“ለአካል ጉዳተኛ መስራት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መስራት ነው” – አቶ ተሰማ ኤርጫፎ

 “ለአካል ጉዳተኛ መስራት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መስራት ነው” – አቶ ተሰማ ኤርጫፎ

በጋዜጣው ሪፖርተር

አቶ ተሰማ ኤርጫፎ ቃልቾ ይባላሉ:: የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ምክትል ሰብሳቢ እና የሀድያ ዞን አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡

ተወልደው ያደጉት በሀድያ ዞን፥ ሌሞ ወረዳ የላኛው ኮዴ ዱና መንደር 4 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እንደማንኛውም ልጅ ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል፡፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ሊሳና አንደኛ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል የካቲት 2567 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን የመሰናዶ ትምህርታቸውን ደግሞ ዋቸሞ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡፡

በ1999 ዓ.ም ለዩኒቨርስቲ የሚያበቃ ውጤት አምጥተው አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በአፕላይድ ማቲማቲክስ ትምህርት ክፍል ለሦስት ዓመታት ተከታትለው 2001 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም ፓራዳይዝ ቫሊ ከተባለ የግል ኮሌጅ በኢኮኖሚክስ፤ 2008 ዓ.ም እንዲሁ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን /ማስተርሳቸውን/ ደግሞ ሀዋሳ ከሚገኝ አትላስ ከተባለ የግል ኮሌጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በ2013 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡

ከአለማዊ ትምህርት ጎን ለጎን መንፈሳዊ ትምህርታቸውንም ተከታትለው ኢንተርናሽናል ባይብል ኮሌጅ ከተሰኘ ተቋም በድግሪ ፕሮግራም ተምረው አጠናቀዋል፡፡ አቶ ተሰማ ሶስት ወንድ እና ሶስት ሴት ልጆች ላሏቸው ቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ልዩ እንክብካቤ እና ድጋፍ ተደርጎላቸው ያደጉ ናቸው፡፡

የቤተሰብ  እገዛው ትምህርታቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ አግዟቸዋል፡፡ ከክፍል ወደ ክፍል የሚሸጋገሩትም ደረጃ በመውጣት በመሸለም ነበር፡፡ ለዚህ ለስኬታቸው ጉልሁን ሚና የተጫወቱት አጠቃላይ ቤተሰቦቻቸው እንደሆኑ በነበረን ቆይታ አጫውተውናል።

አካል ጉዳት እንዴት እንደገጠማቸው ሲገልፁ፡-  

“ቤተሰቦቼ የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ወጣ ብለው ንግድ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ የ6 ወር ህፃን እያለሁ ለሰፈር ልጆች አስጠብቀውኝ ነበር የሚሔዱት፡፡ አንድ ቀን ታድያ ከታዘልኩበት ሰው ጀርባ ላይ ወደኩኝ፡፡ በዚያ ምክንያት ቀኝ እግሬ ላይ ጉዳት ደረሰብኝ፡፡ ሰውነቴ በሙሉ ፓራላይዝድ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ወደ ህክምናና ወጌሻ ቤት ቢወስዱኝም ከቀኝ እግሬ ውጪ ሌላው ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ ቀኝ እግሬ በጣም ተጎድቶ  ስለነበር ቀዶ ጥገና  ተደረገልኝ፡፡ ግን የሚፈለገው ለውጥ አልመጣም፡፡ በኋላም አልታጠፍ ብሎ ቀጥ ስላለ በከዘራ መራመድ ጀመርኩ” ሲሉ ከወላጆቻቸው የሰሙትን ታሪክ አጋርተውናል፡፡

አቶ ተሰማ በባህሪያቸው ደፋር እና በራስ መተማመንን ያዳበሩ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ለሁለት ሴቶች የትዳር ጥያቄ አቅርበው አካል ጉዳተኛ ስለሆንክ የኛ ምርጫ አይደለህም ቢባሉም፤ ያገቧቸውን የትዳር አጋራቸው አሳምነው በማግባታቸው ደስተኛ ናቸው፡፡

