“ከገንዘብ ይልቅ ዕውቀትን አስቀደምኩ” – ወለላ ሰይድ

“ከገንዘብ ይልቅ ዕውቀትን አስቀደምኩ” – ወለላ ሰይድ

በደረሰ አስፋው

“የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ወልዶ ተንከባክቦ ነው ያሳደገኝ፡፡” ዩኒቨርስቲ ገብቶ የቀለም ትምህርት ከመማር ይልቅ በሙያ የመሰልጠን ዓላማ ስለነበረኝ በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምኞቴ ሰምሯል፡፡ የቴክኖሎጂ ባለቤት የመሆን ህልሜም ተሳክቶልኛል፡፡ በሴትነቴ የሚደርሱብኝ ተጽእኖዎችን አልፌ ያገኘሁት ስኬት በመሆኑ ልዩ ትርጉም እሰጠዋለሁ፡፡

“ገንዘብን ሳይሆን እውቀትን ማስቀደሜ ለዛሬው ውጤት አብቅቶኛል” የምትለው የዛሬው የእቱ መለኛ አምድ ባለታሪካችን በእርግጥም ዛሬ ላይ በስራዋ በክልል፣ በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እየተሳተፈች እውቅናን ብታገኝም እዚህ የደረሰችው ግን ብዙ ችግሮችን ተቋቁማ በማለፏ ነው፡፡

“እንደወንድ ሳይሆን እንደሴት ለምን አታስቢም የተባልኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ሴት ሆነሽ እንይሽ ተባልኩ፡፡ አንቺ ይሄን ልትሰሪ አትችይም ተብዬ የማናናቅ ተግባርም ተፈፅሞብኝ ነበር። ሰርቼ አይቶ እንኳ የማያምን አለ፡፡ ይህ አባባል የግድ ሴት ኩሽና ገብታ መጋገር፤ ቤት ውስጥ ቁጭ ብላ ልጅ ማሳደግ ብቻ ተግባሯ አድርጎ የመመልከት አስተሳሰብ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ይህን እና መሰል የሴትነት ተግዳሮቶችን አልፌ ነው ለዚህ የበቃሁት ስትልም ነው የገለጸችው፡፡

ለዚህ የስኬት ጉዞዋ ደግሞ በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የቆየችባቸው 12 ዓመታት የትምህርትና የማስተማር ቆይታዋ በር ከፋች እንደሆነላት ነው ያስረዳችው፡፡ ቀድሞም በውስጧ ታምቆ የቆየውን ክህሎቷን እንድትጠቀምበት አቅም ፈጥሮላታል። ለዚህም ይመስላል የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ማህበረሰብን እና የሲዳማ ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ላደረጉልኝ ድጋፍ ሳላማሰግናቸው አላልፍም ስትል ሀሳቧን የጀመረችው፡፡

ወጣት ወለላ ሰይድ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው ሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ ከመጀመሪያ እስከ 2ኛ ደረጃ የተማረችው በታቦር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከ10ኛ ክፍል በኋላ ሀዋሳ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ገብታ በብየዳ ሙያ በ10+3 ተማረች፡፡ በኮሌጁም በሙያው ታንጻ አድጋበታለች፡፡ በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባገኘችው ዕውቀት ለሌሎች ብርሃን ለመሆንም በአለታ ወንዶ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ በረዳት መምህርነት ተቀጥራ ስራዋን ጀመረች፡፡ ሙያውን ለማሻሻልም ወደ ዱራሜ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ገብታ የመማር እድል አግኝታለች፡፡ ስልጠናዋን እንዳጠናቀቀችም ወደ ሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተመልሳ በረዳት መምህርነት መስራት ጀመረች፡፡

በዚህ ላይ እያለች መንግስት ባመቻቸላት የትምህርት ዕድል ወደ አዳማ በማቅናት በማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰጠውን ትምህርት ተከታትላ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች፡፡ በኋላም ተመልሳ ያገለገለችው ሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ነው፡፡ ከረዳት መምህርነት ወደ አስተማሪነት የማደግን ዕድል ያገኝችበት በመሆኑ ለተጨማሪ ዕድገትና እውቀት አነሳሳት፡፡

