በእንስሳት እርባታ ከተሰማራን ወዲህ ኑሯችን ተሻሽሏል – የጋዘር ከተማ ወጣቶች

በእንስሳት እርባታ ከተሰማራን ወዲህ ኑሯችን ተሻሽሏል – የጋዘር ከተማ ወጣቶች

ሀዋሳ፡ ግንቦት 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወተት ላምና እንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ተሠማርተው መስራት ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን በኣሪ ዞን የደቡብ ኣሪ ወረዳ ጋዘር ከተማ ወጣቶች ገለፁ።

የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት በበኩሉ በወረዳው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ተግባራትን በማጠናከር የከተማ ነዋሪውን ማህበረሰብ የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላ እየተሠራ እንዳለ ገልጿል።

የሌማት ትሩፋት የግለሰቦችን የሥርዓተ ምግብ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የአካባቢውን ህብረተሰብ የእንስሳት ተዋጽኦ አቅርቦት ችግር በመቅረፍ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በኣሪ ዞን ደቡብ ኣሪ ወረዳ ጋዘር ከተማ በአንድ የወተት ላም እርባታ የጀመረው አቶ ፍቅሬ ጌታቸው አሁን ላይ የላሞቹን ቁጥር በመጨመር በቀን ከ20 ሊትር በላይ ወተት በማምረት በወር ከ12 ሺህ እስከ 14 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኝ ይናግራል።

ሌላኛው በከተማው የነጋይ እንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሉቃስ ቴልሞስ፤ ማህበራቸው ከመንግስት በተመቻቸላቸው 1 መቶ ሺህ ብር ብድር ጀምረው አሁን ላይ የተበደሩትን ገንዘብ ከግማሽ በላይ መልሰው መቶ ሺህ ብር የሚገመት ቋሚ ንብረት ማፍራታቸውን ተናግሯል።

በቀጣይ ዘርፋቸውን በማስፋት ከሚያገኙት ጥቅም ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በኣሪ ዞን የደቡብ ኣሪ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ደይዳቅ እንደገለፁት፤ በወረዳው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ አተገባበርን ስኬታማ ለማድረግ የዝርያ ማሻሻል፣ የምርጥ ዘር አቅራቦትና የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ላይ ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

በዘርፉ በንቅናቄና በዕቅድ በተሰራው ስራ ከግለሰቦች ባለፈ የወረዳውን ማህበረሰብ የተመጣጠነ የሥርዓተ ምግብ አቅራቦት ችግሮችን ማረጋጋት እንደተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል።

በቀጣይ የእንስሳት ጤና እና መኖ አቅራቦት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከተጠሪ ተቋማትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አቶ አሸናፊ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን