“ቀምተናቸው የቆየነውን እኩልነት ነው የመለስንላቸው”  – ክቡር ዶክተር ዙምራ ኑሩ

“ቀምተናቸው የቆየነውን እኩልነት ነው የመለስንላቸው”  – ክቡር ዶክተር ዙምራ ኑሩ

በገነት ደጉ

የዛሬው ንጋት እንግዳችን ክቡር ዶክተር ዙምራ ኑሩ ይባላሉ፡፡ የአውራምባ ማህበረሰብ መስራች ናቸው፡፡ የአውራምባ ማህበረሰብን በ1964 ዓ.ም ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ነው የመሰረቱት፡፡ በማህረሰቡ ዘንድ ባበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት እውቅና አግኝተዋል፡፡ ስለግል ሕይወታቸው፣ እንዲሁም የአውራምባ ማህበረሰብ መገለጫዎች ምንድናቸው? መቼ እና እንዴት ተቋቋመ? በሚሉ ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ!!

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍላችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- እኔም ለጋዜጣችሁ እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ትውልድና እድገትዎን ቢያስተዋውቁን?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- ክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደኩት ደቡብ ጎንደር  በገጠራማ መንደር ልዩ ስሙ “የሾ ሚካኤል” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱም የማስባቸው ነገሮች ከዕድሜዬ ጋር የማይመጥንና ለሰዎችም አስደንጋጭ በመሆናቸው ብዙ ችግርና መስዋትነትን ከፍያለሁ፡፡

ገና የአራት ዓመት ልጅ እያለሁ ሰዎች ከሚናገሩትና ከሚሰሩት መነሻ፣ ሰው በሰው ላይ ያልሆነ ነገር መስራትና ያልሆነ ነገር መናገር ለምን አስፈለገ እያልኩ ጥያቄ አነሳ ነበር፡፡ ከ4 እስከ 13 ዓመቴ ድረስ እንደ እብድ ነበር የምታየው። ሲነግሩህ አትሰማም እባልም ነበር፡፡ አብሮህ የተፈጠረ የአዕምሮ ችግር ነው እየተባልኩ ነበር ያደኩት፡፡

በ13 ዓመቴ ስደት ሄጃለሁ፡፡ ከጎጃም ወሎ፣ ከወሎ ደግሞ ጎንደር እያልኩ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ብዙ መከራ አይቻለሁ፡፡ በዚያን ወቅት ወደ መንደር ለመጠጋትም አስቸጋሪ ሆኖብኝ ለዓመታት ብዙውን ጊዜ ከዛፍ ስር አድር ነበር፡፡

ከመንደርም እልፍ ብዬ በጫካ ውስጥ ነበር ኑሮዬን ያደረኩት፡፡ ምግቤንም የዛፎችን ፍሬ ካገኘሁ እየለቃቀምኩ እበላ ነበር፡፡ በወቅቱም ሀይማኖት አባቶችንና ታዋቂ ግለሰቦችንም አሞኝ ከሆነ መድኃኒቴስ ምንድነው? በማለት አስጨንቃቸው ነበር፡፡ ምላሽ ፍለጋ፡፡

የሀይማኖት አባቶች እኛም መጽሐፍ ቅዱስ አንብበን ያልሰራነው ነው፡፡ እውነታው እውነታ ነው ግን አታልፈውም ይሉኝ ነበር፡፡

እውነትማ ከሆነ አንገቴ ቢቆረጥ ወደ ኋላ አልመለስም በማለት በራሴ ሀሳብ ነበር የተጓዝኩት። ሁሉም ሰው የሚናገረው እውነት ነው ይላሉ፤ ሀሳቤን ለመቀበል ግን ፈቃደኛ ሰው አልነበረም፡፡ በኋላም ወደ ቤተሰቦቼ ተመልሼ በድብቅ አቅመ ደካሞችን እየረዳሁ መኖር ጀመርኩ፡፡

ቤተሰቦቼንም ትዳር ፈልጉልኝ ስላቸው በሽታው ለቆት ነው ትዳር የጠየቀው አሉኝ፡፡ ወደ ትዳሩም ገብቼ እንደ ወላጆቼ እርሻ ጀመርኩና በዓመት አርሼ ያገኘሁትን ለአካባቢው አቅመ ደካሞች አከፋፍላለሁ፡፡ የእኔ ደስታ እርሱ ነበር፡፡

ይህን የበጎ ስራ ሳደርግ ደግሞ የሚድን በሽታ አይደለም የተያዘው ይሉኝ ነበር፡፡ እርሱ አይበላም፣ አይጠጣም፣ አይለብስም ማለት ጀመሩ፡፡ የእርሱን ገንዘብ ዘመድ አያገኝም ባዕድ ሰው ነው የሚበላው በማለት ይኮንኑኝም ነበር፡፡

በእኔ እይታ የሰው ልጆች የምትሉትና ባዕድ የምትሉት የትኛውን ነው በማለት እጠይቃቸው ነበር፡፡ ማንም ሰው ራሱን ጥቁርና ነጭ አድርጎ የፈጠረ የለም፡፡ አንድ ፈጣሪ ነው የፈጠረው፡፡ እኛም የአዳምና የሄዋን ልጆች ነን፡፡

በታሪክ ሌላ ዘር የለም፡፡ ከሌለ ባዕድነቱ ከየት መጣ? ለዘመድ አይሰጥም ባዕድ ነው የሚበላው የሚባለው ከየት መጣ? በዚህም ዙሪያ ነበር እደክም የነበረው፡፡

ንጋት፡- ለዚህ አስተሳሰብ በዋናነት ያነሳሳዎት ምንድነው?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- በዋናነት አራት ነገሮች ናቸው፡፡ የሴቶች እኩልነት፣ የህፃናት መብት አለመከበር፣ የወደቁ ሰዎች እንዲበሉና እንዲጠጡ፣ እንዲሁም እነሱን የሚያነሳቸው ማጣት፡፡ እነዚህ በሰዎች ላይ የሚሰሩት መጥፎ እና ግፍ ስራዎች ናቸው ወደዚህ ተግባር እንድገባ ያነሳሳኝ፡፡ ከዚያም በላይ ዱላው፣ መጥፎ ስድብና ግድያዎችም አሉ፡፡

በወቅቱም አንድ የሀይማኖት አባት እንዴት ሴቶች እኩል ናቸው ትላለህ በማለት ይቃወሙኝ ነበር፡፡ ሴት ከአዳም ግራ ጎን ላይ ተወስዳ እንዴትና ለምን እኩል ትሆናለች አሉኝ፡፡ እኔን ወደዚህ ምድር ያመጣችኝ እናቴ ናት፡፡ ወንዱንም እንደዚያው፡፡ ታዲያ ያየሁትን ላውራ ወይም የሰማሁትን ላውራ? ብዬ ጠየኳቸው፡፡

በኋላም ለጉብኝት የመጡትን ሀሳብ ተቀበሏቸው ብዬ ስለነበር ከጉብኝቱ በኋላ ያልገባኝን ነው የመለስኩት በማለት ይቅርታ ብላችሁ ንገሩልኝ ብለው ወጡ፡፡

ንጋት፡- ዘመናዊ ትምህርት ተምረው ይሆን?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- መች አግኝቼው። ከአራት ዓመት እድሜዬ ጀምሬ በዚህ በጎ አስተሳሰቤ ተቃውሞ ደርሶብኝ ከአካባቢዬ ወጣሁ። በኋላም ከብት ጥበቃ ገባሁ፡፡ በ13 ዓመቴም ዞሬ ዞሬ ተመለስኩ፡፡ ትምህርት እንዲያውም ስሙንም አላውቀውም፤ ዕድሉንም አላገኘሁም፡፡

ንጋት፡- የአውራምባ ማህበረሰብ እንዴትና መቼ ተመሰረተ?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- የአውራምባ ማህበረሰብ በለውጥ አራማጅነቱ እና ስራ ወዳድነቱ ይታወቃል። የአውራምባ ማህበረሰብ በአስተሳሰብ ልህቀት፣ በሰው ልጆች እኩልነትና ክቡርነት፣ አብሮ በመኖር እና መተጋገዝ ተምሳሌት መሆኑን ብዙዎች መስክረውለታል። የዘመናዊነት፣ የመልካምነት እና የብዙ ጥሩ ነገሮች መገለጫ መሆን ችሏል።