ከ2 አመት የስራ ቆይታ በኋላ የሲዳማ ክልል በሰጣት የመማር ዕድል በማኑፋክቸሪንግ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ 2ኛ ዲግሪዋን (ማስተርስ) ይዛለች፡፡ የወለላ ሙያዋን በእውቀት የማዳበር ስራ በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም። ፌደራል መንግስት ለክልሎች በሚሰጠው ልዩ የስልጠና ዘርፍ በምታገኘው የትምህርት ዕድልም በተደጋጋሚ ተጠቃሚ ሆናለች። እውቀቷን አጎልብታለች፡፡ ባገኘቻቸው ተጨማሪ እውቀቶችም እራሷን ከመጥቀም ባሻገር ለኮሌጁም የምታበረክተው አስተዋጽኦ እየጎላ ሄዷል፡፡ የላቀ የፈጠራ ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል። ይህም በክልል እና በፌደራል በተከናወኑ የፈጠራ ሥራ ውድድሮች የእውቅና ሽልማት ባለቤት አድርጓታል፡፡

በሴቶች የማይደፈር በሚመስለው በዊልዲንግ ኢንስትራክተር (ብየዳ) ሙያ በቀሰመችው ስልጠና ተጨባጭ እውቀትን አጎልብታለች፡፡ በ6 ዓመታት የክረምት የሙያ ስልጠና ያገኘችው ይህ የሙያ ዘርፍ በሚገባ ልምድ እንድታካብት አስችሏታል፡፡ ስልጠናውም አለምአቀፍ “ዌልደር” የመሆንም ዕድልን አጎናጽፏታል፡፡ ሶፍትዌሮችን፣ የክህሎት ክፍተት ያለባቸውን የሙያ ዘርፎችንም በተከታታይ የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ አቅሟን አሳድጋለች፡፡

“ለመለወጥ የራስ መሰጠትም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው” ያለችው ወጣቷ ስራ ፈጣሪ የሚሰጣትን እድል በአግባቡ በመጠቀሟ የተገኘ ፍሬ በመሆኑ የእሷም አስተዋጽኦ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ላስመዘገበችው እመርታም በ2013 ዓ.ም በክልል እና በፌደራል ደረጃ በተዘጋጁ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ውድድሮች አሸናፊ የመሆን እድልን አጎናጽፏታል፡፡ የ25 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆናለች። ይህ ሽልማትና እውቅና ለበርካታ ቁም ነገሮች እራሷን እንድታዘጋጅ አነሳስቷታል፡፡ በወቅቱ ይህ የአሸናፊነት ስነ ልቦናም ለውጭ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንድትሆን አድርጓት ነበር፤ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ሳይሳካ ቢቀርም፡፡

በ2025 (2017 ዓ.ም) የሲዳማ ክልልን ወክሎ ወደ ፌደራል ለውድድር የሚቀርበው ወጣት፥ ወለላ የተሳተፈችበት በማኑፋክቸሪንክ ዘርፍ አሸናፊ የሆኑበት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው፡፡ የፈጠራ ስራቸው የወዳደቁ ፕላስቲኮችን ይቆራርጣል። ፈጭቶ ወደ ማጠቢያ ይወስዳል፡፡ ከዚያም በራሱ ወደ ማድረቂያ የሚወስድ ማሽንን ነው ያጎለበቱት። ይህን ሂደት ካለፈ በኋላ ወደ ፋብሪካ በመላክ በመልሶ ማልማት ሂደት ይውላል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ በፌደራል ጭምር እውቅና አግኝቷል፡፡ ከሌሎች የሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን ባዘጋጁት የቴክኖሎጂ ፈጠራ የራሳቸው ድርጅት የማቋቋም ውጥን እንዳላቸው ነው የምትገልጸው። በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክታቸውም በሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሚሰለጥኑ ልጆችን በመቅጠር ተጨማሪ የስራ ዕድል የመፍጠር ውጥን አላቸው፡፡

ቴክኖሎጂው የስራ ዕድልን ከመፍጠሩ ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንደሆነ የገለጸችው ወለላ፥ የሀዋሳ ሀይቅንና አካባቢውን በተጣሉ ውሃ መያዣ ፕላስቲኮች ከመበከል የሚታደግ መሆኑንም ነው ያስረዳችው። የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን በመድፈንም የጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት የሚሆነውን የሚታደግ ነው፡፡

የፕላስቲክ ምርቱን ለቅመው ከሚያመጡ ግለሰቦች አንዱን ኪሎ በ30 ብር ይረከባሉ፡፡ ይህ ተፈጭቶ፣ ታጥቦና ደርቆ አዳማና ቢሾፍቱ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞችና ፋብሪካዎች አንዱን ኪሎ በ140 ብር ይሸጣሉ፡፡ ወደፊትም ጥሬ ዕቃውን እራሳቸው ወደ ሌላ ግብአትነት በመቀየር የማምረት ዓላማ እንዳላቸው ነው የተናገረችው፡፡

