እንደ ሃገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማፋጠን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን በሚገባ መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
በጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ትምህርት መምሪያ “ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሁለንተናዊ ሃገር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ለ2 ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየ ዞን አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽንና ውድድር ተጠናቋል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትልና የፈጠራ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን፤ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ በሚሰራቸው ውጤታማ ስራዎች እንደ ክልል የተሻለ መሆኑንና ይህም የዞኑ አስተዳደር ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
ከሚያሳዩት ውጤታማ ስራ አኳያ በተቋማት መካከል የሚደረገው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፤ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የትምህርትና የፈጠራ ስራዎች የሁሉም ነገር መሰረት በመሆናቸው ሁሉም መዋቅሮች ዘርፎቹን በተገቢው መደገፍና ማገዝ ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
በመሆኑም በቀጣይ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ በዞን ደረጃ የኢንኩቤሽን ሴንተር ለማቋቋም ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ዋና አስተዳዳሪው።
የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ የሳይንስና የፈጠራ ስራ ውድድርና ኤግዚቢሽን በዞን ደረጃ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ መደረጉን አስታውሰዋል።
የፈጠራ ስራዎች ባሉበት ተገቢው ድጋፍ ተሰጥቷቸው ለአካባቢው ህብረተሰብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማስቻልና የፈጠራ ባለሙያዎችን ማበረታታትና ለቀጣይ የተሻለ በሃገር ብሎም በአለም ደረጃ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን ማቅረብ እንዲችሉ ማስቻል የዝግጅቱ ዋና አላማ መሆኑን ገልፀዋል።
መሰል ውድድሮችና ኤግዚቢሽኖች የትኛውም የፈጠራ ስራ ያለው አካል በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅምና የፈጠራ ስራ ውጤቱ ለህዝቡ እንዲተዋወቅና በስፋት ተግባር ላይ እንዲውል እድል ይፈጥራልም ብለዋል።
ውድድሩ በተማሪ፣ በመምህራን፣ በኢንተርፕራይዝና በግል ተወዳዳሪዎች መካከል እንደተካሄደም ተመላክቷል።
እንደሃገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማፋጠን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን በሚገባ መደገፍ እንደሚያስፈልግ አቶ ደምስ ተናግረዋል።
መሰል ኤግዚቢሽንና ውድድሮችን ከማዘጋጀት ባለፈም ውጤታማ የሆኑና እንደሃገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ወሳኝ የሆኑትን እየተመረጡ የፈጠራ ስራ ውጤቶችን ወደታለመላቸው አላማ እንዲሸጋገሩ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ይህ ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊታከልበት ይገባልም ነው ያሉት።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም በበኩላቸው፤ ሃገራችን ካቀደቻቸው በርካታ እቅዶች መካከል አንዱ ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት መሆኑን አስታውሰው መሰል ኩነቶች ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር በማስደገፍ የሳይንስ ትምህርቶችን በማጠናከር የተቀመጠውን አላማ ከግብ ለማድረስ ያግዛልም ብለዋል።
አመቱን በዞኑ ያሉ ትምህርት ቤቶች የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች የሚመሩበት እቅዶች በማስቀመጥና መግባባት ላይ በመድረስ በየትምህርት ቤቶቹ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ውድድሮች ሲደረጉ መቆየቱን ተናግረዋል።
የኤግዚቢሺኑና የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባዩዋቸው የፈጠራ ስራ ውጤቶች መደሰታቸውን ገልፀው በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
በመድረኩ ከ95 በላይ የፈጠራ ስራዎች ለኤግዚቢሽንና ለውድድር የቀረቡ ሲሆን በየተቋማቱና በየዘርፉ ከአንደኛ እስከ ሶስት የወጡ አሸናፊዎች ማበረታቻና እውቅና ተበርክቶላቸዋል።
የኤግዚቢሽኑና የውድድሩ አሸናፊዎች በሰጡት አስተያየትም ውድድሩ መዘጋጀቱ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለብዙሃኑ ለማስተዋወቅና ለቀጣይ የተሻለ እድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን ገልፀው የተበረከተላቸው ማበረታቻና ሽልማት በቀጣይ ለተሻለና ለላቀ ስራ የሚሰናዱበት የሞራል ስንቅ ነው።
ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የእርሻ መሳሪያዎችን የማምረት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ
በሆሳዕና ከተማ በዋቸሞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ የሆነው ታዳጊ ብሩክ ግርማ ሮኬት ፣ ደሮኖችን፣ ደማሚት (Dymamet) ከነ መቆጣጣሪያ ስርዓት የፈጠራ ውጤት
በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ ልማቶችን በጥናትና ምርምር አስደግፎ በመሥራት ረገድ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