በደቡበ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ በወጅ አውራምባ ቀበሌ የሚገኘው የአውራምባ ማህበረሰብ ከክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር 74 ኪሎ ሜትር፣ ከወረታ ከተማ ደግሞ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ማህበረሰቡ የተመሰረተው በ1964 ዓ.ም ሲሆን ዘንድሮ 53ኛ ዓመቱ ነው፡፡ 

እስከ 50ኛ ዓመት ድረስ አክብረናል፡፡ አሁን ላይ በተለያዩ ሁኔታዎች ለሶስት ዓመታት አላከበርንም፡፡ ከዚያ በፊት ግን ባህርዳር፣ አውራምባ እና አዲስ አበባ ላይ በልዩ ሁኔታ አክብረናል፡፡

ለቀጣይ ዓመት በሰላምና በጤና ካደረሰን በደቡብ ምዕራብ ክልል ቦንጋ ከተማ ላይ ለማክበር አቅደናል፡፡ በኋላም ህብረተሰቡ የማህበረሰቡን እሴት እንዲለምደው እና እንዲያውቀው ብሎም እንዲለማመድ በሀገሪቱ ባሉት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለማክበር እቅድ ተይዟል፡፡

ንጋት፡- የአውራምባ ማህበረሰብ መስራችስ ማን ይሆን?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- የአውራምባ ማህበረሰብን የመሰረትኩት እኔ ነኝ፡፡ ከእኔ ጋር አባወራዎች በቁጥር 19 ያህል ነበሩ፡፡ እነዚህ 19 አባወራዎች ከእኔም ጋር ተከታይ ሆነው አብረውኝ ጀመሩ፡፡ በወቅቱ መንግስት እንዳይቃወመን ብለን ማህበር አቋቋምን፡፡ ማህበሩም አምራች ማህበር ነው፡፡

ንጋት፡- የአውራምባ ማህበረሰብ ዓላማውስ ምንድነው?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- የአውራምባ ማህበረሰብ የተነሳባቸውን መሰረታዊ ሀሳቦች ማለትም የሴቶችን እኩልነት አረጋግጦ፣ የህፃናትን መብት አስከብሮ፣ ለስራ ብቁ ያልሆኑ አቅመ ደካሞችን ተንከባክቦ፣ መጥፎ አነጋገርን እና አሰራርን አስወግዶ፣ በራስ ላይ እንዲሆኑ የሚፈለጉትን ነገሮች በሰዎች ላይ እንዲሆኑና በራስ ላይ እንዳይደርሱ የሚፈለጉ ነገሮችን በሰዎች ላይ እንዳይደርሱ አርቆ አስወግዶ፣ ነጭ ጥቁር ሳይባል ሁሉም የሰው ልጆች የዘር ሀረግ “የአንድ አዳምና ሄዋን ልጆች ነን” ብሎ በማመን ሁሉንም ወንድም እህት በማድረግ ለሁሉም እኩል ክብር ሰጥቶ የሚኖር ማህበረሰብ ነው።

ሌላ አዳም ከሌለ ባዕድነቱ ከየት ገባ? ይህንን ባዕድነት የፈጠርነው እኛው ነን፡፡ ችግር ውስጥም የገባነው፡፡ እኔ በራሴ እሳቤ ወንድም ሴትም ሰው በመሆኑ የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች ነን ብዬ ነው የማስበው፡፡

አውራምባ ማህበረሰብ ሁለት ዓይነት የአባልነት ደረጃዎች አሉት። እነሱም የአውራምባ ማህበረሰብ አዲስ ምዕራፍ ባህሪና ልማት ግንባታ ሁለገብ ማህበር (የማህበረሰብ) አባል እና የአውራምባ ማህበረሰብ የገበሬዎችና እደ-ጥበባት ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበር (የህብረት ስራ ማህበር) አባል ናቸው።

የማህበረሰቡ አባላት የሚመራባቸውን እሴቶችና መርሆዎች በማወቅ፣ በመተግበርና እሴቶቹንም ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል እንዲስፋፉ በማድረግ የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ነው።

ማህበረሰቡ ለስራ ያመቸው ዘንድ የሚመራው 12 ኮሚቴዎችን አዋቅሮና አደራጅቶ ነው። እያንዳንዱ ኮሚቴ የራሱ አባላትና የስራ ድርሻ ሲኖረው ከ12 ኮሚቴዎች የልማት ኮሚቴው ዐቢይ ኮሚቴ ነው፡፡

በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚካሄዱትን እንቅስቃሴዎችና የሌሎቹን /የ11ዱን ንዑሳን ኮሚቴዎች/ የስራ እንቅስቃሴዎቻቸውን ዐቢይ ኮሚቴ ይከታተላል፤ ያስተባብራል።

የማህበረሰቡ አባላት በሙሉ በየ15 ቀን አንድ ጊዜ ሰላምን ፍለጋ የቤተሰብ ውይይት ያካሂዳሉ። ለዚህ ውይይት የመወያያ አጀንዳ የሚሆኑት የስራ እቅድ ክንውንን በተመለከተና በጥቅሉ መጥፎ አሰራርና አነጋገርን መዋጋትን በተመለከተ ነው፡፡ የዚህ የቤተሰብ ውይይት ዋና ዓላማ የሰው ልጆች በሙሉ በየቤታቸው እየተወያዩ ችግሮቻቸውን ሁሉ እየፈቱ ዕድገትና ሰላምን ለማምጣት ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ነው።

ንጋት፡- የማህበረሰቡ ዋና ዋና መገለጫዎችስ ምንድናቸው?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- በአውራምባ ማህበረሰብ ውሸት፣ ሌብነት፣ ዘረኝነት፣ ምቀኝነት እና ሀሜት የለም፡፡ ሁሉም ተዋድዶ ስለሚኖር ሰው ወዳጁን አያማም፡፡ ችግር ካለም ተነጋግሮ መተማመን መፍጠር አለበት፡፡ በአውራምባ ማህበረሰብ ሀሜት ወንጀል እና ሀጢአት ነው፡፡ መጥፎ አነጋገሮች እና አሰራሮች በአውራምባ ማህበረሰብ የሉም፡፡

ንጋት፡- በአውራምባ ማህበረሰብ የሴቶች እኩልነት እንዴት ይገለፃል?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- እኩልነቱን ለሴቶች እኛ አልሰጠናቸውም፡፡ ተፈጥሮ የሰጣቸው ነው። ሴት እናት ናት፤ ወንድም አባት ነው፡፡ እናት ከሌለችበት አባት የለም፡፡ አባትም ከሌለበት እናት የለችም፡፡ በፊት ሴቶችን ቀምተናቸው የቆየነውን እኩልነት ነው የመለስንላቸው፡፡ ለአንድ እውነት ግጥም ማንበብ አይጠበቅብኝም፡፡

በአውራምባ ማህበረሰብ የሴቶችና ወንዶች ተብሎ የተለየ ስራ የለም፡፡ ወንድ እንጀራ ይጋግራል፣ ይፈትላል፣ ሴት የምትሰራውን ሁሉ ይሰራል፡፡ ሴቷንም የአባቷን ስራ የከለከላት ማነው? ወንዱንስ የእናቱን ስራ የከለከለው ማነው?

በአውራምባ ማህበረሰብ ስራ በችሎታ እንጂ በፆታ አይደለም፡፡ ስራ የሁላችንም ነው፡፡ ሊጥ አብኩቶ መጋገር ወንጀል ነው እንዴ? ፈትሎ የማይለብስና ጋግሮ የማይበላ ሰው ካለ መሀይምነት ነው፡፡  በማህበረሰቡ ሁሉም ስራ በችሎታ እና በሚያፈጥነው እንጂ በፆታ ልዩነት አይለካም፡፡ አውራምባ ላይም ጭራሽ አይሰራም፡፡ እኛ ታግለን እዚህ አድርሰናል፤ ያሁን ልጆች ግን አያውቁትም፡፡

ንጋት፡- ወጣቱ እናንተ ያለፋችሁትን መንገድ እየተከተለ ነው?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- የእኛ ልጆች ከትምህርት ቤት ጀምሮ ገንዘቡ ሰው እንደሆነና ሰውም ክቡር እንደሆነ ይማራል፡፡ የገንዘቡ ምንጭ ራሱ ሰው እንደሆነ፣ ገበያውም ለሰው ሰው እንደሆነ እና የሁሉም ነገር መሰረት ሰው እንደሆነ ይረዳሉ፡፡