የጋራ ተጠቃሚነትን በማንገብ የፈጠራ ባለቤት ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው ወለላ የፈጠራ ባለቤት መሆኗ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን እንዳሳደገላት ነው የምትገልጸው፡፡ ደመወዝን ብቻ ከመጠበቅ ወጥታ በትርፍ ጊዜዋ በምትሰራው ተጨማሪ ገቢ እንድታገኝ ዕድል ፈጥሮላታል። ህይወቷን ቀይሯል፡፡ በምትሰራቸው የፈጠራ ስራዎቿ ኦርቢት፣ ኢንተርፕርነር ዲቨሎፕመንት፣ በሰመር ካፕ፣ በተዘጋጁ ውድድሮች ተሳትፋ ከ200 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆናለች። እንደሀገርም ግብር በመክፈል የፈጠራ ስራዋ ለሀገርም እየጠቀመ ነው፡፡ የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል ባሻገር ለሰዎችም የስራ ዕድል ፈጥራለች፡፡

የፈጠራ ስራቸውን በክልል እና በፌደራልና ደረጃ ለእይታ በማቅረብ የገበያ ትስስር እየፈጠሩ ነው፡፡ ማሽኑን ከሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ትዕዛዝ እየተቀበሉ ነው፡፡ የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ይህን የፈጠራ ስራ አምርቶ የመሸጥ ፈቃድና እውቅና ስለተሰጠው በዚሁ በኩል ሽያጭ ይደረጋል፡፡ የወጣት ወለላ እና ጓደኞቿ የተክኖሎጂ ፈጠራ በዚህ ብቻ የተገታ አይደለም፡፡ ለእርሻ ተግባር የሚሆን ማረሻ፣ የእንስሳት መኖ መፍጫ ለማምረትም በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

ወጣት ወለላ የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቤቴ ነው ትላለች፡፡ ከተማሪነት ጀምሮ እስከ አስተማሪነት የዘለቀ የአብሮነት እድሜን አስቆጥራበታለች። ከሰርተፊኬት የጀመረው ትምህርቷ እስከ 2ኛ ዲግሪ የደረሰ እውቀትን ቀስማበታለች፡፡ በክልል፣ በፌደራል እንዲሁም አለም አቀፍ የሆኑ አጫጭር ስልጠናዎች የተለያዩ የሙያ ዘርፎችን ቀስማበታለች፡፡ ለዛሬው የፈጠራ ባለቤት የመሆን ሚስጥሩም ይሄው የቀሰመችው እውቀት ነው። በስራ እና በትምህርት 12 ዓመታት ያስቆጠረው ልምዷም ነገን ለተሻለ ውጤት እያነሳሳት እንደሆነና ይህንንም እውን እንደምታደርገው ነው በልበ ሙሉነት የምትናገረው፡፡

በሀገራችን በሴቶች ላይ ዘመናት የዘለቀ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ሀይማኖታዊ ተጽእኖዎች ተጭኗቸው ዘልቋል፡፡ እሷም ይህ እጣ ፈንታ ሳይገጥማት አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ ተጽእኖውን አሸንፎ በመውጣት ለዛሬው ዕድል እንደበቃች ነው የምትገልጸው፡፡ ሴቶች በተለያዩ ሙያዎች ቢሳተፉ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ከተሞክሮዋ ተረድታለች፡፡

“እኔ እድሉን ስላገኘሁ ተጠቃሚ ሆኛለሁ። አቅሙና ተሰጥኦው ያላቸው በርካታ ሴቶች ያሉባቸውን ጫናዎች አሸንፈው መውጣት ይገባቸዋል። መንግስት ለሴቶች ያመቻቸውን ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ አልችልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር አለባቸው” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

ወጣት ወለላ ወደፊት ለመሆን ያሰበችው ነገር አለ፡፡ ዌልደር ኢንጅነር (የብየዳ ስራ) ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ የመማርና አቅሟን የማሳደግ እንዲሁም ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ባለሙያ የመሆን ውጥን አላት፡፡ እስካሁን የሚሰራው የብየዳ ስራ በልምድ እንጂ በሳይንስ የተደገፈ አለመሆኑን ታስረዳለች፡፡ ይህን አሰራር ለመቀየርም ሳይንሳዊ እውቀትን የመጨበጥ አላማ አላት፡፡ በሀገራችን በዚህ ዘርፍ ዕውቅና ያላቸው 80 ባለሙያዎች ብቻ እንደሆኑ ጠቅሳ እሷም የዚሁ እድል ተጠቃሚ ለመሆን የትምህርት ዕድል ማግኘቷን ነው የተናገረችው፡፡ በሀገር ደረጃ በብየዳ ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር በማረም ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን የማስቀረት ሀሳብ አላት፡፡