“መታመሜን ነግሬያችሁ ነበር”

“መታመሜን ነግሬያችሁ ነበር”

በአንዱዓለም ሰለሞን         

እንደምን ሰነበታችሁ? ሳምንቱስ እንዴት አለፈ? ሰሞኑን አንድ ዘመዴ ለቅሶ ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ እናም አንዳንድ ነገሮችን መታዘቤ አልቀረም፡፡ ትዝብቴም እነሆ የዛሬው ወግ መነሻና ማጠንጠኛ ሆነ፡፡

እኔ ምለው፤ ለቅሶ ቤት ግን መቼ ነው መጠጥ ይዞ ማምሸት የተጀመረው? ነው ወይስ እኔ ለቅሶ ከደረስኩ ስለቆየሁ ይሆን አዲስ ነገር መስሎ የተሰማኝ? እንዲህ እንድል ያደረገኝ፣ ነገሩን ለጓደኞቼ ሳጫውታቸው ብዙም አለመገረማቸውን ማስተዋሌ ነው፡፡ አለመገረም ብቻም ሳይሆን፣ እነሱም መሰል ገጠመኞቻቸውን አውግተውኛል፡፡ አንድ ጓደኛዬ እንደውም “አንዳንድ ቦታማ ድንኳኑን ግሮሰሪ ነው የሚያስመስሉት” ብሎኛል፡፡

እንዴት ነው ነገሩ ጎበዝ፤ ከባህላችን ከማፈንገጥ ባሻገር ሌላ አሉታዊ ተጽዕኖስ ያለው አይመስላችሁም? እስቲ አስቡት፤ አንድ ሀዘንተኛ ለማጽናናት የመጣ ለቀስተኛ፣ በሞቅታ ተገፋፍቶ ከ20 ዓመት በፊት የሞተ ቤተሰቡን አልያም ዘመዱን አስታውሶ እዬዬውን ሲያስነካው አልታያችሁም? እሱን ለማጽናናት ወይም ዝም ለማስባል ሲባል የሚፈጠረውን ሁኔታስ አስባችሁታል? ለቅሶ ቤት “ችርስ” እየተባባሉ ብርጭቆ ማጋጨትንስ? በዚህ ዓይነት፣ “እግዜር ያጽናችሁ ለማለት ብሎ እግዜር ይማረው ወይም ይማራት ብሎ የሚሰናበት ሰውስ አይኖር ይሆን?

የታዘብኩት ነገር በዚያ ደረጃ ባይሆንም፣ ውሎ ሲያድር ያው ሂደቱ ወደዚያው ማምራቱ የሚቀር አይመስልም፡፡ 

ሌላው ገጠመኜ ለመጀመሪያ ጊዜ የሟች የህይወት ታሪክ መጻፌ ነው፡፡ የህይወት ታሪክ ይጻፍ ሲባል፣ ማን ይጻፈው? የሚል ነገር ተነሳ፡፡ ያኔም ጉዳዩ ወደ እኔ መጣ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ “ጋዜጠኛ አይደለ” የሚል ነበር፡፡

የህይወት ታሪክ መጻፍ ወግ እንደመጻፍ አይደለም፡፡ አለ አይደል፤ የተለመደ ደግ፣ ቸር ሩህሩህ በሚል ሰውዬውን ከሰውነት ተራ አውጥቶ፣ ከመላእክት ወገን የመመደብ አይነት ነገር አለው፤ በባህላችን “ሙት አይወቀስም” የሚል ቢሂል ስላለ ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የነጮቹ ነገር ከእኛ ይለያል፡፡

እዚህ ላይ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፤ በአንድ ወቅት ከአንድ መጽሀፍ ላይ ያነበብኳቸው የመቃብር ላይ ጥቅሶች። ከደራሲ ኤፍሬም ገ/ እየሱስ ጽሁፍ ጥቂት ልበላችሁ፡-

“የተንኮል ጽዋው ሞልቶ የፈሰሰ ለነበረ አንድ ክፉ ሰው እንዲህ በማለት እፎይታ የተሰማቸው ዘመዶቹ መቃብሩ ላይ ጻፉለት፡-

“መልካም ያላደረገ እዚህ ያርፋል፡፡ በየሄደበት የሰራውን ማን ያውቃል? ጠያቂም የለው ተረስቷል፡፡”

ዝም ብትል መቀጮ የሚጣልባት የሚመስላት ዓይነት አለብላቢት የሆነች አንዲት ሴት መቃብር ላይ ደግሞ፡

“ሚስስ አራቦራ እዚህ አርፋለች፡፡ ወደ ትቢያም ትለወጣለች፡፡ በወርሀ ሚያዚያ ነው በሞት የተነጠቀች፡፡ ያን ጊዜም ነበር አፏን የያዘች” ሲሉ ቀባሪዎቿ መቃብሯ ላይ ጻፉ፡፡

አንድ ልመርቅላችሁና ይብቃኝ፡፡ የተጠረበ እምነበረድ ቀርቶ ፍልጥ እንጨት እንኳ ሊቆምለት የማይገባ ነበር፡፡ ውቧን ዓለማችንን ሲሰናበት ያደረገው ንግግርም በትዕዛዙ መሰረት መቃብሩ ላይ ሰፍሮለት ይገኛል፡-

“ክቡር አንባቢ ሆይ፤ ያገኘሁትን ስበላ ስጠጣ ኖርኩኝ፤ አሁን በተራዬ እኔም በትል እየተበላሁ ነኝ”