በአውራምባ ማህበረሰብ የሰው ገንዘብ መውሰድ አይቻልም፡፡ መውሰድ ይቅርና ያገኙትን መውሰድ አይቻልም፡፡

በአውራምባ ማህበረሰብ ገንዘብ ማለት በስራ የተገኘ ብቻ ነው፡፡ ወድቆ የተገኘም ቢሆን ለባለቤቱ ይመለሳል፡፡ በማህበረሰቡ አታሎ፣ ሰርቆና የሰውን ገንዘብ ነጥቆ መውሰድ ወንጀል መሆኑን ወጣቶቹ እየተማሩ ነው ያደጉት፡፡

እስካሁንም ወጣቱንም በዚሁ ልክ እየቀረጽንና እየመራን ነው ያለነው፡፡ ምንም ዓይነት ችግር አልገጠመንም፡፡ ችግሮች ቢኖሩም በሚኖረን የውይይት ጊዜ በመወያየት እና በንግግር ጊዜ ሳይሰጠው ይፈታል፡፡

ንጋት፡- በአውራምባ ማህበረሰብ ትልቁ ሀብት ምንድነው?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- በአውራምባ ማህበረሰብ ትልቁ ሀብት ሰው ነው፡፡ የእውቀቱም ሆነ የገንዘቡ ምንጭ ሰው ነው፡፡ ለአውራምባ ማህበረሰብ ዘመዱም ሀገሩም ሰው ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ እስካሁንም የነበረውን የማህበረሰቡን እውቀት ለወጣቱም በሚገባ እያስተማርነው ነው፡፡ እስካሁንም ወጣ ያለ ነገር የለም፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀውም እንኳን እዛው አውራምባ ላይ ነው ስራቸውን የሚሰሩት፡፡ ሰው ሀብት ነው የሚለው የማህበረሰቡ እሳቤ ዛሬ ሶስተኛው ትወልድ ላይ ደርሷል፡፡ ከእንግዲህ ሀገርን ሙሉ እያዳረሰ ነው የሚሄደው፡፡ ግን ፈርታችሁታል፡፡ ለሁሉም መዳረሱ አይቀርምና አስባችሁበት ጠብቁን፡፡

ልጆች ስንሳደብ ካዩ ይሳደባሉ፤ ስንዋሽ ካዩ ይዋሻሉ፤ ስንራገም ያያሉ ይራገማሉ፤ ስንደባደብ ያያሉ ይደባደባሉና የመገብናቸውን ከእኛ ያዩትን ነው የሚያደርጉት፡፡ ልጅ ወላጁንና ቤቱን ነው የሚመስለው፡፡ ይቻላል ወይ? ከማለት ይልቅ እስካሁን ቤቴ ተበላሽቷል ካሁን በኋላ እርም ይሁንብኝ ማለት ይሻላል፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ ነው ዱር ለዱር እያደርኩ ረሃቡንና ጥሙን አንድ ፈጣሪ ይቁጠረው ብዬ እርሱም ረድቶኝ ዛሬ ላይ የደረስኩት፡፡

ንጋት፡- ይዘው የወጡትን ራዕይ በህዝቡ ዘንድ አሳክቻለሁ ብለው ያስባሉ?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- አንድ እርምጃ ብቻ ነው ያሳካሁት፡፡ ዓለም ሁሉ እንዲህ እንዲሆን ነው የምፈልገው፡፡ ገሚሱም እንደ እናንተ ብንሆን ይላል፡፡ እናስ ማን ከለከለ፡፡ መሆን ነው ያቃተን። መንገዱንና መስመሩን አንድ ሰው ካስተዋወቀ መንገዱን አለማወቅ የራሱ ስህተት ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ንጋት፡- የክብር ዶክተሬትዎን መቼ እና ከየት አገኙ? ለእርስዎስ የክብር ዶክተሬቱ ያስገኘው ጥቅምና ፋይዳ ካለ ቢገልጹልን?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- በ2002 ዓ.ም ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ነው የክብር ዶክተሬት ያገኘሁት፡፡ የጂማ ዩኒቨርሲቲ ክብር ይገባዋል፡፡ አመሰግናለሁ። እስከ አውራምባ ድረስ በመምጣት አይቶ እና ተገንዝቦ ነው የሰጠኝ፡፡

