ለማላላትና ቻይናን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ለመወያየት ማሰባቸው እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፤ የሀገሪቱ የቦንድ ገበያ ያሳየው መቀዛቀዝም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የወለድ ምጣኔ በማሳደግና ይህም ገንዘብ ለመበደር በሚፈልጉ ሀገራት ላይ ጫና ስለሚፈጥር፡፡
ችግሩ ታዳጊና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እስካሁን ያለባቸው የገንዘብ እጥረት እንደሚያባብስ ያመለከተው የገንዘብ ተቋሙ ብድራቸውን ለመክፈልና የልማት ወጪያቸውን በከፍተኛ ዋጋ እንዲጨምሩ ያስገድዳቸዋል ብሏል፡፡
የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይስማሙበታል በማለት አልጀዚራ በሠራው ዘገባ ላይም ሊደርስ የሚችለውን ሥጋት በድጋሚ አስፍሯል፡፡ ይህንን ጎልድማን ሳች የተባሉ ባለሙያ የደገፉት ሲሆን በተለይ በአሜሪካ ያለው የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ስለሚቀዘቅዝ ዕድገቷም በ0 ነጥብ 5 በመቶ ይወሰናል ብለዋል፡፡ ቀጣይ ዓመት የሚጠብቃት የኢኮኖሚ ድቀትም እስከ 45 በመቶ እንደሚደርስ በመጠቆም፡፡
በቢዝነስ ኢኮኖሚክስ ላይ ትኩረት የሚያደርገው ብሔራዊ ማህበር የተባለው ድርጅት ባስጠናው ጥናት መሠረትም ዘንድሮ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዙ ጨምሮ እስከ 49 በመቶ እንደሚደርስ ጠቁሞ ጀፕ ሞርጋን የተባለው ተቋም በበኩሉ 60 በመቶ መድረስ መቻሉን አመልክቷል፡፡
ብዙ ተቋማትና ባለሙያዎች ችግሩን ለመግታት ሥራ እንደሚያስፈልግ እየገለጹ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ የሀገሪቱ ማዕከላዊ ግምጃ ቤትም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ነው የደረሰው፤ የምጣኔ ሀብቱ 1 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ በዓመቱ እንደሚያስመዘግብ በማስታወቅ፡፡
ፕሬዝዳንቱ አሁን በጀመሩት መልክ ዕቅዳቸውን የሚያሻሽሉና የሚከልሱ ከሆነ ግን ሥጋቱን በመቀነስ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመፍጠር ይቻላል ተብሎ ይገመታል፡፡
More Stories
“በእኔ እንዲኮሩ እፈልግ ነበር፤ ተሳክቶልኛል” – መምህርት ትህትና ተረፈ
የአሥም በሽታ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ተገለፀ
“ቀምተናቸው የቆየነውን እኩልነት ነው የመለስንላቸው” – ክቡር ዶክተር ዙምራ ኑሩ