ያው እንግዲህ እኔ ደግሞ እንደተለመደውና እንደባህላችን የሟችን የህይወት ታሪክ መክተቤ የግድ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ግን፤ እኔ ከማውቀውም ሆነ እንድጽፍ ከተነገረኝ መሀል አንድ ጎልቶ ያስተዋልኩት እውነታ ነበር፤ በብዙ ለቀስተኞች ምስክርነት ጭምር የተገለጸው የሟች ደግነት፡፡ እናም “… ለሰዎች መልካም ነገርን በማድረግና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በመርዳት የሚታወቁ ደግ ሰው ነበሩ፡፡ …” በማለት ስጽፍ እጄ አልታዘዝ አላለኝም፡፡

ከለቅሶ ጋር በተያያዘ ሌላው የምንታዘበውና የሚነሳው ነገር ሟችን በቁም መርዳት እየተቻለ ችላ ብሎ፣ ሲሞት ያዙኝ ልቀቁኝ የማለቱ ነገር ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ሰውዬውን በገንዘብ፣ በጊዜና በመሰል ሁኔታ መርዳት ሲችሉ በቸልተኝነት ያለፉትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህን ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፤ አንድ ሰው መቃብር ላይ የተጻፈ በሚል የሆነ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያየሁት  ጽሁፍ፡፡ እንዲህ ይላል፡-

“መታመሜን ነግሬያችሁ ነበር፡፡” 

የመልዕክቱ ባለቤቶች የሚለበልባቸውን የጸጸት ሳማ አስቡት፡፡

እንግዲህ በተቻለን መጠን የቻልነውን ነገር ማድረጉ ኋላ ላይ ከሚመጣ ጸጸትና የህሊና ወቀሳ ያድናል፡፡ ደግሞ የደግነት ትንሽ የለውም፤ ምክንያቱም ከልባዊ ፍቅርና ፍላጎት የሚመነጭ ስጦታ ነውና! …

እዚህ ላይ፡-

    ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፥

    ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፡፡

የምትለዋን የደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም አስታውሼ ልቀጥል፡፡

በነገራችን መካከል፤ ለቅሶ ለረጅም ጊዜ ሳንተያይ ከቆየናቸው ወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር የምንገናኝበትም ነው፡፡ አሁን ላይ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ባሻን ጊዜ በአካል ለመገናኘትና ለመጠያየቅ ሁኔታዎች ይገድቡናል። በዚህ የተነሳ ድንኳን ውስጥ የሚወራ ወሬ አይጠፋም፡፡ ሁሉም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ትዝታውን ያወጋል፡፡ ስላሳለፈውና ስለገጠመው ነገር ይጨዋወታል፡፡

እኔም በነበረኝ ቆይታ ካየኋቸው ረጅም ዓመት የሆኑኝ ዘመዶቼን አግኝቼ ማውጋቴ አልቀረም፡፡ በዚህ መሀል ታዲያ፣ አንዲት ቀልድ ወዳድ ዘመዴ ስንለያይ የተናገረችኝ ነገር አግራሞትን አጭሮብኛል፡-

“በል እንግዲህ ሌላ ለቅሶ ላይ ለመገናኘት ያብቃን፡፡” 

ነገሩ ቀልድ ሊመስል ይችላል፡፡ ግን ደግሞ መራራ እውነትም ነው፡፡ ያለው የኑሮ ሁኔታና የጊዜ መጣበብ ያመጣው ሀቅ፡፡

ብቻ እንኳንም ቴክኖሎጂ የዘመነበትና ሶሻል ሚዲያ ያለበት ዘመን ላይ ሆንን፡፡ በፊት ጊዜ “ደብዳቤ በአካል የመገናኘት ግማሽ ነው” ይባል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በፈጣን መልዕክት ማድረሻ ቴክኖሎጂዎች ነገሩ ሩብ ጉዳይ የሆነ ይመስላል፤ ምንም እንኳ የመገናኘትን ያህል ባይሆንም፡፡ ያኔ፡-

ደብዳቤ ቢጽፉት እንደአካል አይሆንም፣

እንገናኝና ልንገርህ ሁሉንም፡፡

እንዳለችው ድምፃዊ ዓይነት መሆኑ ነው፡፡

ለማንኛውም የአክስቴን ልጅ ምን አልኳት መሰላችሁ፡-

“እንግዲህ ተረኛ እኛ ካልሆን እንገናኛለን!”

እና ምን ልበላት ታዲያ፡፡ አብሮ አደጌ ነች፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ስንገናኝም ቀልዷና የተለየ ሳቋ ያልጠፋ፡፡ እየተከፋች እንኳ ፊቷ ላይ ፈገግታ የማይጠፋ፣ ግን ደግሞ በማስመሰል ጭንብል የምትደበቅ ሳትሆን በተስፋ ጮራ የምትፈካ ትመስለኛለች፡፡

ያው ሞት የተራ ጉዳይ ነው፡፡ የነገዋ ጀንበር ስትፈነጥቅ የሚፈጠረውን ነገር ማን ያውቃል? ብቻ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ነው። እንዴት ካላችሁኝ፤ ባለን ጊዜ መልካሙን በማሰብና በመስራት በመኖር ነው ምላሼ፡፡ የሚቻለው ሞትን ማስቀረት ሳይሆን ስምን ከመቃብር በላይ ማዋል ነውና፡፡ ይህን ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? ጀግናው ሌ/ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ መቃብር ላይ የተጻፈ አንድ ጥቅስ፤ እንዲህ ይላል፡-

“ሰው ምን ጀግና ቢሆን መልአከ ሞትን ድል ማድረግ አይቻለውምና መዘጋጀት ያሻል!”

እንግዲህ የዛሬውን በዚሁ አብቅቼ ልሰናበታችሁ ነው፡፡ የሳምንት ሰው ይበለንማ፤ ሰላም!