በወቅቱም ዶክተር ካሳሁን የሚባል ምሁር ክብር ዶክተሬት ልንሰጥዎት ነው ሲለኝ፡- ምን ሰርቼ ነው አልኩት፡፡ እኛ እኮ ልጆቻችንን አልዳኘንም አንተ ሌሎችን እየመራህ ነው አለኝ፡፡

በእኔ እሳቤ ዶክተር ማለት ሳይንሳዊ እና ከእውቀት ጋር የተያያዘ መሆን አለበት በሚል መለስኩለት፡፡

አክብረን ጠርተናል በማለት አጽንኦት ሰጡኝና ለክብራቸው በመሄድ ዶክተር ቴዎድሮስ የሚባል የዩኒቨርሲቲው ኃላፊ የማዕረግ ልብሱን አልብሶኝ ለማበረታታት ለቀጣይም ከእኔ ብዙ ነገር እንደሚጠብቁ በማሰብ አክብረውኝ የክብር ዶክተሬት ሰጥተውኛል፤ ዳግመኛም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

የጂማ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያሉት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ስለ አውራምባ ዓላማና ምንነት በምርምርና ጥናት አስደግፈው ለተተኪው ትውልድ ሰንደው ሊያስቀምጡ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሊያም አሁን ያለው ትውልድ እንኳን ለቤተሰብ ለሀገርም ስጋት ነውና ሊታሰብ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ንጋት፡- የጂማ ዩኒቨርሲቲ በአውራምባ ማህበረሰብ ምርምርና ጥናት ሰርቷል?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡-  አይ አላደረገም። ነገር ግን በየዓመቱ ተማሪዎችን ይዘው ጉብኝት ይመጣሉ፡፡ ብዙ ነገርን ከማህበረሰቡ አግኝተዋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ እንኳንስ ከሀገር ውስጥ ከአውሮፓ ድረስ አውራምባ ማህበረሰብን ለመጎብኘት መጥተው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያኖች ለትምህርት እያሉ ወደ ውጪ ሀገራት የሚሄዱት ለምንድነው? እኛ ጋር የሌለ ትምህርት እዚህ አለ አይደል እያሉ ይተቹም ነበር፡፡

ንጋት፡- በቀጣይስ ምን ለመስራት አስበዋል?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- በቀጣይ በሀገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ወደ አውራምባ ማህረሰብ እንዲመጡ ሳይሆን እኛ በየዩኒቨርሲቲዎች ተንቀሳቅሰን ተማሪዎችን ለማስተማር ዕቅዱ ነበረን፡፡ ነገር ግን ሀገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ስላልተመቸ ነው፡፡ ሀገራችን ሰላም ከሆነች ዕቅዱ አለን፡፡

ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት?

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- አውራምባ ማህበር ነው ብዬሻለሁ፡፡ ሁሉም በተለያየ ቦታ ተሰማርቶ ይውላል፡፡ ማታ ሲመለሱ አብረን ተገናኝተን ውሎ እንዴት ነበር? ምንስ ጎደለ? የታመመ አለ? ዕቃስ የተሰናከለ አለ ወይ? ብለን የጎደለውን ነገር እንወያያለን፡፡ ወዲያውኑ ምላሽ እንሰጣለን፡፡

ማለዳም ከ2 ሰዓት በፊት ተወያይተን እና ተነጋግረን ነው የምንለያየው፡፡ ከዚያም ባለፈ በየ15 ቀን የስራ እና የህይወት እቅድ ስብሰባ አለን፡፡ ችግርም ካለ መደበቅ የለም ወዲያውኑ ይነገራል፡፡ ማንኛውም ሰው ይህንን መልመድ ቢችል መልካም ነው፡፡

አሁን ሀገራችን ላይ የምናያቸው ችግሮች እየዋሉ እያደሩ መጥተው መፍታት እና መነጋገር የማንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን ችግሮች ውለው ሳያድሩ መነጋገርና መፍታት ለመቻል ልምድ ሊኖረን ይገባል መልዕክቴ ነው፡፡ ሠላም፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

ክቡር ዶክተር ዙምራ፡- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ከእኔ ጋር ቆይታ ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ፡፡