“የትኛውም ስራ ፍላጎትንና ጥረትን ይጠይቃል”

“የትኛውም ስራ ፍላጎትንና ጥረትን ይጠይቃል”

በአለምሸት ግርማ

ወጣቶች መሆን የሚፈልጉትን መለየት እንዲችሉ የቤተሰብ ወይም የቅርብ ሰዎች እገዛ ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ከእገዛው ባሻገር የራሳቸው የውስጥ ጥንካሬ ለስኬታቸው ትልቁን ድርሻ ይይዛል።

የዛሬው ባለታሪካችን በሁለት የተለያዩ የትምህርት መስኮች፥ ከሁለት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቋል። በህይወቱ የተሻለ ደረጃ ለመድረስም ከቤተሰቡ ጋር በመተጋገዝ እየሰራ ይገኛል። ለስራው አክብሮት ስላለው፥ ያላግባብ የሚያጠፋው ጊዜ የለውም።

ኢንጂነር አማኑኤል ታደሰ ይባላል። ተወልዶ ያደገው ጠንባሮ ልዩ ወረዳ፥ ሙዱላ ከተማ ነው። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርቱን በከተማው በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተከታትሏል። ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ እስከ አስራ ሁለተኛ ድረስ በከተማው በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ሃይስኩል) በመከታተል በ2004 ዓ.ም አጠናቋል።

ባመጣው ከፍተኛ ውጤት በ2005 ዓ.ም በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ለመከታተል በቃ። ከአምስት ዓመታት የትምህርት ቆይታ በኋላ በ2009 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል። ከዚያም ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ኦሞ ኩራዝ 5 በኮንስትራክሽን ዘርፍ ባሸነፈ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ አገልግሏል።

ይሁን እንጂ በሙያው ከዚያ በላይ አልቆየም። ስራውን ትቶ እንደገና ወደ ትምህርቱ ዓለም ተመለሰ። መመለስ ብቻ ሳይሆን የሙያ ዘርፉንም ከምህንድስና ወደ ጤና ቀይሯል። ሙያውን የቀየረበት የተለየ ምክንያት ይኖረው እንደሆነ ጠይቀነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፦

“በልጅነቴ በተለይም አምስተኛ ክፍል እያለሁ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራችን ወደ ፊት ምን መሆን እንደምንፈልግ ጠይቀውን መሃንዲስ መሆን እንደምፈልግ ነግሬያቸው ነበር። ያም ሁል ጊዜ በአዕምሮዬ ይመላለስ ነበር። በወቅቱ ደግሞ የምህንድስና ሙያ ሁሉም መሆን የሚመኘው ስለነበር ቤተሰቦቼም በዕቅዴ ደስተኛ ነበሩ። ያንንም አሳክቻለሁ። ከቆይታ በኋላ ከቤተሰብ መካከል በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ስለነበሩ፥ ወደ ጤናው ዘርፍ እንድገባ ሃሳብ ሲያቀርቡልኝ አምኜበት ወደ ጤናው የሙያ ዘርፍ ልገባ ችያለሁ”

ከኦሞ ኩራዝ ተመልሶ ሻሸመኔ ፓራዳይዝ ኮሌጅ በመግባት የፋርማሲ ትምህርት መከታተሉን ቀጠለ። በዚያም ለአምስት ዓመታት ትምህርቱን ተከታትሎ በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቅ ችሏል። አሁን በመድሐኒት ቤት ውስጥ እየሰራ ሲሆን፤ ስለስራው እንዲህ ሲል ይናገራል፦

“የትኛውም ስራ ፍላጎትና ጥረት ይጠይቃል። ችላ ካሉት የትኛውም ስራ ለስኬት አያበቃም፡፡ ተማሪ ትምህርቱን ችላ ካለ ውጤታማ መሆን አይችልም። ውጤታማ ለመሆን ለትምህርቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊያጠና ይገባል። አርሶ አደሩም ሲያርስ ደጋግሞ በደንብ ካላረሰ የሚፈልገውን ምርት ማግኘት አይችልም። በግል ስራ የተሰማራ ሰውም ሳይደክምና ሳይታክት መስራት አለበት። ድካም ቢኖር እንኳን ድካሙን ተቋቁሞ ሊሰራ ይገባል። ስለዚህ በቸልተኝነት የሚሰራ ስራ ስኬታማ አያደርግምና ማንም ሰው ሲሰራ ከልቡ መስራት አለበት። እኔም ወደ ሙያው ከገባሁ በኋላ በፍላጎትና በትጋት እየሰራሁ እገኛለሁ”

በህይወትህ የማትረሳው ገጠመኝ ካለ ብለን ላቀረብንለት ጥያቄም እንዲህ ሲል መልሶልናል፦

“በምህንድስና ሙያዬ እየሰራሁ በነበርኩበት ወቅት ከዕለታት በአንዱ ቀን ከምሰራበት ቦታ ስራዬን ጨርሼ የሚወስደኝን መኪና እየጠበኩ ነበር። ለካ መኪናው መንገድ ላይ ተበላሽቶ ነበር። እኔም ለሰዓታት ከጠበኩ በኋላ ሳላውቀው ሰዓቱ መምሸት ጀመረ። በወቅቱ ትኩረቴ ስልኬ ላይ ነበር፥ ድንገት ቀና ብዬ ስመለከት ለካ በዙሪያዬ ተኩላ ከቦኝ ነበር። ከመጠን በላይ ቁጥር ያላቸው ተኩላዎች በዙሪያዬ ከበውኝ ሳይ በጣም ደነገጥኩኝ። ከተኩላ ማምለጥ ከባድ ነገር ነውና፤ ማምለጥ የማልችልበት ሁኔታ ተፈጠረ። መቼም አትሙት ያለው ነፍስ አይሞትምና ከርቀት ያሉ የሳይት ሰራተኞች ሮጠው መጥተው ተኩላዎቹን በማባረር አትርፈውኛል። እንዲሁም አንድ ጊዜ መሳሪያ የያዙ ሰዎች በማጎ ፓርክ አካባቢ አስቁመው ሊዘርፉን ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም ወቅት ሾፌራችን ጠጋ ብሎ የሚቆም በማስመሰል ፍጥነቱን ጨምሮ ለማምለጥ ችለናል። መኪናው የሚቆም መስሏቸው ተዘናገተው ስለነበር ከራቅን በኋላ ቢተኩሱብንም የተተኮሰው አላገኘንም። እነዚህን ገጠመኞች መቼም አልረሳቸውም፥ እግዚአብሔር ነፍስን ከሚያሳጡ ክፉ ገጠመኞች አድኖኛል፡፡”

አሁን ባለበት ስራ ደስተኛ ስለሆነ፥ ከዚህ በኋላ ያለው ዕቅድ ስራውን በታማኝነትና በጥንካሬ መስራት ነው። ስራውን በማጠናከር ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚፈልግም ይናገራል።

የግል ህይወቱን በተመለከተ 2014 ዓ.ም ትዳር መስርቶ የአንድ ልጅ አባት ለመሆን መብቃቱንና፥ ባለቤቱ የመንግስት ሰራተኛ እንደሆነችም አጫውቶናል።

በስራ ህይወቱ ደስተኛ ቢሆንም ስራው በባህሪው አንዳንድ ተግዳሮቶች እንዳሉት አልሸሸገም። “መድሐኒት ለመግዛት ብዙ ዓይነት ሰው ይመጣል። ተናዶ የሚመጣ አለ። ማዘዣ ይዞ መጥቶ ስንሰጠው ይሔ አይደለም፥ ብሎ የሚከራከርም አለ። ራሱ ያመነበትን ብቻ የሚፈልግ አለ፤ ለማስረዳት ብዙ እንጥራለን። በዚህ መሃል አንዳንዴ ያልተገባ ባህሪ የሚያሳይም ያጋጥማል። በሙያው ያለው ትልቁ ተግዳሮት ይሔ ነው። ስለዚህ ሁሉንም እንደየአመሉ በትዕግስት ማስተናገድ ያስፈልጋል። ደስታን የሚሰጠን ዛሬ ታሞ የመጣ ሰው፥ በሌላ ጊዜ ተሽሎት ስናይ ነው። በዚህ ምክንያት ሙያውን እወደዋለሁ። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ወደ ሌላ ሙያ የመግባት ዕቅድም ዓላማም የለኝም። እግዚአብሔር ከፈቀደ ወደ ፊት ስራዬን አቁሜ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ መግባትና ማገልገል ነው ህልሜ፤ ከዚህ ሌላ ህልምም፥ ሆነ ፍላጎት የለኝም።”