ስለሁኔታው እንዲህ ሲሉ ያስታውሳሉ፡-

“ታላቅ ወንድሟ ጓደኛዬ ስለ ነበር ሙሉ በሙሉ አምኖበታል፡፡ እናትየው ግን ከተጋባን በኋላ እንዴት ለአካል ጉዳተኛ ትሰጣለች ብለው ከታላቅ ወንድሟ ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ እያደር ስንግባባና የእኔን ሁኔታ ሲያዩ ግን የእሳቸው ፍቅር የተለየ ሆነ፡፡ ስሜንም ሲጠሩ ፍቅሬ፤ (አዲላ) ንጉስ እያሉ እያሞካሹ ነው።”

እሳቸው ከአመለካካት ጋር ተያይዞ ለሚደርስባቸው ተፅዕኖ ቦታ አይሰጡም ነበር፡፡ ለትዳር መሠረቱ ከሰውነት አቋም ይልቅ ጥሩ ባህሪ ነው፡፡ ጥሩ ባህሪ ስለነበራቸው ሊያሰናክላቸው የነበረውን  አመለካከት ጥሰው በማሸነፋቸው ትዳራቸው ሰምሯል፡፡

በ2007 ዓ.ም የተመሰረተው ትዳር 10 ዓመታትን አስቆጥሮ ዛሬ ላይ 4 ወንድ ልጆችን አፍረተዋል፡፡ በትዳራቸውም ደስተኛ እንደሆኑ ጭምር ገልፀውልናል፡፡

ሥራ የጀመሩት ሆሳዕና ከተማ ሴችዱና ክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የካዳስካር (መሬት እና መሬት ነክ መረጃዎች ጉዳዮች) ሥራ ሂደት ውስጥ ነው፡፡ በሥራ ሂደቱ እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል። ከ2005 ዓ.ም እስከ 2011 ድረስ ደግሞ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመሬት ልማት መረ/ ባንክ ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሆሳዕና ከተማ መዘጋጃ ቤት የመሬት ልማትና መልሶ ማልማት ሥራ ሂደት ውስጥ የከተማ እርካታ ድምፅ እና ምክትል አረጋጋጭ ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ሥራ ለማግኘት የገጠማቸውን ውጣ ውረድም እንዲህ ሲሉ አጫውተውናል፦

“ተወዳድሬ ካለፍኩ በኋላ ሰው ሀብቱ ላንተ አይሆንም ብሎ ከለከለኝ፡፡ ከኔ ጋር የተወዳደረ ጉዳት አልባ ልጅ ሥራው እንደሚገባው ነገረኝ። የሚያስገርመው ግን ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ 5 ነጥብ መኖሩን እንኳን ግንዛቤ አልነበረውም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከብዙ ክርክር በኋላ መብቴን አስከብሬ ተቀጠርኩ፡፡

“አንዳንድ መስሪያ ቤቶች እስካሁንም ድረስ ስለ አካል ጉዳተኝነት በቂ ግንዘቤ ስለሌላቸው ‹አይችሉም፤ ለእነሱ አይሆንም› ብለው በጅምላ የመፈረጅ ሁኔታ ያንፀባርቃሉ፡፡ ለዚህም ማሳያው በቅርቡ የገጠመኝ የሥራ ሥምሪት ነው ሲሉም ሥራ ከጀመሩ በኋላ የገጠማቸውን ነገር ያነሳሉ፡-

“በክፍላችን ውስጥ የሥራ ስምሪት ሲሰጥ ለእሱ አይሆንም በሚል ከለከሉኝ፤ እኔ ግን ሳትጠይቁኝ ለምን አይችልም ትላላችሁ? በሚል አስተባባሪዬን በማናገር በራሱ መወሰን እንደማይችል አስረዳሁት፡፡

“አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው አዕምሮ ስላለን መሥራት እንችላላን፡፡ ከእናንተ የሚጠበቀው እንድንሠራ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሥራውን ለመሥራት ወደታዘዘው ቦታ የሚሄደው በሞተር ወይም በትራንስፖርት በመሆኑ ውሳኔው ተገቢ አለመሆኑን አስረዳሁ” ሲሉ መሥሪያ ቤቶች አካባቢ አሁንም አካል ጉዳተኞች ላይ የሚንፀባረቁ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና መድሎዎችን በማንሳት ኮንነዋል፡፡

እጅ የማይሰጡት አቶ ተሰማ፥ በየጊዜው ለመብታቸው ይከራከራሉ፡፡ ለመሰል አካል ጉዳተኞች ዘብ እየቆሙ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በየደረጃው ያሉ የአካል ጉዳተኞች ማህበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ቢሆንም፤ ሥራውን በጥልቀት እንዳንሰራ የሚጎትቱን ነገሮች አሉ ይላሉ፡፡ ለዚህም የወጡ መመሪያና ደንቦች እምብዛም አለመሆናቸውን በማንሳት ተግባራዊነታቸውን እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡

በሌላ በኩል ሥራውን ለመሥራት በጀት ያስፈልጋል፡፡ ከኢ.ሰ.ማ.ኮ (ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን) የድጋፍ ደብዳቤ ወስደን ማህበር ለማቋቋም ንቅናቄ ፈጥረን ሀብት አፈላልገን ነበር። ማህበሩን እስከ ወረዳ ለማቋቋም ያገኘነው ገንዘብ በቂ ካለመሆኑም በላይ አንዳንድ የመምሪያ ኃላፊዎች ስንጠይቅ በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ፍቃደኞች አይደሉም ሲሉ አንስተዋል፡፡

ለአካል ጉዳተኛ መስራት ማለት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መስራት መሆኑን በመረዳት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል። ምክንያቱም አካል ጉዳተኝነት ነግሮ የማይመጣ ነገር ስለሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለአካል ጉዳተኞች መሥራት አለበት ይላሉ፡፡ ለዚህም ሚዲያም የአካል ጉዳተኞች አፍ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው 5 እና 10 ብር ከመስጠት ባለፈ ህብረተሰቡም ተቆርቋሪ ሆኖ በእኔነት መንፈስ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

መንግስት ትኩረት መስጠት ያለበት የሚነገረው ነገር ተፈፃሚነት እንዲኖረው ማድረግ ላይ ነው፡፡ በጣም የተቸገርነው ነገር ቀደም ሲል ተራድኦ ተብሎ ለአካል ጉደተኞች የሚያዝ በጀት ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ ሁኔታ የለም፡፡

20 ሚሊዮን የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍል አካል ጉዳተኛ በሆነበት ሃገርስ ለምን ዝም ይባላል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ለየትኛውም መስሪያ ቤት ሥራ ማስኬጃ በጀት እንደሚመደብ ሁሉ፥ ለአካል ጉዳተኞችም መመደብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

የአካል ጉዳተኞችን ችግር ነቅሶ ለማውጣት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ መሥራት አስፈላጊ ነው የሚል ፅኑ እምነት አላቸው፡፡ እንደ ኣካል ጉዳታቸው ለይቶ መሥራት የሚችሉ፣ አረጋዊ የሆኑ እና ሙሉ በሙሉ መሥራት የማይችሉ አካል ጉዳተኞችን በሚል ተለይቶ ድጋፍ ቢደረግላቸው መልካም ነው፡፡ ለሚሠሩት ደግሞ መሥሪያ ቦታ ለማመቻቸት በሚዲያ የታገዘ ግንዛቤ ፈጥረን ብንሠራ የመንግስትንም የአካል ጉዳተኞችንም ችግር እንቀንሳለን፡፡ 

በየዓመቱ ዘላቂነት ያለው በጀት ቢመደብ እና በሚዲያ የታገዘ የግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ቢሰራ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን መቀንስና መቅረፍ ይቻላል ይላሉ፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ዋነኛ ፈተና የሆነው ካለማወቅ እና ከተሳሳተ ግንዛቤና አመለካከት የሚመነጩ ድርጊቶች ናቸው የሚሉት አቶ ተሰማ፤ ያደጉበት አካባቢ የነበረው ማህበረሰብ ሊያሸማቅቋቸው ይሞክሩ እንደነበር ያወሳሉ፡-

“ማሳ ውስጥ ከብቶች ሲገቡ ሳባርር አንዳንድ ሰዎች እሱ እኮ ሽባ ነው አይችልም ይሉኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ልጅም ስለነበርኩ እንደዛሬው ባይገባኝም ይሰማኝ ነበር፡፡

“እኔ አካል ጉዳተኛ መሆኔ ትዝ ብሎኝ አያውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ስመለስ ገላጣ ሜዳ ላይ በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ዘነበ፡፡ ከኛ ቤት እስከ ትምህርት ቤቱ 2 ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ሙሉ ዝናቡ እኔ ላይ ወረደ፡፡ ያቺ ቀን አካል ጉዳተኛ በመሆኔ ነው የደበደበኝ በሚል የተሰማኝን ስሜት መቼም አልረሳሁም” ሲሉ ያዘኑበትን ገጠመኝ አጋርተውናል፡፡

“ዛሬ እንደማንኛውም ግለሰብ ምንም ሳይገድበኝ ሥራ ይዤ፣ ትዳር መስርቼ፣ እና  ልጆች ወልጄ በትዳሬ ተከብሬ መኖር መቻሌ በጣም ያስደስተኛል” ሲሉም የሚደሰቱበትን የህይወት ክፍል ገልፀውልናል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ስንል ላነሳንላቸው ሃሳብ ሲመልሱ፡- “አካል ጉዳተኛ ማለት አለመቻል አይደለም፡፡ አካል ጉዳተኞች አዕምሯቸውን ለሥራ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ የሥራ ትንሽ እንደሌለው በመረዳት መሥራት እና ከልመና ይልቅ የሥራ ባህልን ማዳበር ቢችሉ ጥሩ ነው” ሲሉ መክረዋል፡፡

መስራት የሚችል አካል ጉዳተኛ መለመን የለበትም የሚል ፅኑ አቋም ያላቸው አቶ ተሰማ፤  ሥራ የማይሰሩ የማውቃቸውን አካል ጉዳተኞችን ሙሉ የሊስትሮ እቃ ገዝቼ ልስጣችሁ? ሲሏቸው አንዳንዶቹ መንገድ በመቀየር ጭምር እንደሚሸሿቸው አንስተዋል፡፡

የወደፊት ዕቅዳቸውን በተመለከተ ባነሱት ሃሳብ፡- ብዙ ነገሮችን እንደሚያቅዱ እና ከፋይናንስ እና ከመሥሪያ ቦታ ጋር የተያያዙ ችግሮች ፈተና እንደሆነባቸው ገልፀዋል፡፡

“ከመንግስት ሥራው ይልቅ የጥምር ግብርናን ብሰራ ደስ ይለኛል” የሚሉት አቶ ተሰማ፤ ትንሽ መሬት ቢኖር ብዙ ሥራ አጥ ሰዎችን እና መሥራት የሚችሉ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ የመስራት ዕቅድ አላቸው፡፡

ዛሬ ላይ በሕይወት የሌሉትን አባታቸውን ጨምሮ በሁሉ ነገር ሲደግፏቸው ለነበሩ እናታቸው እንዲሁም የልጆቻቸው እናት ለሆኑት ባለቤታቸው እና የባለቤታቸው ወንድም ላዳረጉላቸው መልካም ነገር እና የማያቋርጥ ድጋፍ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