የትምህርቱም የስራውም ሃሳብ የመጣው ከቤተሰብ ቢሆንም፥ በአሁኑ ወቅት ስራውን ወዶት እየሰራ ይገኛል። ብዙ ዓይነት ልምድም እያገኘበት ስለመሆኑንና ለስራ ያለው ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ይናገራል፦

“ስራው በባህሪው ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚጠይቅ ሙያ ነው። ስለዚህ በቸልተኝነት በመዘናጋት የሚፈጠር ትንሽ ስህተት ከባድ ዋጋ ያስከፍላል። ቀጥታ ከሰው ጤናና ህይወት ጋር የተገናኘ በመሆኑ በጥንቃቄ መስራትንም ይጠይቃል። በሙያው ቅድሚያ የሚያስፈልገው ዕውቀት ነው። ዕውቀት ያለው ሰው ስራውን በኃላፊነት ለመወጣት አይቸገርም” ሲልም ስለሙያው ያብራራል።

ህይወት ሁል ጊዜ በከፍታ ብቻ አይጓዝም። ብዙ ውጣ ውረዶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ምንም ነገር ቢጋጥም ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ከውድቀት መማር ይቻላል። አንድ ስራ ባይሳካ ወይም ችግር ቢያጋጥም ሌላ አማራጭ በመፈለግ ታድሶ መነሳት ይገባል። ተማሪዎች ሲማሩ ከፊት ለፊታቸው ሊጨብጡት የሚችሉት ዓላማ አስቀምጠው ሊማሩ ይገባል። በጉጉትና በፍላጎት ከተማሩ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይችላሉ። በንግድ ስራ የሚሰማሩም እንዲሁ፤ አንድን ነገር ከመወሰናቸው በፊት በደንብ ማሰብ ያስፈልጋቸዋል።

በ2010 ዓ.ም ኩራዝ5 ስሰራ ሙቀቱ 42/43 ዲግሪ ነበር። አካባቢው ሞቃታማ ስለሆነ ማታ ውጪ ነው የምንተኛው። ቤት ውስጥ መተኛት የማይታሰብ ነው። ከዕለታት በአንዱ ቀን ውጭ ተኝተን እያለ ጊንጥ ጆሮዬን ነደፈችኝ፥ ከዛ መርዙ እንዳይሰራጭ ጆሮዬን በቀጭን ገመድ አሰሩ። የተነደፈውን ለማቃጠል ክብሪት ሲፈለግ ማግኘት አልተቻለም፥ ከዛ መዶሻና ሚስማር ፈልገው በመቀጥቀጥ በጋለው መዶሻ ጆሮዬን ማቃጠል ጀመሩ። ከዛ ድኜ ቁስሉ ተራግፎ ጆሮዬ ጠቁሮ ቀረ። በወቅቱ ብዙ ጓደኞቼ ቻሌንጁን ፈርተው ስራቸውን ትተው ወጥተዋል። ስለዚህ ወጣቶች የሚገጥማቸውን ፈተና ፈርተው ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም። ተደላድሎ መቀመጥን የሚፈልጉ ከሆነ የሚመኙትን ነገር በቀላሉ ማግኘት አይችሉም። ችግሮችን ተጋፍጦ መስራት ካልሆነም፤ የተሻለ ልምድ እና እውቀት ያላቸውን ሰዎች ማማከር ተገቢ ነው።

ኢንጂነር አማኑኤል ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን የስራ ተነሳሽነት ሊያዳብሩትና ጊዜያቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል ሲልም ምክሩን ለግሷል።